1ጌታውም አዳምን ይቤዠው ዘንድ አለው፤ አንተንም ያሳፍርሃል፤ በጉንም ከተኵላ አፍ ያድነዋል። 2ነገር ግን አንተ የገዛሃቸውን ሰዎች ከአንተ ጋር ይዘህ ወደ ጥፋት ትሄዳለህ። 3የፈጣሪያቸው የእግዚአብሔርን ሕግ የጠበቁ ግን የእርሱ እድል ፋንታ ያደርጋቸው ዘንድ፥ የፈጣሪያቸው የእግዚአብሔርንም ሕግ እንዳንተ ካልተላለፉ ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር ያመሰግኑት ዘንድ ከክፉ ሥራህ ከሰወራቸው ከፈጣሪያቸው ከእግዚአብሔር ጋር ደስ ይላቸዋል። 4አንተ ግን ከመላእክቱ ጋራ ታመሰግነው ዘንድ እንደ አንተ ካሉት ሁሉ ይልቅ መርጦ የሰጠህ እግዚአብሔር በትዕቢትህ ከፍ ያለ ዙፋንን ነሳህ። 5አንተም ታበይህ፤ ዲያብሎስም ተባልህ፤ ሠራዊቶችህም አጋንንት ተባሉ። 6እግዚአብሔርን የሚወዱ ግን እንደ ቅዱሳን መላእክት ለእርሱ ወገኖቹ ይሆናሉ፤ የሚያመሰግኑት ሱራፌልና ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘርግተው ያለማቋረጥ ያመሰግናሉ። 7አንተ ግን በመልክህ ከተፈጠሩ ከነገድህና ከሠራዊትህ ጋር ሁልጊዜ ታመሰግነው ዘንድ ምስጋናህን በትዕቢትህና በስንፍናህ አጠፋህ። 8እንደ አንተ ያለ መፍጠር የማይቻለው መስሎህ አንተ የፈጠረህ የእግዚአብሔርን ምስጋና በዘነጋህ ጊዜ፥ ዐሥረኛ ነገድ አድርጎ የፈጠረህ የእግዚአብሔር ምስጋናው እንዳይጐድል አንተም ከወንድሞችህ አንድነት በተለየህ ጊዜ የፈጠረህ የእግዚአብሔር ምስጋናው እንዳይጐድል፥ 9አንተም በልቡናህ ትዕቢት የፈጠረህ የእግዚአብሔርን ምስጋና ቸል ባልህ ጊዜ፥ እርሱም በተቈጣህና፤ በተዘባበተብህ ጊዜ፤ ከሠራዊቶችህም ጋራ በገሃነም እንቅጥቅጥ በአጋዘህ ጊዜ 10በቅዱሳት እጆቹ ከምድር መሬትን ወሰደ፤ ውኃንና እሳትን፥ ነፋስንም ጨመረ፤ አዳምንም በመልኩና በምሳሌው ፈጠረው። 11ምስጋናው በአንተ ጉድለት ይመላ ዘንድ በእጁ በፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ላይ ሾመው። የመሬታዊውም ምስጋና ከሰማያውያኑ ምስጋና ጋር ተጨመረ፤ ምስጋናቸውም እኩል ሆነ። 12አንተ ግን በትዕቢትህና በአንገትህ መደንደን ተሰደድህ፤ ከፈጠረህ ከእግዚአብሔርም ጌትነት ወጥተህ ራስህን አጠፋህ። 13የእግዚአብሔርነቱ ምስጋና እንዳይጐድል እግዚአብሔር በፈቃዱ ምክር የሚያመሰግነውን ፈጥሯልና ምስጋናው እንዳይጐድል ዕወቅ። 14እርሱ ሳይደረግ ሁሉን ያውቃልና፥ ትእዛዙንም እንደምታፈርስ ሳይፈጥርህ ዐወቀህ፤ ዓለም ሳይፈጠር በእርሱ ዘንድ የተሰወረ ምክር ነበረና በካድኸው ጊዜ ባርያው አዳምን በመልኩና በምሳሌው ፈጠረው። 