ስድስተኛ ራእይ
1ከዚህም ከሰባተኛው ቀን በኋላ በሌሊት ሕልምን አየሁ። 2እነሆ፥ ጽኑ ነፋስ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ ማዕበሎቹም ሁሉ ታወኩ። 3ያም ነፋስ በሰው አምሳል ከባሕሩ ሲወጣ አየሁ፤ ከዚህ በኋላ ያ ሰው ከሰማይ ደመናዎች ጋር ወጣ፤ ፊቱንም መልሶ ባየ ጊዜ፥ ሁሉ በጊዜው ጊዜ ወደ እርሱ ይመጣል። 4ቃሉም በወጣ ጊዜ ከቃሉ የተነሣ ሁሉ ይቀልጣል፤ ቃሉን የሰሙት ሁሉም አደሮ ማር ወደ እሳት በቀረበ ጊዜ እንደሚቀልጥ ይቀልጣሉ። 5ከዚህ በኋላ ቍጥር የሌላቸው ብዙ ሰዎች ከባሕር የወጣ ይኽን ሰው ይዋጉት ዘንድ ከአራቱ ማዕዘን ሲሰበሰቡ አየሁ። 6ከዚህ በኋላም ታላቅ ተራራን ሠራ፤ በላዩም ተቀመጠ። 7ያ ተራራም የተሠራበትን ላውቅ ወደድሁ፤ ነገር ግን አልቻልሁም። 8ከዚህም በኋላ ይጣሉት ዘንድ የተሰበሰቡት ሁሉ ፈጽመው ፈሩት። ነገር ግን ይዋጉት ዘንድ ደፈሩ። 9ከዚህም በኋላ በከበቡት ጊዜ፥ ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እጁን በእነርሱ ላይ አላነሣም፤ ጦርን ወይም ማናቸውንም የጦር መሣሪያ አላነሣም። 10ከአፉ የእሳት ማዕበልን፥ ከከንፈሩም የእሳት ነበልባልን፥ ከአንደበቱም የእሳት ፍምን እንደ ጥቅል ነፋስ አወጣ እንጂ፤ ያ የእሳት ማዕበል፥ ያም የእሳት ነበልባል፥ ያም የእሳት ፍም ሁሉ ተቀላቅሎ እንደ ጥቅል ነፋስ ሆነ። 11ሊገድሉት በከበቡት በእነዚያ በብዙዎች ላይም ወረደ፤ ከዐመዳቸው ትቢያና ከቃጠሏቸው ጢስ በቀር ከእነርሱ የተረፈ እስከማይኖር ድረስ ሁሉንም አቃጠላቸው። ከዚህም በኋላ ደንግጬ ነቃሁ። 12ከዚህም በኋላ ያን ሰው ከዚሁ ተራራ ሲወርድ አየሁት፤ ለእርሱ የሚስማሙ ብዙዎች ሌሎችንም ወደ እርሱ ጠራ። 13ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጡ፤ ከእነርሱም ደስ ያላቸው ነበሩ፤ ከእነርሱም ያዘኑ ነበሩ፤ ከእነርሱም እስረኞች ነበሩ። ከዚህ በኋላ ይህ ሁሉ በደረሰብኝ ጊዜ ደንግጬ ነቃሁ፤ ወደ ልዑልም ጸለይሁ። 14እንዲህም አልሁ፥ “ቀድሞ አንተ ይህን ጌትነትህን ለባሪያህ አሳየኸው፤ ጸሎቴንም ትሰማ ዘንድ አደረግህልኝ። 15አሁንም የዚህን የሕልሜን ትርጓሜ ዳግመኛ ንገረኝ። 16ነገር ግን እኔስ እንደምጠራጠረው በእነዚያ ወራቶች ለሚኖሩ ሰዎች ወዮላቸው! ይልቁንም ላልነበሩት ወዮላቸው! 17በኋላ ዘመን የሚቈያቸውን ገና ያልደረሰላቸውን ባለማወቅ ያዝናሉና። 18ላሉት ግን ፈጽመው ስላወቁት ነው። 19ስለዚህም ወዮላቸው! በዚህ ሕልም እንዳየሁ ታላቅ ጭንቅንና ብዙ ድካምን ያያሉና። 20ነገር ግን ይህ ሳይደርስ መከራ መቀበል ይሻላል፤ እንደ ደመናም ከዚህ ዓለም ያልፉ ዘንድ ይሻላል፤ በኋላ ዘመን የምታገኛቸውን አያውቁምና።”
