ሰባተኛው ራእይ
1በሦስተኛውም ቀን በዛፍ ሥር ተቀምጬ ሳለሁ፦ 2ከዚያች ዛፍ ፊት ለፊት ቃል መጣ፤ “ዕዝራ! ዕዝራ!” ብሎ ጠራኝ፤ እኔም፥ “እነሆኝ ጌታ ሆይ፥” አልሁ፤ ተነሥቼም ቆምሁ፤ 3እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “ለሙሴ ፈጽሜ ታየሁት፤ ወገኖችም ለግብፅ በተገዙ ጊዜ ጳጦስ በሚባል እንጨት ሥር ተናገርሁት። 4ላክሁትም፤ ወገኖችንም ከግብፅ አወጣኋቸው፤ ሙሴንም ወደ ደብረ ሲና ወሰድሁት፤ ብዙ ቀንም በእኔ ዘንድ አኖርሁት። 5ብዙ ድንቅን ነገርሁት፤ የዘመናትንም ምሥጢር አሳየሁት፤ ኋለኛውንም ዘመን ነገርሁት። 6ይህን ነገር ተናገር፤ ይህንም ነገር ሰውር ብዬ አዘዝሁት። 7አሁንም ለአንተ እልሃለሁ፦ 8የነገርሁህን ያን ነገር ታውቅ ዘንድ፥ ያየኸው ሕልምህንም፥ የሰማኸውን ትርጓሜውንም በልቡናህ ጠብቀው። 9ከሰው ለይተው ይወስዱሃልና፥ ከዚህም በኋላ ዓለም እስኪያልፍ ድረስ እንዳንተ ያሉት ባሉበት ቦታ ከልጆች ጋር ትኖራለህ። 10የዓለም የጐልማሳነቱ ወራት አልፏልና፥ ዘመኑም አርጅትዋልና። 11ዓለም ለዐሥር ክፍል ተከፍሏልና እስከ ዐሥርም ድረስ ደርሷልና። 12የዐሥረኛው እኩሌታ ቀርትዋልና። 13አሁን ግን ቤትህን አዘጋጅ፤ አዘንተኞቻቸውንም ደስ አሰኛቸው፤ ዐዋቆቻቸውንም ልብ አስደርጋቸው፤ እንግዲህ የምታልፍ ሕይወትንም ተዋት። 14መዋቲ አሳብን እንግዲህ ተወው፤ የሰው ሸክምንም ከላይህ ጣል፤ የሚሞት አሳብንም ተው፤ የማይሞተውንም ልበስ፤ እንግዲህም ወዲህ ከዚህ ዓለም ትሸጋገር ዘንድ አፍጥን። 15ይች ያየሃት ክፋት ዛሬ ደርሳለችና፤ እንግዲህ ወዲህ ከእርሷ የምትከፋ ዳግመኛ ትደረጋለችና። 16ዓለም እያረጀና እየደከመ በሚሄድ መጠን እንዲሁ በውስጡ የሚኖሩ ክፋታቸው ትበዛለችና። 17እውነት ትጠፋለችና፥ አሰትም ትጸናለችና። ይህ ያየኸውም ንስር ይደርስ ዘንድ ይቸኵላልና።” 18እኔም መለስሁለት፤ እንዲህም አልሁት፥ “እንግዲህስ ወዲህ በፊትህ እናገራለሁ። 19አቤቱ፥ እኔ እሄዳለሁና፥ እንደ አዘዝኸኝም ዛሬ ያሉትን ሕዝብ አስተምራቸዋለሁና። እንግዲህ ወዲህ ዳግመኛ የሚወለዱትን ማን ያስተምራቸዋል? 20ዓለም በጨለማ ውስጥ አለና፤ በውስጡ ለሚኖሩትም ብርሃን የላቸውም። 21ኦሪትህ ተቃጥላለችና፥ የሠራኸውን፥ ትሠራውም ዘንድ ያለህን የሚያውቀው የለምና። 22በፊትህስ ባለሟልነትን ካገኘሁ፥ ቅዱስ መንፈስህን ላክልኝ፤ እኔም ሰው የሕይወት መንገድን ማግኘት ይችል ዘንድ፥ ሊኖሩ የሚወድዱ ሰዎችም ይድኑ ዘንድ ከጥንት ጀምሮ በዓለም የሆነውን ሁሉና በኦሪትህ ውስጥ ተጽፎ ያለውን እጽፋለሁ።” 23እርሱም መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “ሄደህ ወገኖችህን ሰብስባቸው፤ እስከ አርባ ቀንም ድረስ እንዳይፈልጉህ ንገራቸው። 24አንተ ግን ብዙ ብራና አዘጋጅ፥ ከአንተም ጋራ ሶርያን፥ ደርብያን፥ ሰላምያን፥ ኢቀናንንና አሳሄልን እኒህን አምስቱን ሰዎች ውሰዳቸው። እነርሱ በመጻፍ ጠቢባን ናቸውና። 25ወደዚህ ና፤ በልቡናህም የጥበብ መብራትን አበራለሁ፤ ትጽፍም ዘንድ ያለህን ሁሉ እስክትጨርስ ድረስ እንግዲህ አትጠፋም። 