መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 11
1ከዚህም በኋላ ፈጣሪ ለዚያ ንስር ይህን ቃል በነገረው ጊዜ፥ 2የቀረው ያ ራስ ጠፋ፤ወደ እርሱ የመጡ እነዚያም ክንፎች ተነሡ፤ እነርሱም ይገዙ ዘንድ ተነሡ፤ በጥፍራቸውም ይታወኩ ነበር። 3ከዚህ በኋላ እነርሱም ጠፉ፤ ሥጋቸውም ሁሉ ተቃጠለ፤ ምድርም ፈጽማ ደነገጠች። እኔም ከብዙ ምርምር የተነሣ ደነገጥሁ፤ በጽኑ ፍርሀትም ነቃሁ። 4ልቡናዬንም እንዲህ አልኋት፥ “የልዑልን ሥራ ስትመረምሪ አንቺ ይህን ሁሉ አደረግሽኝ። 5ሰውነቴም ደከመች፤ ልቡናዬም እጅግ ተጨነቀች፤ በብዙ ፍርሀት ተይዤ ምንም ኀይል የለኝም፤ በዚችም ሌሊት ደነገጥሁ። 6አሁንም ለዘለዓለሙ ያጸናኝ ዘንድ ወደ ልዑል እጸልያለሁ።” 7እንዲህም አልሁ፥ “አቤቱ ጌታዬ በዐይኖችህ ፊት ባለሟልነትን ካገኘሁ፥ በአንተም ዘንድ ራሴን ብፁዕ ካሰኘሁ፥ ጸሎቴም በፊትህ ከደረሰች፥ 8አድነኝ፤ አጽናኝም፤ ነፍሴም ፈጽማ ደስ ይላት ዘንድ የሚያስፈራ የዚህን ሕልም ትርጓሜ ለባሪያህ ንገረው። 9በኋላ ዘመን የሚደረገውንና የዓለሙን ኅልፈት ያሳየኸኝ አንተ ብፁዕ አድርገኸኛልና።”
የራእዩ ትርጓሜ
10መልአኩም እንዲህ አለኝ፥ “ያየኸው የዚህ ሕልምህ ትርጓሜ እንዲህ ነው። 11ከባሕር ሲወጣ ያየኸው ይህ ንስር ለወንድምህ ለዳንኤል በሕልም የታየችው አራተኛዋ መንግሥት ናት። 12ነገር ግን ዛሬ ለአንተ እኔ እንደተረጐምሁልህ ለእርሱ አልተረጐምሁለትም። 13እነሆ፥ ዘመን ይመጣል፤ በምድርም ከእርስዋ አስቀድሞ ከነበሩት መንግሥታት ይልቅ የምታስፈራ መንግሥት ትነሣለች። 14በእርሷም ዐሥራ ሁለት ነገሥታት በተከታታይ ይነግሣሉ። 15ቀጥሎ የሚነግሠውም በዘመኑ ከዐሥራ ሁለቱ ነገሥታት ፈጽሞ የሚጸና ነው። 16ያየሃቸው የእኒህ የዐሥራ ሁለቱ ክንፎች ትርጓሜ ይህ ነው። 17ቃልን ሲናገር ያየኸው ይህም ከሥጋው መካከል ነው እንጂ ከራሱ የሚወጣ ሁለተኛው አይደለም። 18ትርጓሜውም እንዲህ ነው፤ ከዚያ መንግሥት ወገን መካከል ብዙ ሁከት ይፈጠራል፤ መንግሥትም ለመውደቅ ትንገዳገዳለች፤ ነገር ግን ጸንታ ትኖራለች እንጂ ያንጊዜ አትወድቅም። 19ከክንፎቹም ራሶች ሲወጡ ያየኸው ይህ፥ 20ትርጓሜው እንደዚህ ነው፤ ስምንቱ ነገሥታት በእርስዋ ይነግሣሉ፤ ዘመናቸውም የከፋ፥ ወራታቸውም ያጠረ ይሆናል፤ ከእነርሱ ሁለቱ ግን በዘመናቸው መካከል ፈጥነው ይጠፋሉ። 21ነገር ግን አራቱ መንግሥታት የሚጠፉበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ይጠበቃሉ፤ ሁለቱም ለብዙ ዘመን ይጠበቃሉ። 22“ዝም ብለው ያየሃቸው እነዚህ ሦስቱ ራሶችም፦ 23ትርጓሜው እንዲህ ነው፤ ልዑል በኋላ ዘመን ሦስት ነገሥታትን ያስነሣል፤ በውስጧም ብዙውን ያድሳሉ፤ ምድርንም ያሠቃዩአታል። 24በውስጧ የሚኖሩትንም ከእነርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ እጅግ ያሠቃዩአቸዋል። ስለዚህም የንስሩ ራሶች ተባሉ። 25እነርሱ የመንግሥት መጀመሪያዎች፥ የመንግሥትም መጨረሻዎች ናቸውና። 