የራእዩ ትርጓሜ
21እርሱም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “የዚህን የሕልምህን ትርጓሜ እነግርሃለሁ፤ ይህን ያልኸኝንም እተረጕምልሃለሁ። 22ስለሚቀሩትና ስለሚኖሩት ተናግረሃልና ትርጓሜው እንዲህ ነው። 23በእነዚያ ወራቶች ያን መከራ የሚያዩት እነዚያ የሚቀሩት ናቸው፤ ያም መከራ የሚያገኛቸውንና በልዑል ዘንድ ሃይማኖትና በጎ ምግባር፥ ጽናትም ያላቸውን እርሱ ራሱ ይጠብቃቸዋል። 24ነገር ግን ከሞቱት ይልቅ በሕይወት የቀሩት ፈጽመው ብፁዓን እንደ ሆኑ ዕወቅ። 25የዚህስ የሕልምህ ትርጓሜው እንደዚህ ነው፤ ከባሕር ሲወጣ ያየኸው ይህ ሰው፥ 26ዓለሙን ሁሉ በእርሱ ያድን ዘንድ ለኋላ ዘመን ልዑል የጠበቀው ይህ ነው። እርሱም የተረፉትን በሥርዐት ያኖራቸዋል። 27እንደ ጥቅል ነፋስ ከአፉ የእሳት ነበልባል፥ የእሳትም ፍሕም ሲወጣ ያየኸው፥ 28ጦሩን ወይም የጦር መሣሪያውን ያላነሣ፥ ግን የከበቡትንና ሊገድሉት የመጡትን እነዚያን ብዙዎችን ያጠፋቸው ትርጓሜው እንዲህ ነው። 29በምድር የሚኖሩትን ልዑል የሚያድንበት ዘመን ይመጣል። 30ያንጊዜ እርስ በእርሳቸው ይወነጃጀላሉ። 31ከተማ ከከተማ ጋር፥ ገጠር ከገጠር ጋር፥ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር፥ መንግሥታት ከመንግሥታት ጋር ይዋጋሉ። 32ይህም በተደረገ ጊዜ፥ ቀድሞ ያሳየሁህ ምልክቱም በደረሰ ጊዜ ያንጊዜ ከባሕር ሲወጣ ያየኸው ያ ሰው ይገለጣል። 33“አሕዛብም ሁሉ ቃሉን በሰሙ ጊዜ ሀገሮቻቸውና እርስ በርሳቸው የሚጣሉበትን ጠባቸውን ይተዋሉ። 34ቍጥር የሌላቸው ሰዎች እንዳየሃቸው መጥተው ሊገድሉት ወድደው በአንድነት በዝተው ይሰበሰባሉ። 35እርሱ ግን በጽዮን ተራራ ራስ ይቆማል። 36ያለ ሰው እጅ የተፈጠረው ተራራ ሲወጣ እንዳየኸው፥ ጽዮን ትመጣለች፤ ተዘጋጅታና ተሠርታም ለሁሉ ትታያለች፤ 37እንደ ዓውሎ ነፋስ የሆኑ አሕዛብን በኀጢአታቸው የሚዘልፋቸው እርሱ ወልድ ነው። የሥራቸውንም ክፋት በፊታቸው ይገልጥባቸዋል። እንደ እሳት ነበልባል የሆኑትም በጽኑዕ የሚሠቃዩበትን ይገልጣል። 