1የፈጠረህን ዕወቀው፤ ያጸናህና ያዳነህ የእስራኤልን ቅዱስም አትርሳው፤ አንተ መሬት ስትሆን በመልኩና በምሳሌው ፈጥሮሃልና ደስ ይልህ ዘንድ፥ ምድርንም ትቈፍራት ዘንድ በገነት አኖረህ። 2ትእዛዙንም ባፈረስህ ጊዜ ከዚያ ከገነት አሜከላና እሾህ ወደምታበቅል፥ በአንተም ምክንያት ወደ ረገማት ወደዚች ምድር አወጣህ። 3አንተ ምድር ነህና፥ እርስዋም ምድር ናትና፥ አንተ ትቢያ ነህና፥ እርስዋም ትቢያ ናትና፥ አንተ መሬት ነህና እርስዋም መሬት ናትና ከእርስዋም ትመገባለህ፤ ወደ እርስዋም ትመለሳለህ፤ ያስነሣህ ዘንድ እስኪወድድ ድረስ ትቢያ ትሆናለህና የሠራኸውን በደልና ኀጢአት ሁሉ ይመረምርሃልና። 4ያንጊዜ የምትመልሰውን ዕወቅ፤ በዚህም ዓለም የሠራኸውን ክፉውንና በጎውን አስብ፤ ክፉው ይበዛ እንደ ሆነ፥ ወይም በጎው ይበዛ እንደ ሆነ መዝን፤ ምከርም። 5በጎ ነገርንም ብታበዛ፥ ሙታን በሚነሡበት ቀን ደስ ይልህና ሐሤት ታደርግ ዘንድ ለአንተ መልካም ይሆንልሃል። 6ክፉ ሥራን ብታበዛ ግን ወዮልህ፤ እንደ እጅህ ሥራና እንደ ልቡናህ ክፋት ፍዳህን ትቀበላለህና በባልንጀራህ ክፉ እንደ ሠራህበት፥ እግዚአብሔርንም እንዳልፈራኸው እንደ ሥራህ ፍዳህን ትቀበላለህና። 7ባልንጀራህንም ብትከዳው፥ በእግዚአብሔርም ስም በሐሰት ብትምል፥ እንደ ሥራህ ፍዳህን ትቀበላለህና። 8ለባልንጀራህ በማስመሰል ቃልህን በሐሰት እውነተኛ እንዲሆን ታደርጋለህና፤ አንተ ግን ሐሰት እንደ ተናገርህ ታውቀዋለህ። 9ከአንተ ጋራ ያሉትንም እያሳመንህ ቃልህ እውነት እንደ ሆነ ታጸናለህ፤ እውነት ያልሆነ ነገርንም ታበዛለህ፤ እንደ ሥራህም ፍዳህን ትቀበላለህ፤ የማትሰጠውን ለባልንጀራህ እሰጥሃለሁ እያልህ ባልንጀራህን ትከዳዋለህ። 10በንጹሕ ልቡናህም እሰጣለሁ ባልህ ጊዜ አጋንንት እንደ ውሾች ደጅ ይጠኑሃል፤ ሁሉንም ያስረሱሃል፤ ብትነሣም፥ ትሰጥ ዘንድ ብትወድም የማይጠቅምህንና የማትበላውን ገንዘብ ታደልብ ዘንድ የዚህ ዓለም ገንዘብ ያስጎመጅሃል፤ “ይሰበስባሉ፤ የሚሰበስቡለትንም አያውቁም” ብሏልና። 11ዳግመኛም “ሐሰተኞች የአዳም ልጆች ሚዛንን ሐሰተኛ ያደርጋሉ፤ እነርሱስ መቼም መች ከከንቱ ወደ ከንቱ ይሄዳሉ” ብሏልና። 12ሰዎች ሆይ ሚዛንንና ላዳንን በማሳበል፥ የሌላውንም ገንዘብ በመስረቅና በዐመፅ ወደ ገንዘባችሁ በመጨመር፥ የባልንጀራችሁንም ገንዘብ፥ የባልንጀራችሁንም እርሻ በመድፈር፥ ለባልንጀራችሁ ያይደለ ለራሳችሁ ትርፍ በምታደርጉት ሁሉ ዐመፅን ተስፋ አታድርጓት። 13ይህንም ብታደርጉ እንደ ሥራችሁ ትቀበላላችሁ። 14ሰዎች ሆይ በሚገባ በእጃችሁ ሥራ ተመገቡ እንጂ ቅሚያን አትታመኗት፤ በማይገባ ያለ ፍርድ በመቀማትና በመንጠቅ የሰውን ገንዘብ ትበሉ ዘንድ አትውደዱ። 15ብትበሉትም አያጠግባችሁም፤ ብታደልቡትም በምትሞቱበት ጊዜ ለሌላ ትተዉታላችሁ እንጂ አይጠቅማችሁም። 16ገንዘባችሁም ቢበዛ ልቡናችሁን አታኵሩ፤ የኀጢአተኞች ሰዎች ገንዘብ ከምድጃ እንደሚወጣ፥ ነፋስም እንደሚወስደው እንደ ጢስ ነውና፥ ከብዙ የኀጢአተኞች ገንዘብ በእውነት ያለ ጥቂት ገንዘብ ይሻላል።