አሦራውያን ደንግጠው መሸሻቸው
1በሰፈርም የነበሩ ሰዎች በሰሙ ጊዜ ስለ ተደረገው ነገር ደነገጡ፤ 2ፍርሀትና እንቅጥቅጥም ያዛቸው፤ ከባልንጀራውም ጋር የቆመ ሰው አልነበረም። ነገር ግን ሁሉም ደንግጠው ወደ ምድረ በዳውና ወደ ተራራማው ሀገር በአንድነት ሸሹ። 3እነዚያም በቤጤልዋ ዙሪያ፥ በሰፈሩና በተራራማው ሀገር የነበሩ ሰዎች ሁሉ ተሸብረው ሸሹ፤ ያንጊዜም አርበኞች የሆኑ የእስራኤል ወንዶች ልጆች ሁሉ ተነሥተው ተከተሏቸው። 4ዖዝያንም ስለ ሆነው ሁሉ ይናገሩ ዘንድ፥ ሁሉም ይረዱ ዘንድ፥ ጠላቶቻቸውንም ተከትለው ያጠፏቸው ዘንድ፥ ወደ ቤጦምስታምና ወደ ቢቤ፥ ወደ ኮቤና ወደ ኮላ ወደ እስራኤልም አውራጃ ሁሉ ላከ። 5የእስራኤልም ልጆች በሰሙ ጊዜ ሁሉም በአንድነት እስከ ኮቤ ድረስ ተከትለው አጠፏቸው፤ በጠላቶቻቸው ሰፈር የሆነውን ነገር ነግረዋቸዋልና ከኢየሩሳሌምና ከአውራጃዋ ሁሉ የመጡ ሰዎች እንደዚሁ አጠፏቸው፤ ከገሊላና ከገለዓድም የመጡ ሰዎች አባረሯቸው፤ ከደማስቆና ከአውራጃዋም እስኪሻገሩ ድረስ ታላቅ ሰልፍ አድርገው አጠፏቸው። 6በቤጤልዋም የሚኖሩ ሰዎች ወደ አሦራውያን ሰፈር ወርደው ገንዘባቸውን በዘበዝዋቸው፤ ፈጽመውም ከበሩ። 7ከዚህ በኋላም የእስራኤል ልጆች ከተዋጉበት ተመለሱ፤ ከብዙ ዘመን ጀምሮ ሰፊ አውራጃቸውን ይዘውባቸው ነበርና የቀሩትን በተራራማው ሀገርና በሜዳው የነበሩትን መንደሮችና ከተሞች ወሰዱ።
እስራኤላውያን የድል በዓል ማክበራቸው
8ታላቁ ካህን ኢዮአቄምና በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የእስራኤል ልጆች ሽማግሌዎችም እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን በጎ ነገር ያዩ ዘንድ፥ ዮዲትንም ያዩአት ዘንድ፥ ከእርሷም ጋራ ሰላምታ ያደርጉ ዘንድ መጡ። 9ወደ እርሷም በገቡ ጊዜ ሁሉም በአንድነት መረቋት፤ እንዲህም አሏት፥ “የኢየሩሳሌም ልዕልና አንቺ ነሽ፤ የእስራኤልም ክብራቸው አንቺ ነሽ፤ የወገኖቻችንም መመኪያ አንቺ ነሽ፤ 10ይህ ሁሉ በእጅሽ ተደርጓልና፥ ይህንም በጎ ነገር ለእስራኤል አድርገሻልና፥ እግዚአብሔርም እነርሱን ወዷልና፥ ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ለዘለዓለሙ ይባርክሽ!” ሕዝቡም ሁሉ፥ “አሜን” አሉ። 11ሕዝቡም ሠላሳ ቀን ሰፈራቸውን በረበሩ፤ ለዮዲትም የሆሎፎርኒስን ድንኳንና የብሩን ዕቃ ሁሉ፥ ዙፋኑንና ያለውንም ገንዘብ ሁሉ ሰጧት፤ እርሷም ወስዳ በበቅሎዋ ጫነች፤ ሠረገላዎችዋንም ነድታ ከእርሷ ጋር ይዛ ገባች። 12የእስራኤልም ሴቶች ሁሉ ያይዋት ዘንድ፥ ይመርቋትም ዘንድ ወደ እርሷ ሮጠው ተሰበሰቡ፤ ታላቅ በዓልንም አደረጉላት፤ ዘንባባውንም በእጅዋ ያዘች፤ ከእርሷ ጋራ ላሉ ሴቶችም ሰጠች። 13ለእርስዋና ከእርስዋ ጋር ለነበረችውም ብላቴና የወይራ ጕንጕን አደረጉላቸው፤ በሕዝቡም ፊት ሴቶችን ሁሉ እየመራች በዝማሬ ሄደች፤ የእስራኤልም አርበኞች ሁሉ የጦር መሣሪያቸውን ከዘንባባ ጋር ይዘው እየዘመሩ ተከተሏት።