1ለአንተስ ፈጣሪህ ወደላከህ እየተላክህ ፈጽመህ ታመሰግን ዘንድ አንድ አሳብን ፈጠረልህ። 2ለአዳም ግን ክፉ የሆኑ አምስት አሳቦችና በጎ የሆኑ አምስት አሳቦች ዐሥር አሳቦች ተሰጡት። 3ዳግመኛም እንደ ባሕር ሞገድ፥ ከምድርም አንሥቶ ትቢያን እንደሚበትን ጥቅል ነፋስ፥ ነፋስም እንደሚያናውጠው እንደ ባሕር ሞገድ የሚታወኩ ብዙ አሳቦች አሉት፤ እንደማይቈጠር እንደ ዝናብም ጠብታ በልቡ ከአለ ከማይቈጠር ከአሳቡ ብዛት የተነሣ የአዳም አሳብ እንደዚሁ ነው። 4የአንተ ግን አሳብህ አንዲት ናት፤ ሥጋዊ አይደለህምና ሌላ አሳብ የለህም። 5አንተ ግን በእባብ ልቡና አድረህ አንድ አካል የሆነ አዳምን በክፉ ሽንገላ አጠፋኸው፤ ሔዋንም የእባብን ነገር ሰማች፤ ሰምታም እንዳዘዘቻት አደረገች። 6መጥታም የእግዚአብሔር መጀመሪያ ፍጥረቱ አዳምን የበለስን ፍሬ በማብላት አሳተችው፤ የፈጣሪዋንም ትእዛዝ ስለ ተላለፈች በእርስዋና በልጆችዋ ሞትን አመጣች። 7በእግዚአብሔርም እውነተኛ ፍርድ ከገነት ወጡ፤ ተጣልቶም ከገነት አላራቃቸውም። ነገር ግን በተሰደዱበት ምድር በሆዳቸው ፍሬ በልጆቻቸውና በምድራቸው ፍሬ አረጋጋቸው። 8በቅንአትህም ከገነት ባስወጣሃቸው ጊዜ እግዚአብሔር ከገነት የለመለሙ ዕፀዋትን ሰጣቸው፤ ይተክሉ ዘንድ እግዚአብሔር በሰጣቸው በገነት ፍሬና በምድር ፍሬ ይረጋጉ ዘንድ፤ 9ልጆችን በማየት፥ ገነትንና ምድር ከአፈር ያበቀለችውን የምድር ፍሬ በማየት ልቡናቸውን እጅግ ደስ ያሰኙ ዘንድ፤ እርሱንም በበሉ ጊዜ ከገነት እነርሱን ካስወጣህበት ኀዘን ፈጽመው ይረጋጋሉ። 10እግዚአብሔርም ፍጥረቱን ማረጋጋት ያውቃልና በልጆቻቸውና በምድር ፍሬ ልቡናቸው ይረጋጋል። 11ወደዚች የእሾህና የአሜከላ ምድርም ተሰደዋልና ልቡናቸውን በእህልና በውኃ ያጸናሉ።