1“ከዚህ በኋላ ወደ ጫጕላው በገባ ጊዜ ወድቆ ሞተ። 2ከዚህ በኋላም ፋናችንንና መብራታችንን አጠፋን፤ እናለቅስ ዘንድም ተቀመጥን፤ ያገሬ ሰዎችም ሁሉ ተነሥተው ይመክሩኝና ያረጋጉኝ ጀመሩ፤ ከዚህም በኋላ እስከ ማግሥትዋ ቀን ሌሊት ድረስ ዝም አልሁ። 3ከዚህ በኋላ ሁሉም ዝም ባሉ ጊዜ፥ እኔንም መምከር በተዉ ጊዜ እኔ ሌሊት ተነሥቼ ሸሸሁ፤ ወደዚህም ምድረ በዳ መጣሁ። 4ለዘለዓለሙ በዚሁ እኖራለሁ እንጂ እንግዲህ ወዲህ ወደ ሀገሬ እንዳልመለስ ቈረጥሁ፤ ሁልጊዜ እጾማለሁ፤ እስክሞትም ድረስ አለቅሳለሁ እንጂ እህል አልበላም፤ ውኃም አልጠጣም።” 5ያ የማስበው አሳቤም ተወኝ፤ እኔም መለስሁላት፤ እንዲህም አልኋት፦ 6“ከሴቶች ሁሉ አንቺ አላዋቂ ነሽ፤ ያገኘችንን የእኛን ልቅሶ አታዪምን? 7ስለ ሁላችን እናት ስለ ጽዮን ሁላችን በኀዘን አለን፤ መከራንም ፈጽመን ተቀበልን። 8አሁንም በእውነት ታዝኚና ታለቅሺ ዘንድ ይገባሻል፤ እኛ ሁላችንም ያዘንን ነንና፤ እኛም ስለ ብዙዎች እናዝናለን፤ አንቺ ግን ስለ አንዱ ልጅሽ ታዝኛለሽ። 9ምድርን ጠይቂአት፤ ትነግርሻለችም፤ በእርስዋ ላይ ይህን ያህል ስለ ተወለዱት ታለቅስ ዘንድ አግባብ ለእርስዋ ነው። 10ሁሉም ከጥንት ጀምሮ በእርስዋ ላይ ተፈጠሩ። እነሆም ሌሎች መጥተው ሁሉንም በሙሉ ፈጽሞ ለማጥፋት ወሰዷቸው። 11እንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ ያለቅስ ዘንድ የሚገባው ማን ነው? ይህን ያህል ብዙ የጠፋበት ነውን? ወይስ አንቺ ስለ አንድ ልጅሽ ታዝኛለሽን? 12ወይስ በጻዕርና በገዓር የወለድሁትን ልጄን አጥቻለሁና፤ የእኔ ልቅሶ እንደ ምድር ልቅሶ አይደለም ትያለሽን? 13ምድር ግን ብዙ አሕዛብ ወደ እርሷ እንደ መጡ እንደዚሁ ሄዱ። 14ነገር ግን እኔ እንዲሁ እልሻለሁ፤ አንቺ አምጠሽ እንደ ወለድሽ እንዲሁም ምድር ከጥንት ጀምሮ በእርሷ ለተፈጠሩ ሰዎች ፈጣሪዋ የሰጣትን ፍሬዋን ሰጠቻቸው። 15አሁንም ይህን ኀዘንሽን ካንቺ አርቂ፤ ስለ አገኘችሽ ቅጣትና መከራም ትዕግሥተኛ ሁኚ። 