በንስር አምሳል ያየው አምስተኛው ራእይ
1ከዚህም በኋላ በማግሥቱ ሌሊት ንስር ከባሕር ሲወጣ በሕልም አየሁ፤ ክንፎቹም ዐሥራ ሁለት ናቸው፤ ራሶቹም ሦስት ናቸው። 2በክንፎቹም በዓለሙ ሁሉ ይበርራል፤ የሰማይ ነፋሳትም ሁሉ ይነፍሱበታል፤ ደመናትም በእርሱ ይሰበሰባሉ። 3ከእነዚያም ክንፎች ራሶች ይበቅላሉ፤ እነዚያም ራሶች ደቃቅና ታናናሽ ክንፍ ይሆናሉ፤ 4ራሶቹም ዝም ይላሉ፤ ከእነዚያም ራሶች መካከለኛው ራስ ይበልጣል፤ ነገር ግን እርሱም ከእነርሱ ጋር ዝም ይላል። 5ያም ንስር ምድርንና በምድር የሚኖሩትን ይገዛ ዘንድ በክንፎቹ ይበርራል፤ 6ከሰማይ በታች ያለ ሁሉ ይገዛለት ዘንድ ያን ንስር በምድር ከተፈጠረው ፍጥረት የሚከራከረው ማንም የለም። 7ከዚህ በኋላ ያ ንስር ተነሣ፤ በጥፍሮቹም ቆመ፤ በታላቅ ድምፅም ጮኸ፤ ክንፎቹንም እንዲህ አላቸው፦ 8“በየቦታችሁ ተኙ እንጂ ሁላችሁ እያንዳንዳችሁ በአንድነት አትነሡ፤ በየጊዜውም ትነሣላችሁ። 9የኋለኛዪቱ ራሱም ከሁሉ ትበልጣለች።” 10ባየሁ ጊዜም ድምፁ የሚወጣ ከሥጋው መካከል እንጂ ከራሱ ውስጥ አይደለም። 11የእነዚያ ራሶች ቍጥሮችም ስምንት ናቸው። 12ከዚህ በኋላ በቀኝ በኩል ክንፍ ወጣ፤ ምድሩንም ሁሉ ገዛ። 13ከዚህ በኋላ ጥፋቱ በደረሰ ጊዜ ቦታው እስከማይታይ ድረስ እርሱም ጠፋ፤ ሁለተኛውም ወጣ፤ እርሱም ብዙ ዘመን አጽንቶ ገዛ። 14ከዚህም በኋላ ጥፋቱ በደረሰ ጊዜ እርሱም እንደ ፊተኛው ጠፋ። 15ቃልም መጣለት፤ እንዲህም አለው፦ 16“ምድርን ይህን ያህል ዘመን አጽንተህ የምትገዛ አንተ ንስር ሳትጠፋ ይኽን የምነግርህን ስማ። 17ከአንተ በኋላ እንደ አንተ የሚጸና፥ የእኩሌታህንም ያህል የሚገዛ የለም።” 18ሦስተኛውም ወጣ፤ እርሱም እንደ መጀመሪያው አጽንቶ ገዛ፤ ከዚህ በኋላ እርሱም ጠፋ። 19ከዚህም በኋላ ዳግመኛ ክንፎቹ ሁሉ ወጡ፤ እያንዳንዳቸውም ገዙ፤ ዳግመኛ ሁሉም ጠፉ። 20ከዚህ በኋላ ክንፎቹ አጽንተው ይገዙ ዘንድ በግራ በኩል በየጊዜያቸው ተነሡ፤ ነገር ግን ፈጥነው ጠፉ። 21ከእነርሱም ውስጥ የተነሡ አሉ፤ ነገር ግን እነርሱ አልገዙም። 22ከዚህ በኋላም እነዚያ ዐሥራ ሁለቱ ክንፎቹ ጠፉ፤ እኒያም ሁለቱ ራሶቹ ጠፉ። 23ዝም ከሚሉ ከሦስቱ ራሶቹና ከስድስቱ ራሶቹ በቀር ከዚህ ንስር ወገን የቀረ የለም። 24ከዚህም በኋላ ከእነዚያ ከስድስቱ ራሶች ሁለቱ ተለይተው ሄዱ፤ በቀኝ በኩል ባለ ራሱ ውስጥም ተቀመጡ፤ አራቱ ግን በቦታቸው ቀሩ። 