1“አንተ ግን እንደ ባርያዬ እንደ ኢዮብ ማሳት የተሳነህን እኔ በክብር የአንተን ዙፋን አወርሳቸዋለሁ፤ አንተ ማሳት ለተሳነህ ሰዎች መንግሥተ ሰማያትን እሰጣቸዋለሁ ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር።” 2እኔም የአዳምን ልጆች በሁሉ እተነኰልባቸዋለሁ፤ እነርሱን ማሳት ከተቻለኝ በበጎ ሥራ ይጸኑ ዘንድ አልተዋቸውም፤ የአዳምን ልጆች ሁሉ እተነኰልባቸዋለሁና፥ የዓለምን ምኞትም አጣፍጥላቸዋለሁና። 3መብልን በመውደድ፥ መጠጥንም በመውደድ፥ ልብስን በመውደድም ቢሆን፥ ነገርንም በመውደድ፥ በመስጠትም በመንሣትም ቢሆን፥ 4መስማትንና ማየትንም በመውደድ ቢሆን፥ መዳሰስንና መሄድንም በመውደድ ቢሆን፥ ትዕቢትንና ነገርንም በማብዛት ቢሆን፥ እንቅልፍንና ሕልምንም በመውደድ ቢሆን፥ 5መጠጥንና ስካርን በማብዛት ቢሆን፥ ስድብንና ቍጣንም በማብዛት ቢሆን፥ ቡዋልትንና ቀልድን በመናገርም ቢሆን፥ 6ባልንጀራቸውንም በማማት በጠብ ቢሆን፥ መልከ መልካሞች የሆኑ የዚህን ዓለም ሴቶችን በማየትም ቢሆን፥ የሚያስትዋቸውን የሽቱዎችን መዓዛ በማሽተትም ቢሆን፥ 7መዳንን እንዳይችሉ በዚህ ሁሉ እኔ እጣላቸዋለሁ፤ በእነርሱም ምክንያት ከመንበሬ ወደ ተዋረድሁበት ጥፋት ከእኔ ጋራ ይገቡ ዘንድ ከእግዚአብሔር መንገድ አርቃቸዋለሁ። 8ነቢዩም እንዲህ አለ፥ “አንተ ጥፉና አጥፊ! በትዕቢትህና በልብህ ደንዳናነት፥ ፈጣሪህን በማሳዘንና ፈጣሪህንም ባላማመስገን አንተ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ወጥተህ በካድህ ጊዜ በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ እንዲህ ትታበያለህን? 9ፈጣሪህ በተቈጣህ ጊዜ ስለ ክፉ ሥራህ ጣለህ፤ ፈጣሪው ከመሬትና ከትቢያ የፈጠረውን፥ እንደ ወደደም የሠራውንና ለምስጋናው ያኖረውን ምስኪን ለምን ትወስደዋለህ? 10“ረቂቅ የምትሆን አንተ ከእሳት ነበልባልና ከነፋስ የፈጠረህን ፈጣሪ ነኝ በማለት በታበይህ ጊዜ፥ 11አንተም በተመካህ ጊዜ እግዚአብሔር ክፉ ሥራህን ተመለከተ፤ ሳያጓድል ስሙን ያመሰግን ዘንድ፥ በአንተ ፋንታ የሚያመሰግን አዳምን ፈጠረው፤ አንተ ከሠራዊቶችህ ጋራ እግዚአብሔርን ክደሃልና። 12አዳምና ልጆቹም እግዚአብሔር ስለ ትዕቢትህ በናቃችሁ በአንተና በሠራዊትህ ምስጋና ፋንታ የእግዚአብሔርን ስም ያመሰግኑ ዘንድ ተፈጠሩ፤ ከሊቃነ መላእክት ሁሉ ይልቅ ራስህን አኵርተሃልና። 13ስለዚህም እግዚአብሔር እንደ አንተ ከአሉ ከመላእክት አለቆች ሁሉ ለይቶ አዋረደህ፤ በአንድ ምክር የተፈጠራችሁ አንተና ሠራዊትህም ስለማይጠቅም ስለ ልቡናችሁ መደንደንና ስለ ሕሊናችሁ ትዕቢት ከእግዚአብሔር ምስጋና ወጥታችሁ ሳታችሁ፤ በሌላም ሳይሆን በፈጣሪያችሁ ላይ ታበያችሁ። 14ስለዚህም በትሑታን ይመሰገን ዘንድ አዳምን ከምድር አፈር ፈጠረው፤ ከበለስም ፍሬ እንዳይበላ ትእዛዝንና ሕግን ሰጠው። 15በፈጠረውም ሁሉ ላይ ሾመው፤ እንዲህም ብሎ አስታወቀው፤ “በገነት ውስጥ ከአለው ዛፍ ሁሉ ብላ፤ በራስህም ላይ ሞትን እንዳታመጣ የሞት እሾህ ከሆነችው ከአንዲት ዛፍ አትብላ፤” 16ይህቺንም ቃል በሰማሃት ጊዜ ከአዳም የጎን አጥንት በተገኘች በሔዋን ላይ የአፍህን መርዝ ተፋህ። 17እንደ አንተም ሕግ አፍራሽ ታደርገው ዘንድ በክፉ ሽንገላ ንጹሑን በግ ነጠቅኸው። 18እንደ የዋህ ርግብ ሆና የተፈጠረች ተንኰልህን የማታውቅ ሔዋንንም ባሳትሃት ጊዜ በተከናወነ ነገርህና በጠማማ ቃልህ አስካድሃት፤ ያችንም መጀመሪያዪቱን ፍጥረት ካሳትሃት በኋላ፥ እርሷ ሄዳ ከመሬት የተፈጠረ መጀመሪያውን የእግዚአብሔር ፍጥረት አዳምን አሳተችው። 19በትዕቢትህም ወደማይገባ ሁከት ጨመርኸው፤ የፈጣሪውንም ቃል እንዲክድ አደረግኸው፤ በትዕቢትህም ድሃውን አጠፋኸው። 20በተንኰልህም ከፈጣሪው ፍቅር አራቅኸው፤ በምክንያትህም ከደስታ ገነት አወጣኸው፤ በመሰናክልህም የገነትን መብል አስተውኸው። 21በሐሰትህም ከገነት መጠጥ አስጠማኸው፤ አንተ ፍዳ ወደምትቀበልባት ወደ ሲኦል ታወርደው ዘንድ ካለመኖር ወደ እውነተኛ መኖር ካመጣው አምላኩም ፍቅር ታወጣው ዘንድ የዋህ አዳምን ከጥንት ጀምሮ አንተ ተጣልተኸዋልና። 22መሬታዊም ሲሆን በነፍሱና በሥጋው፥ በልቡናውም ፈጣሪውን የሚያከብርና የሚያመሰግን መንፈሳዊና ተናጋሪ አደረገው። 23እንደ በገና በተለያዩ ብዙ ስልቶች የሚያመሰግኑ ዐሥር ሕሊናትን ፈጠረለት።