16እግዚአብሔርን ብታመሰግኚው ይረዳሻልና፥ ልጅሽንም በጊዜው ታገኚዋለሽና፥ በሴቶችም ዘንድ መከራን የታገሠች ትባያለሽና፥ 17አሁንም ወደ ሀገርሽ ግቢ፤ ወደ ባልሽም ሂጂ።” 18እርስዋም አለችኝ፥ “እንዲህስ አላደርግም፤ በዚህ እሞታለሁ እንጂ ወደ ሀገሬ አልገባም።” 19ዳግመኛም ተናገርኋት፤ እንዲህም አልኋት፦ 20“ይህን ነገር አታድርጊ፤ እሺ በዪኝ፤ ራስሽንም እንደ ጽዮን መከራ አድርጊ፤ ስለ ኢየሩሳሌምም ከተማ ተረጋጊ። 21ቤተ መቅደሳችን እንደ ፈረሰ፥ መሠዊያችን እንደ ተሰባበረ አታዪምን? 22ግናያቱ እንደ ጠፋ፥ ምስጋናችን እንደ ቀረ፥ ዘመራ ዘውዳችን እንደ ወደቀ፥ የመቅረዛችን መብራት እንደ ጠፋ፥ የቃል ኪዳናችን ታቦት እንደ ተማረከች፥ ንዋየ ቅድሳታችን እንዳደፈ፥ ስማችን እንደ ረከሰ፥ ጌቶቻችን እንደ ተዋረዱ፥ ካህኖቻችን እንደ ተቃጠሉ፥ ሌዋውያኖቻችን እንደ ተማረኩ፥ ደናግሎቻችን እንደ ተገደሉ፥ ሚስቶቻችንን እንደ ቀሙን፥ ጻድቃኖቻችን እንደ ተጐተቱ፥ ጐልማሶቻችን እንደ ተገዙ፥ ወንዶች ልጆቻችን እንደ ተቀሙ፥ አርበኞቻችን እንደ ደከሙ አታዪምን? 23ከዚህ ሁሉ የሚበልጥ ጽዮን ጠፋች፤ ክብርዋም ከእርስዋ ወጣ፤ በጠላቶቻችንም እጅ ወደቅን። 24አንቺም ተዪ፥ ልዑልና ኀያል ይቅር ይልሽ ዘንድ፥ ከድካምሽም እግዚአብሔር ፈጽሞ ያሳርፍሽ ዘንድ ይህን ብዙ ኀዘንሽን አርቂ።” 25ከዚህ በኋላ ይኽን ስናገራት ድንገት ፊትዋ ከፀሐይ ይልቅ በራ፤ መልኳም እንደ መብረቅ አንጸባረቀ፤ ወደ እርሷ መቅረብንም ፈራሁ፤ ልቡናዬም ደነገጠብኝ፤ ከዚህም በኋላ ይህ ምን እንደ ሆነ ሳስብ አስደነገጠችኝ። 26በታላቅ ድምፅም ጮኸች፤ ከድምፅዋም የተነሣ ምድር እስክትነዋወጥ ድረስ ድምፅዋ እጅግ የሚያስፈራ ሆነ። 27ባየኋትም ጊዜ እነሆ የከበረችና የታነጸች ከተማ ነበረች እንጂ ሴት አልነበረችም፤ ታላቅ የሆነ የመሠረቶችዋንም ቦታ አየሁ፤ ፈርቼም በታላቅ ድምፅ ጮህኹ። እንዲህም አልሁ፦ 28“አስቀድሞ ወደ እኔ የመጣህ መልአኩ ዑርኤል፥ አንተ ወዴት ነህ? ወደ ብዙ ምርምር እገባ ዘንድ፥ ፍጻሜዬም ለጕስቍልናዬ ትሆን ዘንድ፥ ጸሎቴም ለተግዳሮት ይሆን ዘንድ እንዲህ ለምን አደረግኸኝ?”