15ሰሎሞን፥ “ከኮረብቶች በፊት ወለደኝ፤ ዓለምም ሳይከናወን የምድርም መሠረት ሳይመሠረት፥ 16የተራራዎችና የኮረብቶች መቋምያ ሳይተከል፥ የዓለምም ጐዳና ሳይጸና፥ የፀሐይና የጨረቃ ብርሃን ሳይበራ፥ የከዋክብትና የዘመኖች ምግብና ሳይታወቅ፥ 17ሌሊትና መዓልት ሳይፈራረቁ፥ ባሕርም ባሸዋ ሳትወሰን፥ የተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ሳይፈጠር፥ 18ዛሬም የሚታየው ሁሉ ሳይታይ፥ ዛሬ የሚጠራው ስም ሁሉ ሳይጠራ ፈጠረኝ” ብሎ እንደ ተናገረ፥ አንተና እንዳንተ ያሉ መላእክት፥ ባርያው አዳምም በእግዚአብሔር ኅሊና ውስጥ ነበራችሁ። 19አንተ በካድህ ጊዜ ቅዱስ ስሙ ይመሰገን ዘንድ፥ አንተም በታበይህ ጊዜ ከመሬት በፈጠረው በተዋረደ በባርያው በአዳም ይመሰገን ዘንድ አዳምን ፈጠረው። 20እግዚአብሔር የድሆችን ጸሎት ከሩቅ ይሰማልና፥ የተዋረዱ ሰዎችንም ምስጋና እግዚአብሔር ይወዳልና። 21እግዚአብሔር የትዕቢተኞችን ነገር ቸል ይላል፥ የፈረስን ኀይል አይወድምና፥ በሰው ጕልበትም ደስ አይለውምና። 22ነገር ግን እግዚአብሔር በሚፈሩትና ስለ ኀጢአታቸው ጩኸው በሚያለቅሱ ደስ ይለዋል። 23አንተ በንስሓ መናዘዝ ተሳነህ። 24ያ መሬት ግን ስለ ኀጢአቱ በእግዚአብሔር ፊት ፈጽሞ እያለቀሰ በንስሓ ተመለሰ። 25አንተስ በልብህ ትዕቢትና በአንገትህ መደንደን የሰላም መንገድን አላወቅሃትም፥ ንስሓንም አላወቅሃትም፥ በንስሓ፥ በልቅሶና በእንባ በፈጣሪህ በእግዚአብሔር ፊት መናዘዝ ተሳነህ። 26ያ አመድና መሬት የሆነ ድሃ ግን በልቅሶና በእንባ ወደ ንስሓ፥ ወደ ሰላምና ወደ ትሕትና መንገድ ተመለሰ። 27አንተስ ለፈጠረህ ለእግዚአብሔር ራስህንና የልብህን ቀፈት አላዋረድህም። 28እርሱ ግን በበደለው በደል ራሱን አዋርዶ ተናዘዘ፤ አልታበየምም። 29ያንም ስሕተት የፈጠረው እርሱ አይደለም። ከአንተ የተገኘ ነው እንጂ፥ ወንጀልን ፈጥረህ አውጥተኸዋልና። በትዕቢትህም ከአንተ ጋራ ወደ አንተ ጥፋት ወሰድኸው። 30ሁለታችሁን ሁሉ ሳይፈጥራችሁ ዐውቋችኋልና፥ አካሄዳችሁንም ዐውቋልና ይህ የተደረገ በልብህ ትዕቢት እንደ ሆነ እርሱ ያውቃል። 31ያን የትዕቢት ተንኰል የሌለውን ግን በንስሓ፥ በልቅሶና በእንባ መለሰው። 32አንተ ግን በልብህ ትዕቢት በንስሓ መናዘዝ ተሳነህ። በድሎ በንስሓ የማይናዘዝ ሰው ከቀድሞ በደሉ ይልቅ በደሉን ያከፋልና። 33ነገር ግን በድሎ በፈጣሪው በእግዚአብሔር ፊት የሚናዘዝና የሚያለቅስ፥ እርሱ በእውነት ንስሓ ገባ፤ የጌታውንም ልብ ያራራ ዘንድ የመዳኑን መንገድ አገኘ፤ በጌታውም ፊት ተናዘዘ፤ ጌታውም በባሪያው ላይ ይቈጣ ዘንድ ቀድሞ ከመከረበት ያቃልልለታል፤ በብዙ ንስሓና ስግደት ተናዝዞአልና። የቀደመ ኀጢአቱንም ይቅር ይለዋል። 34ወደ ቀደመ በደሉም ካልተመለሰ፥ ይህንም ካደረገ ይህ ፍጹም ንስሓ ነው። አዳምስ ፈጣሪውን ማሰብንና ለፈጣሪው መናዘዝን አልዘነጋም። 35አንተም ለፈጣሪህ በንስሓ ተናዘዝ፤ በእርሱ ላይና በእጁ ሥራ ላይም በደልን አታብዛ፤ እነርሱ ሥጋውያንና ደማውያን ስለ ሆኑ የፈጠራቸው እግዚአብሔር ድካማቸውን ያውቃልና። 36ነፍሳቸውም ከተለየች በኋላ ሥጋቸው እግዚአብሔር እስከፈቀዳት ቀን ድረስ ትቢያ ይሆናል።