26ይህም ሲጠፋ ያየኸው አንዱ ታላቅ ራስ በታላቅ ጻእር ተጨንቆ በመኝታው የሚሞት ከእነርሱ አንዱ ነው። 27የቀሩት እነዚያ ሁለቱ ግን በጦር ይሞታሉ። 28አንዱ ኋለኛውም በጦር ይሞታል። 29“በቀኝ በኩል ወደ አለው ራሱ የሄዱት እነዚያ ያየሃቸው ሁለት ራሶችም፥ 30ትርጓሜው ይህ ነው፤ ልዑል በኋላ ዘመን የጠበቃቸው፥ መጀመሪያው ጥፋት የሚደረግባቸው ናቸው፤ አንተ እንዳየኸውም ብዙ ጸብ ይደረጋል። 31ከዱር እያገሣ ሲወጣ ያንም ንስር በሰማኸው ሁሉ ነገር ሲናገረውና በኀጢአቱ ሁሉ ሲዘልፈው ያየኸው ይህ አንበሳም፥ 32ልዑል ለኋላ ዘመን የጠበቀው፥ ከዳዊትም ወገን የሚወለደው ነው፤ መጥቶም ኀጢአታቸውን ይነግራቸዋል፤ ስለበደላቸውም ይዘልፋቸዋል፤ በፊታቸውም ፍዳቸውን ይገልጥባቸዋል። 33በሕይወት ሳሉም አስቀድሞ በፍርድ ያቆማቸዋል፤ ከዘለፋቸውም በኋላ ያንጊዜ ያጠፋቸዋል። 34ትሩፋኑን ግን በቸርነቱ በከበረ አውራጃ ይቤዣቸዋል፤ አስቀድሜም የነገርሁህ የፍርድ ቀን እስኪደርስ ድረስ ደስ ያሰኛቸዋል። 35ያየኸው ሕልምህ ይህ ነው፤ ትርጓሜውም እንደዚህ ነው። 36ልዑል ይህን ምሥጢር አንተ ብቻ እንድታውቀው አደረገልህ። 37ነገር ግን ይህን ያየኸውን ሁሉ ጻፈው፤ በተሰወረ ቦታም አኑረው። 38ይህንም ምሥጢር በልቡናቸው ለመጠበቅ እንዲቻላቸው አንተ ለምታውቃቸው ለጠቢባን አስተምራቸው። 39አንተ ግን ልዑል ሊያሳይህ የሚወድደውን ታይ ዘንድ ዳግመኛ ሰባት ቀን በዚህ ተቀመጥ።”
ሕዝቡ ወደ ዕዝራ እንደ ተሰበሰቡ
40ከዚህም በኋላ ከእኔ ተለይቶ ሄደ፤ እኒያ ሰባት ቀኖች እንዳለፉ፥ እኔም ወደ ከተማ እንዳልገባሁ ሰዎች ሁሉ በሰሙ ጊዜ፥ ሕዝቡ ሁሉ ትንሹም ትልቁም ተሰብስበው ወደ እኔ መጡ፤ እንዲህም አሉኝ፦ 41“እኛን ትተኸን በዚህ ምድረ በዳ ትኖር ዘንድ ምን በደልንህ? ምንስ ግፍ ሠራንብህ? 42ከሚለቅሙት ፍሬ ሁሉ እንደ አንድ ፍሬ፥ በጨለማ ቦታ ውስጥም እንደ አለ መብራት፥ ከጥልቅም እንደሚያድን የመርከብ ወደብ ከነቢያት ሁሉ አንድ አንተ ብቻ ቀርተህልናልና። 43ወይስ ያገኘችን መከራ አልበቃችንምን? 44አንተስ የምትለየን ከሆነ ጽዮን በተቃጠለች ጊዜ ብንኖር በተሻለን ነበር፤ 45በዚያ ከሞቱት ሰዎች እኛ የምንሻል አይደለንምና።” በታላቅ ድምፅም አለቀሱ። 46እኔም መለስሁላቸው፤ እንዲህም አልሁአቸው፥ “የያዕቆብ ልጆች እመኑ፤ የእስራኤልም ወገኖች አትዘኑ። 47መታሰቢያችን በልዑል ፊት አለና፥ የማይዘነጋን እርሱም ጽኑዕ ነውና። 48እኔስ አልተዋችሁም፤ ከእናንተም አልርቅም፤ ነገር ግን ወደዚህ ቦታ የመጣሁት ስለ ጽዮን ጥፋት እለምን ዘንድ ነው፤ በደስታችን ላይ ስለ መጣብንም መከራ ይቅርታን እለምን ዘንድ ነው። 49አሁንም ሁላችሁ ወደየቤታችሁ ግቡ፤ እኔም ወደ እናንተ እመጣለሁ።” 50ከእነዚያም ወራቶች በኋላ ሕዝቡ እንዳዘዝኋቸው ወደ ከተማ ወደየቤታቸው ገቡ። 51እኔ ግን መልአኩ እንዳዘዘኝ በዚያ ቦታ በምድረ በዳው ውስጥ ሰባት ቀን ተቀመጥሁ፤ ከምድረ በዳ ፍሬ ብቻም ተመገብሁ፤ በእነዚያም በሰባቱ ቀኖች ከምድረ በዳው ቅጠል በላሁ።