38እንደ እሳት ፍም የሆኑትንም ያለ ድካም ከኀጢአታቸው ጋር ያጠፋቸዋል። 39“ለእርሱ የሚስማሙ ብዙዎች ወደ እርሱ ሲሰበሰቡ ያየኸውም፥ 40እኒህ በአሦር ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን ካገራቸው የተማረኩ፥ እርሱም በመንግሥቱ የማረካቸው፥ በወንዙ ማዶም ያኖራቸው ዘጠኙ ነገድና የነገድ እኩሌታ ናቸው፤ ተመልሰውም ሌላ ሆኑ። 41የወገናቸውን ነገድ ይተዉ ዘንድ፥ የሰው ወገን ወደማይኖርበት ሀገርም ይሄዱ ዘንድ እነርሱ ራሳቸው ይህችን ምክር አወጧት። 42በሀገራቸው ያልጠበቁትን ሕግ ይጠብቁ ዘንድ፥ 43መግቢያው ጠባብ ወደ ሆነ ወደ ኤፍራጥስም ገቡ። 44ያንጊዜም ልዑል ተአምር አደረገላቸው፤ የወንዙንም ምንጭ እስኪያልፉ ድረስ አቆመላቸው። 45ሀገሩ ግን ዓመት ከመንፈቅ ያስሄዳል፤ የሀገሩም ስም አዛፍ ይባላል። 46“እስከ ኋለኛውም ዘመን ድረስ በዚህ ኖሩ፤ ከዚህም በኋላ ዳግመኛ ይመለሱ ዘንድ ባላቸው ጊዜ፦ 47መሻገር ይችሉ ዘንድ የወንዙን ምንጭ ልዑል ዳግመኛ ያቆምላቸዋል። 48ስለዚህም ስለ አየኸው ነገር ከሕዝቡ አብዛኛዎቹን ይወስዷቸዋል። እነርሱም በከበረው ቦታዬ ይገኛሉ። 49በእርሱ ላይ የተሰበሰቡ እነዚያን ብዙዎችንም ባጠፋቸው ጊዜ ያንጊዜ የቀሩትን ሕዝብ ያጸናቸዋል። 50ያንጊዜም ብዙ ምልክቱን ያሳያቸዋል።” 51እኔም እንዲህ አልሁት፥ “አቤቱ ጌታዬ፥ ይህንም ንገረኝ፤ ከባሕር መካከል ሰው ሲወጣ እኔ ያየሁት ስለ ምንድን ነው?” 52እንዲህም አለኝ፦ በባሕሩ ጥልቀት ውስጥ ያለውን ማንም ማወቅ እንደማይችል እንደዚሁም በምድር ካሉት ወልድን ማወቅ የሚችል ማንም የለም፤ ሰዓቱና ቀኑ በደረሰ ጊዜ ነው እንጂ፤ ከእርሱም ጋር ያሉት አያውቁትም። 53ያየኸው የሕልምህ ትርጓሜው ይህ ነው፤ ስለዚህም ለአንተ ብቻ አሳየሁህ። 54ግዳጅህን ትተህ የእኔን ግዳጅ ተከትለሃልና ሕጌንም ፈልገሃልና። 55ሕይወትህንም ለዕውቀት አዘጋጅተሃልና፤ ጥበብንም እናት አድርገሃታልና። 56ስለዚህም ይህን ገለጥሁልህ፤ ዋጋህ በልዑል ዘንድ አለና፥ እንግዲህስ ወዲህ ከጥቂት ቀን በኋላ ና፤ የምነግርህ ሌላ ነገር አለና፥ ድንቅንም እተረጕምልሃለሁና።” 57በየጊዜው ስለሚያደርገው ስለ ድንቅ ሥራውም እግዚአብሔርን አመሰግነውና አከብረው ዘንድ ወደ ምድረ በዳ አልፌ ሄድሁ። 58ዘመኖቹን ያዘጋጃቸዋልና፥ ይህንም በየዓመቱ ያደርጋልና። በዚያም ሦስት ቀን ተቀመጥሁ።