1ግፈኛና አሳች፥ የፈጣሪውንም መንገድ የሚፃረር ዲያብሎስን ስለሚበቀለው በኋላ ዘመን ስለሚመጣው ቸርና የዋህ የግብጽ ደሴቶች ደስ ይላቸዋል። 2እርሱም ይበቀለዋል፤ በልቡናውም ታብዮአልና ክብሩን ወደ መሬትና ወደ መዋረድ ይመልሳል። 3እርሱም እንዲህ አለ፥ “ከእኔ በላይ ማን ነው? ወደ ባሕሩ ጥልቅ እገባለሁና፥ ወደ ሰማይም እወጣለሁና፥ ጥልቆችንም አያለሁና፥ የአዳምንም ልጆች እንደ ወፍ ጫጩት ጨብጬ እይዛቸዋለሁና። 4ከቀናች ሕገ እግዚአብሔር አርቃቸው ዘንድ በእነርሱ ላይ ምክንያት ስለምፈጥር የእግዚአብሔርን ፈቃድ ባላደረጉ፥ በምድር ላይ በሚኖሩ ሰዎች እኔ እበረታታባቸዋለሁና ከእጄ የሚያስጥለኝ የለም። 5ከእኔ ጋራም ወደ ጥፋት እንዲሄዱ ጐጣጕጥ ወደ ሆነ ጎዳና እመልሳቸዋለሁ። 6“ስለዚህም እርሱን የወደዱት፥ ሕጉንም የጠበቁ ሰዎች እኔን ይጠላሉ፤ ከጌታቸው ተለይተው የሳቱ ሰዎች ግን ወደ እኔ ይመጣሉ፤ እኔንም ይወድዳሉ፤ ቃል ኪዳኔንም ይጠብቃሉ፤ ወደ ፈጣሪያቸው ወደ እግዚአብሔርም እንዳይመለሱ ልባቸውን አከፋለሁና፥ አሳባቸውንም አጠማለሁና እኔ እንዳዘዝኋቸው ትእዛዜን ያደርጋሉ። 7የዚህን ዓለም ገንዘብ ባሳየኋቸውም ጊዜ ከቀናች መንገድ ልቡናቸውን አስታለሁ፤ መልከ መልካም ሴቶችንና ቆነጃጅትንም ባሳየኋቸው ጊዜ በእነዚህ ከቀናች መንገድ አርቃቸዋለሁ። 8የሚያንፀባርቁ የሕንደኬ ዕንቆችን፥ ወርቅንና ብርን ባሳየኋቸው ጊዜ ወደ እኔ ሥራ ይመለሱ ዘንድ በዚህም ከቀናችው መንገድ አርቃቸዋለሁ። 9ቀጭን ልብስን፥ ነጭ ሐርንና ቀይ ሐርን፥ ግምጃንና የተልባ እግርን ባሳየኋቸው ጊዜ በዚህም ከቀናች መንገድ አርቃቸዋለሁ፤ ወደ እኔም አሳብ እመልሳቸዋለሁ፤ ገንዘብን፥ ከብቶችንም እንደ አሸዋ አብዝች ባሳየሁአቸው ጊዜ በዚህም ወደኔ ሥራ እመልሳቸዋለሁ። 10ስለ ሴቶች፥ ስለ ቍጣና ስለ ጠብ፥ የትዕቢት ቅናትን ባሳየኋቸው ጊዜ በዚህ ሁሉ ወደ እኔ መንገድ እመልሳቸዋለሁ። 11ምልክቶችንም ባሳየኋቸው ጊዜ በባልንጀሮቻቸው ልቡና አድራለሁ፤ በልቡናቸውም እየራሱ የሆነ የምልክት ነገርን አሳድራለሁ፤ የቃላቸውንም ምልክት አሳይች አስታቸዋለሁ። 12ማደሪያዬም ላደረግኋቸው ሰዎች ምልክትን አሳያቸዋለሁ፤ በከዋክብት አካሄድም ቢሆን፥ ወይም በደመና መውጣት፥ ወይም በእሳት ማናፋት፥ ወይም በአውሬዎችና በወፎች ጩኸት እነርሱ ማደሪያዎች ናቸውና በዚህ ሁሉ በልቡናቸው ምልክቶችን አሳድርባቸዋለሁ። 13እነርሱ ተናግረው ለባልንጀሮቻቸው ምልክት ይሰጧቸዋል፤ እኔም ቀድሜ እነዚያ ሟርተኞቻቸው እንደ ነገሯቸው ምልክት እሆናቸዋለሁ። 