1የምትሞቱበትን ቀን አስቡ፤ ነፍሳችሁ ከሥጋችሁ በምትለይበት ጊዜ፥ ገንዘባችሁንም ለሌላ በምትተዉበት ጊዜ፥ ወደማታውቁትም መንገድ በምትሄዱበት ጊዜ የምትመጣባችሁን አስቧት። 2የሚቀበሏችሁም ክፉዎች ናቸው፤ በመልካቸውም ጥፉዎች ናቸው፤ በግርማቸውም የሚያስፈሩ ናቸው፤ ቃላችሁን አይሰሙም፤ ቃላቸውንም አትሰሙም። 3የአምላካችሁን የእግዚአብሔርንም ፈቃድ ስለ አላደረጋችሁ በለመናችኋቸው ጊዜ አይመልሱላችሁም፤ ስለዚህም እጅግ ያስፈሯችኋል። 4አጋንንት ይፈሯቸዋልና የእግዚአብሔርን ፈቃድ በሚፈጽሙ ሰዎች ግን ፍርሀት የለባቸውም። በኃጥኣን ነፍሳትም አጋንንት ይዘባበቱባቸዋል። 5ይህን ዓለም ስለ ናቁት እጅግ ደስ ያሰኛቸዋልና የጻድቃን ሰዎች ነፍሳት በመላእክት ይባቤ ደስ ይላቸዋል፤ የኃጥኣን ነፍሳትን ግን ክፉዎች መላእክት ይቀበሏቸዋል። 6የጻድቃንን ነፍሳት ያረጋጓቸው ዘንድ ከእግዚአብሔር ይላካሉና፥ የጻድቃንንና የደጋጎች ነፍሳትን የምሕረት መላእክት ይቀበሉአቸዋል። የኃጥኣንን ነፍሳት ግን ክፉዎች አጋንንት ይቀበሏቸዋል፤ በኃጥኣን ነፍሳት ይዘባበቱባቸው ዘንድ ከዲያብሎስ ይላካሉና። 7ኃጥኣን ወዮላችሁ፤ የምትሞቱባት ቀን ሳትደርስባችሁ ለራሳችሁ አልቅሱ፤ ከሞታችሁ በኋላ ያለፈው ዘመናችሁ አይመለስም። 8ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር ፊት በደረሳችሁ ጊዜ ያለ መከራና ያለ ደዌ በደስታ ትኖሩ ዘንድ ዘመናችሁ ሳያልፍ በአላችሁበት ንስሓ ግቡ። 9ከእግዚአብሔር ወደሚያርቅ ከንቱ ፈቃድ እንዳይስባችሁ፥ በእናንተ ጽኑ ነቀፋና መቀማጠል፥ መብልንና ደስታንም መውደድ አይገኝባችሁ፤ ያለ ልክ የጠገበች ሰውነት የእግዚአብሔርን ስም አታስብምና የዲያብሎስ መንፈስ ያድርባታል እንጂ በእርስዋ የሕይወት መንፈስ አያድርባትም። 10ሙሴ፥ “ያዕቆብ በልቶ ጠገበ ወፈረም፥ ሰባ፥ ሰፋም፥ የፈጠረው እግዚአብሔርንም ተወው፤ 11ሕይወቱም ከእግዚአብሔር ራቀ” ብሎ እንደ ተናገረ፥ ያለ ልክ የሆድ ጥጋብ እንዳለሌ ፈረስ መሆን ነውና፥ ያለ ልክ መብላትና መጠጣት፥ ማመንዘርም እንደ ምድረ በዳ እሪያ መሆን ነውና። 12በልክ የሚበላ ግን በእግዚአብሔር መሠረት የጸና ይሆናል፤ እንደ አድማስም ድንጋይ፥ አጥርም እንዳለው ግንብ ይጸናል። “ኀጢአተኛ የሚያባርረው ሳይኖር ይሸሻል” ተብሎአልና። 13ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ተዘልሎ ይኖራል። 14እግዚአብሔርን የማይወዱ ሰዎች ግን ቃሉን አይጠብቁም፤ ልቡናቸውም የቀና አይደለም። 15እግዚአብሔርም በምድር ሳሉ እንዳያርፉ በመንቀጥቀጥና በፍርሀት፥ ገንዘባቸውንም በመንጠቅ፥ ቍጥርም በሌለው ብዙ መከራ ተይዘው ከጌቶቻቸው እጅ እጃቸውን በሰንሰለት ታስረው፥ 16ከመከራውም ያረፉ እንዳይሆኑ፥ አኗኗራቸውም በሰላም እንዳይሆን በተለያዩ የሚያስደነግጡ መከራዎች ሳሉ ኀዘንንና ድንጋጤን ያመጣባቸዋል።