የዮዲት ምክር
1ዮዲትም፥ “ወንድሞች፥ ስሙኝ፤ ይህን ቸብቸቦ ይዛችሁ በግንቡ ጫፍ ላይ ስቀሉት። 2ከዚህ በኋላ ሲነጋ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ሁላችሁም የጦር መሣሪያችሁን ያዙ፤ አርበኞች የሆኑ ሰዎች ሁሉ ከከተማ ወደ ውጭ ይውጡ፤ የአሦራውያን ሠራዊት ጠባቂዎችም ወዳሉበት ቦታ እንደምትወርዱ ሆናችሁ አለቃ ለራሳችሁ ሹሙ። ነገር ግን አትውረዱ። 3ሁላችሁም የጦር መሣሪያችሁን ያዙ፥ ዘበኞችም ባዩአችሁ ጊዜ የአሦር ሠራዊት አለቆችን ይቀሰቅሱ ዘንድ ወደ ሰፈራቸው ይሄዳሉ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሆሎፎርኒስ ድንኳን ይሮጣሉ፤ አያገኙትም፤ ከዚያም በኋላ እጅግ ፈርተው ከፊታችሁ ይሸሻሉ። 4ከዚህ በኋላም እናንተና በእስራኤል አውራጃ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ተከተሏቸው፤ በጎዳናቸውም ሁሉ ርገጡአቸው። 5ይህንም ከማድረጋችሁ በፊት የእስራኤልን ወገን የካደውን ከእኛም ጋር ይሞት ዘንድ እርሱን ወደ እኛ የላከውን እርሱ መሆኑን አይቶ ያውቅ ዘንድ አሞናዊውን አክዮርን ጥሩልኝ” አለቻቸው። 6አክዮርንም ከዖዝያን ቤት ጠሩት፤ መጥቶም የሆሎፎርኒስን ራስ በአንድ ሰው እጅ ባየ ጊዜ ሰውነቱ ደንግጦ በሕዝቡ ጉባኤ መካከል በግንባሩ ወደቀ። 7በአነሡትም ጊዜ በዮዲት እግር ላይ ወደቀ፤ ሰገደላትም፤ “ከይሁዳ ቤትና ከሕዝቡ ሁሉ አንቺ የተባረክሽ ነሽ፤ ስምሽንም ሰምተው ይደነግጣሉ። 8አሁንም በእነዚህ ወራት ያደረግሺውን ንገሪኝ” አላት። ዮዲትም ከወጣች ጀምሮ እስክትመለስ ድረስ ያደረገችውን ሁሉ በሕዝቡ መካከል ነገረችው። 9ነገሯን ተናግራ በጨረሰች ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ቃላቸውን አሰምተው ደነፉ፤ በየከተማቸውም በደስታ ቃል ጮኹ። 10አክዮርም እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ተአምራት በአየ ጊዜ ፈጽሞ በእግዚአብሔር አምኖ ተገዘረ። እስከ ዛሬም ድረስ ከቤተ እስራኤል ጋር አንድ ሆነ።
የሆሎፎርኒስ ሞት እንደ ተገለጠ
11በነጋም ጊዜ የሆሎፎርኒስን ቸብቸቦ በግንቡ ላይ ሰቀሉት፤ ወንዶቹም ሁሉ መሣሪያቸውን ይዘው ወጡ፤ በተራራውም ዐቀበት በኩል ከበቧቸው። 12የአሦር ሠራዊትም በአዩአቸው ጊዜ ወደ ሹሞቻቸው ላኩ፤ እነርሱም ወደ አለቆቻቸው፥ ወደ ሹሞቻቸውና ገዢዎቻቸው ሄዱ። 13ወደ ሆሎፎርኒስም ድንኳን መጥተው ለመጋቢው፥ “እነዚህ ባሮች እስከ መጨረሻው ይጠፉ ዘንድ ሊዋጉን ተደፋፍረው ወርደዋልና ጌታችንን ከእንቅልፉ ቀስቅሰው” አሉት። 14ባግዋም ከዮዲት ጋር የተኛ መስሎታልና ገብቶ በድንኳኑ አንጻር ያለ በሩን መታ። 15ቃል የሚመልስለት ሰውም በአጣ ጊዜ ድንኳኑን ተርትሮ ወደ እልፍኙ ገባ፤ ሬሳውንም በወለሉ ላይ ወድቆ አገኘው። ራሱም በላዩ አልነበረም። 16እያለቀሰና እያቃሰተ በታላቅ ቃል ፈጽሞ ጮኸ፤ ልብሱንም ቀደደ። 17ዮዲትም ወደምታድርበት ድንኳን ገባ፤ ነገር ግን አላገኛትም፤ ወደ ሕዝቡም እየሮጠ ሄዶ ጮኸላቸው። እንዲህም አላቸው፦ 18“እነዚህ ባሮች አታለሉን፤ እነሆ፥ የሆሎፎርኒስ ሬሳው በምድር ላይ ወድቋልና፥ ራሱም በላዩ የለምና አንዲት ዕብራዊት ሴት በንጉሡ በናቡከደነፆር ቤት ላይ ኀፍረትን አድርጋለች።” 19የአሦር የሠራዊት አለቆችም ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ሰውነታቸውም ፈጽማ ደነገጠች፤ በታላቅ ድምፅም በሰፈር መካከል ፈጽመው ጮኹ።