የራእዩ ትርጓሜ
29እኔ እንደዚህ ስናገር እነሆ፥ ቀድሞ ወድ እኔ የመጣው ያ መልአክ ወደ እኔ መጣ። 30እንደ ሬሳ ተኝቼ አገኘኝ፤ አእምሮዬም ከእኔ ጋር አልነበረም፤ ቀኝ እጄንም ይዞ አጸናኝ፤ በእግሮችም አቅንቶ አቆመኝ። 31መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “ምን ሆንህ? ምንስ ያስደነግጥሃል? ልብህስ ካንተ ጋር ስለምን የለም?” 32እኔም አልሁት፥ “አንተ ጥለኸኛልና፥ ተለይተኸኛልምና፥ እኔ እንደ ነገርኸኝ ወደዚህ ምድረ በዳ መጣሁ፤ ወደዚህም ምድረ በዳ በመጣሁ ጊዜ እነሆ፥ ማወቅ የማይቻለኝን አየሁ።” 33እርሱም አለኝ፥ “እንግዲህስ እነግርህ ዘንድ እንደ ሰው ቁም።” 34እኔም አቤቱ ተናገር አልሁት፥ “ድንገት እንዳልሞት እንግዲህ አትለየኝ እንጂ። 35ያላየሁትን አይቻለሁና፥ የማላውቀውንም ሰምቻለሁና። 36ነገር ግን ምናልባት ልቡናዬ ይዘነጋ ይሆንን? ሰውነቴስ ትጨነቅ ይሆንን? 37አሁንም አቤቱ በጅ በለኝ፤ የዚህንም ራእይ ትርጓሜ ለባሪያህ ንገረው።” 38እርሱም መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “ስለምትፈራው ነገር አስተምርህ ዘንድ ስማኝ። ይህ የተሰወረ ምሥጢር ስለሆነ፦ ልዑል እግዚአብሔር ገልጦልሃልና። 39ጽድቅህንም አየ፤ ስለ ወገኖችህ ብዙ ታዝናለህና፤ ስለ ጽዮንም እጅግ ትቈረቈራለህና። 40ነገሩ ይህ ነው፦ 41ቀድሞ እንደ አልቃሽ ሆና ያየሃት፥ ታረጋጋትም ዘንድ የጀመርህ ይች ሴት፥ 42አሁን አንተ እንዳየሃት ሴት አይደለችም። የታነጸች ከተማ እንጂ። 43ስለ ልጅዋ መከራ ነግራሃለችና። 44ያች ያየሃት ሴት ዛሬ እንደ ታነጸች ከተማ ሀገር ሁና የምታያት ጽዮን ናት። 45ሠላሳ ዘመን መካን ሆንኹ ያለችህም ይህ ነው፤ የሚያቀርቡት መሥዋዕት ሳይኖር ዓለም ሦስት ሺህ ዘመን ኖሯልና። 46ከሦስት ሺህ ዓመት በኋላም ሰሎሞን ከተማን ሠራ፤ ያንጊዜም ቍርባንን አቀረበ። ያችም መካን ሴት የወለደችው ልጅ፥ 47ይህም በብዙ ድካም አሳደግሁት ያለችህ ኢየሩሳሌም የኖረችው ዘመን ነው። 48ይህም ልጅዋ ወደ ጫጕላው በገባ ጊዜ ወድቆ ሞተ፤ ይህም መከራ አገኘን ያለችህ የኢየሩሳሌም ጥፋትዋ ነው። 49እነሆ ለልጆችዋ እንዴት እንደምታለቅስላቸው ያየሃት፥ አንተም ከመከራዋ ታረጋጋት ዘንድ የጀመርህ ያች ሴት ኢየሩሳሌም ናት። 50አሁንም ልዑል እግዚአብሔር ስለ እርስዋ በፍጹም ሰውነትህ እንድታዝን፥ በፍጹም ልቡናህም እንድትቈረቈር ባየ ጊዜ የደስታዋን ጌጥና የክብሩዋን መገለጥ አሳየህ። የተሰወረ ምሥጢር ነውና። 51ስለዚህ ነገር ቤት ባልተሠራበት በዚህ በምድረ በዳ ትኖር ዘንድ እነግርሃለሁ። 52ልዑል እግዚአብሔር ያሳይህ ዘንድ ያለውን ሁሉ አውቄአለሁና። 53ስለዚህም የግንብ መሠረት ወደሌለበት ወደዚህ ትመጣ ዘንድ እነግርሃለሁ። 54ልዑል ይገለጥበት ዘንድ ባለው ቦታ የሰው ሥራ ግንብ ሊኖር አይቻልምና። 55“አንተስ እንግዲህ አትፍራ፤ ልብህም አይደንግጥ፤ ገብተህ ብርሃንዋንና የግንብዋን ጽናት እይ እንጂ። 56መስማት የምትችለውን ያህል በጆሮህ ስማ። 57አንተ ከብዙዎች ይልቅ ራስህን ብፁዕ አሰኝተሃልና፥ በልዑልም ዘንድ እንደ ጥቂቶች ተጠርተሃልና። 58ዛሬም በዚህ እደር። 59ልዑል እግዚአብሔር በዓለም በሚኖሩ ሰዎች ላይ በጊዜው የሚያደርገውን ራእይ ነገ በሕልም ያሳይሃል።” 60በዚያችም ሌሊት፥ በማግሥቱም እንዳዘዘኝ አደርሁ።