26በጨረስህ ጊዜ ግልጥ የምታደርገው አለ፤ የምትሠውረውም አለ፤ ለዐዋቂዎችም፥ ለጠቢባንም ትሰጣቸዋለህ፤ ነገ በዚህ ሰዓት ትጽፍ ዘንድ ትጀምራለህ።” 27እንደ አዘዘኝም ሄጄ ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰብሁ። 28እንዲህም አልኋቸው፥ “እስራኤል፥ ይህን ነገር ስሙ። 29አባቶቻችሁ ቀድሞ በግብጽ ምድር ኖሩ፤ ከዚያም ተቤዣቸው። 30የሕይወት ሕግንም ተቀበሉ፤ ግን አልጠበቁም፤ ከእነርሱም በኋላ ያላችሁት እናንተ ካዳችሁት። 31ምድረ ርስትን ሰጠን፤ የጽዮንንም ምድር አወረሰን፤ እናንተም፥ አባቶቻችሁም ካዳችሁት፤ እርሱንም መበደል አልተዋችሁም፤ የአዘዛችሁ የልዑል መንገድን አልጠበቃችሁም። 32እርሱ እውነት ፈራጅ ነውና በጊዜው የሰጣችሁን ቀማችሁ። 33አሁንም እናንተ በዚህ አላችሁ፤ ወንድሞቻችሁ ግን ከእናንተ ተለይተው በውስጥ ናቸው። 34ልቡናችሁን ያስገዛችሁት፥ ሕሊናችሁንም የገሠጻችሁት እንደ ሆነ፥ ሕይወታችሁንም የጠበቃችሁት እንደ ሆነ አትሞቱም። 35ከሞት በኋላ ፍርድ ይመጣልና፥ እኛንም በሕይወት አያኖረንምና፥ ያንጊዜም የጻድቃን ስማቸው ይገለጣል፤ የኃጥኣንም ሥራቸው ይገለጣል። 36ከእናንተ ወደ እኔ የሚመጣ አይኑር፤ እስከ አርባ ቀንም ድረስ አትፈልጉኝ።” 37እንዳዘዘኝም እነዚያን አምስቱን ሰዎች ይዤ ወደ ምድረ በዳው ሄድን፤ በዚያም ተቀመጥን። 38በማግሥቱም ቃል መጣ፥ “ዕዝራ! ዕዝራ!” ብሎ ጠርቶ እንዲህ አለኝ፥ “አፍህን ክፈት እኔም የማጠጣህን ጠጣ።” 39አፌንም በከፈትሁ ጊዜ ውኃ የተመላ፥ መልኩ እሳት የሚመስል መጠጥን አጠጣኝ። 40ተቀብዬም ጠጣሁት፤ ልቡናዬም ፈጽሞ ዕውቀትን ተናገረ፤ ዕውቀትም በልቡናዬ በዛ፤ ነፍሴም ትጠብቀዋለች፤ ታስበዋለችም። 41አፌም ተከፈተ፤ ከዚያም ወዲያ ዝም አላለም። 42ልዑልም ለእነዚያ ለአምስቱ ሰዎች ጥበብን ሰጣቸው፤ የማያውቁትንም ምልክት የሆነውን ይህን ሁሉ በማከታተል ጻፉ፤ በዚያም አርባ ቀን ተቀመጡ፤ እነርሱም ቀን ቀን ይጽፉ ነበር፤ ማታ ማታም እህል ይመገቡ ነበር፤ 43እኔ ግን ቀን እናገራለሁ፤ ሌሊትም ዝም አልልም። 44በእነዚያ በአርባ ቀኖችም ሃያ አራት መጻሕፍት ተጻፉ። 45ከዚህም በኋላ እነዚያ አርባ ቀኖች በተፈጸሙ ጊዜ ልዑል ተናገረኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “አስቀድሞ የጻፋችሁትን ያን ግልጥ አድርገው፤ የሚገባውም የማይገባውም ሁሉ ያንብበው። 46ይህን ግን ለጠቢባን ሕዝብ ትሰጣቸው ዘንድ ጠብቅ። 47በእነዚህ ውስጥ የማስተዋል መብራት፥ የጥበብ ምንጭ፥ የዕውቀትም ፈሳሽ አለና።” 48እንዲሁም አደረግሁ፤ በአራተኛው ዓመት፥ ከዓመታቱ ሱባዔያት በአምስተኛው ሱባዔ፥ ከፍጥረተ ዓለም በኋላ በአምስት ሺህ ዓመታት፥ ጨረቃ ሠርቅ ባደረገች በዐሥረኛው ቀን በሦስተኛው ወር፥ በዘጠና አንድ ቀናት። 49ያንጊዜ ይህን ሁሉ ከጻፈ በኋላ ዕዝራን ይዘው እንደ እርሱ ያሉ ሰዎች ወዳሉበት ሀገር ወሰዱት፤ እርሱም እስከ ዘለዓለም ድረስ የልዑል የጥበቡ ጸሓፊ ተባለ።