25እኒህ አራቱ ራሶች ግን ይቆሙ ዘንድ፥ እነርሱም ይገዙ ዘንድ ተማከሩ። 26ከዚህም በኋላ አንዱ ተነሥቶ ቆመ፤ ነገር ግን ፈጥኖ ጠፋ። 27ሁለተኛውም እንዲሁ ከፊተኛው ይልቅ እርሱ ፈጥኖ ጠፋ። 28ከዚህ በኋላ የቀሩት እኒህ ሁለቱ ተተክተው ይገዙ ዘንድ እንዲሁ ተማከሩ። 29ከዚህም በኋላ እኒህ ሲማከሩ ዝም ከሚሉ ከሦስቱ ራሶች መካከለኛ የሚሆን አንዱ ተነሣ፤ ከእነርሱም የሚበልጥ እርሱ ነው። 30ከዚህም በኋላ እኒህን ሁለቱን ራሶች ከእርሱ ጋር ወሰዳቸው። 31ያም ራስ አብረውት ካሉት ጋራ ተመለሰ፤ ይገዙ ዘንድ የተማከሩ እኒህን ሁለቱንም ራሶች ዋጣቸው። 32ያም ራስ ምድርን ሁሉ ያዛት፤ በውስጥዋም የሚኖሩትን በብዙ ድካምና መከራ አሠቃያቸው፤ ከቆሙት ከእኒያ ክንፎች ሁሉ ይልቅ ፈጽሞ ዓለምን ቀማ። 33ከዚህም በኋላ መካከለኛው ራስ እንደ እነዚያ ጠፋ። 34ሁለቱ ራሶችም ቀሩ፤ እነርሱም እንዲሁ ምድርንና በውስጧ የሚኖሩትን ገዙ። 35ከዚህ በኋላ ያ በቀኝ በኩል ያለው ራስ በግራ በኩል ያለውን ዋጠው።
ከዱር የወጣ አንበሳ
36“ወደ ፊትህ ተመልከት፤ የምታየውንም ዕወቅ” የሚለኝን ቃል ሰማሁ። 37ባየሁም ጊዜ እነሆ አንበሳ እያገሣ ከዱር ተነሣ፤ እንደ ሰውም ድምፅ ሲናገር ሰማሁት፤ ያንም ንስር እንዲህ አለው፦ 38“የምነግርህንና ልዑል ያለህን አንተ ስማ። 39ምድርን ይገዟት ዘንድ ከፈጠርኋቸው፥ የዘመንም ፍጻሜ ከሚደርስባቸው ከእነዚያ ከአራቱ እንስሳ የቀረህ አንተ አይደለህምን?” 40አራተኛውም መጥቶ ያለፉትን በብዙ ድካምና ሕማም ይህን ዓለም የቀሙትን እነዚያን እንስሳ ሁሉ ድል ያደርጋቸዋል፤ ይህን ያህል ዘመን በዚህ ዓለም በተንኰል ኖረ። 41ዓለምንም በክፉ አገዛዝ ገዛት። 42ጻድቃንን ቀምቶአቸዋልና፥ ደጋጎቹንም በድሎአቸዋልና፥ ቅኖቹንም ጠልቶአቸዋልና፥ አሰተኞቹንም ወዶአቸዋልና፥ የጻድቃንንም አንባቸውን አፍርሶአልና፥ ያልበደሉትንም ቅጽራቸውን አፍርሶአልና። 43ኀጢአቱም ወደ ልዑል ደርሳለችና፥ ትዕቢቱም ወደ ኀያል ደርሳለችና። 44ልዑልም የራሱን ሰዎች ተመልክትዋቸዋልና፥ እነሆም ዓመቱ ተፈጽሞአልና። 45ስለዚህም አንተ ንስር ፈጽመህ ትጠፋለህ፤ ኀጢአተኞች ክንፎችህ፥ ዝንጉዎች ራሶችህ፥ ክፉዎች ጥፍሮችህና ዐመፀኛው ሥጋህ ይጠፋሉ። 46ምድርም ከመከራዋ ሁሉ እፎይ ብላ ካንተ ፈጽማ ታርፍ ዘንድ የፈጣሪዋን ፍርዱንና ቸርነቱን ተስፋ ታደርጋለች።