14“የመረመሯቸው ሰዎች ይስቱ ዘንድ፥ ዋጋንም ይሰጧቸው ዘንድ፥ እንደ ተናገሩት የሚደረግላቸው ትንቢትንም የሚያውቁ፥ ክፉና በጎንም የሚለዩ፥ ሁሉም እንደ ተናገሩ የሚሆንላቸው፥ እንደ ቃላቸውም የሚደረግላቸው እንደ እገሊትና እንደ እገሌ ዐዋቆች የሉም ብለው ለባልንጀሮቻቸው ይነግሯቸው ዘንድ የቃላቸውን ምልክት አደርግላቸዋለሁ። 15የሚጠፉ፥ በእኔም የሚስቱ ሰዎች ፈጽመው ይበዙ ዘንድ፥ የአዳምም ልጆች ከእኔ ጋር ይጠፉ ዘንድ ይህን በተናገሩ ጊዜ እኔ ደስ ይለኛል፤ ለበታች አልሰግድም በማለቴ እግዚአብሔር ስለ አባታቸው ስለ አዳም ከክብሬ አዋርዶኛልና። 16“እኔም በትእዛዜ የሚሄዱ ልጆቹን ሁሉ ወደ ጥፋት እወስዳቸዋለሁ” ያሳትኋቸው ሰዎች ከእኔ ጋራ በእሳት ውስጥ ይጨመሩ ዘንድ ከፈጠረኝ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን አለኝ። 17እኔም ቍጣውን በእኔ ላይ ባበዛ ጊዜ፥ አስረውም ወደ ገሃነምና ወደ ሲኦል ጥልቅ ይጥሉኝ ዘንድ ባዘዘ ጊዜ፥ ጌታዬን ማለድሁ፤ ፈጣሪዬም እንዲህ በአዘዘ ጊዜ ተቈጥተኸኛልና በመቅሠፍትህም ገሥጸኸኛልና፥ በመዓትህም ቀሥፈኸኛልና አቤቱ ጌታዬ በፊትህ አንዲት ነገር እናገር ዘንድ ፍቀድልኝ ብዬ በፊቱ ማለድሁ። 18ጌታዬም፦ ተናገር እሰማሃለሁ ብሎ መለሰለኝ፥ ያንጊዜም ወደ እርሱ እንዲህ እያልሁ እለምን ጀመርሁ። ከክብሬ ከተዋረድሁ በኋላ ያሳትኋቸው ሰዎች እኔ መከራ በምቀበልበት ከእኔ ጋር ይሁኑ። 19ነገር ግን እንቢ ያሉኝ፥ በእኔም ያልሳቱ፥ ትእዛዝህን ያደርጉ ዘንድ፥ ፈቃድህንም ይፈጽሙ ዘንድ፥ ቃልህንም ይጠብቁ ዘንድ፥ ትእዛዜን ያልጠበቁ፥ እኔም እንዳስተማርኋቸው እንቢ ባሉ ጊዜ፥ እኔም እንዳሳትኋቸው በእኔ ባልሳቱ ጊዜ እነርሱ ለመንግሥትህ ይሁኑ፤ ትወድደኝም በነበረ ጊዜ ለእኔ የሰጠኸኝን ዘውድ ይውሰዱ። 20ከእኔ ጋር ላልተሰደዱና ሰይጣናት ላልተባሉ ሥልጣናትም የእኔን ዘውድ ስጣቸው፤ ከእኔና ከሠራዊቶችም ባዶ በሆነች መንበሬ በቀኝህ አስቀምጣቸው። 21እንደ ወደድህም ያመስግኑህ፤ እንደ እኔና እንደ ሠራዊቶች ይሁኑ፤ እኔን ጠልተህ ከአመድና ከመሬት የተፈጠሩትን ስለ ወደድሃቸው፥ የእኔ ሥልጣን ተሽሮአልና፥ የእነርሱም ሥልጣን ከፍ ከፍ ብሏልና እንደ ወደድህ ያመስግኑህ።” 22ጌታዬም መልሶ እንዲህ አለኝ፥ “እያዩና እየሰሙ ሥራዬን ሳይወዱ አንተ አስተሃቸዋልና እንደ ፈቃድህና እንደ ቃልህ ይሁኑህ። 23ትእዛዜንና የመጻፎችን ቃል ትተው ወደ አንተ ከመጡ ጥፋታቸው አያሳዝነኝም፤ አንተም ከአሳትሃቸው ከአንተ ጋር በገሃነም ይቀጡ። 24እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ለአንተና በአንተ ለሳቱ ከገሃነም ቅጣት መውጫ የላችሁም። ነገር ግን ለዘለዓለም በእሳት ውስጥ ትሠቃያላችሁ።