መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 8
1መልአኩም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “አንተ ራስህ ገምግመው፤ እኔ ከነገርሁህ ምልክት ያለፈ ብታይ፥ 2ልዑል የፈጠረውን ዓለም ይጐበኝበት ዘንድ ያለው ጊዜ እንደ ደረሰ ያንጊዜ ዕወቅ። 3በዓለም በየሀገሩ ሽብር በሆነ ጊዜ፥ አሕዛብም በታወኩ ጊዜ፥ ሕዝቡም በተሸበሩ ጊዜ፥ አለቆችም በተዋጉ ጊዜ፥ መሳፍንቱም በደነገጡ ጊዜ፥ 4ስለዚህ ልዑል ከጊዜው አስቀድሞ እንደ ተናገረ ያንጊዜ ዕወቅ። 5በዓለም የሆነው ሁሉ አስቀድሞ በቃል፥ ኋላም በመገለጥ እንደ ሆነ፥ 6እንዲሁም የልዑል ዓለም መጀመሪያ በቃል፥ በተአምርና በኀይል፥ ኋላ ግን በሥራና በድንቅ ነው። 7በምግባሩና በአመነበት ሃይማኖቱ የዳነና ማምለጥ የቻለ፥ 8ከነገርሁህ ሥቃይ የሚድን እርሱ ብቻ ነው፤ ከዚህ ዓለም ለእኔ በለየኋት በምድሬና በድንበሬም ሕይወትን ያያል። 9ዛሬ ትእዛዜን ቸል ያሉ ያንጊዜ መከራን ይቀበላሉ፤ እኔን መፍራትን የተዉና የናቁኝም በገሃነም ውስጥ ይጨነቃሉ። 10እኔ እየረዳኋቸው በሕይወታቸው ሳሉ የማያውቁኝም ሁሉ፥ 11እነርሱ ነጻ ሳሉ በሕጌ ላይ የታበዩም ሁሉ፥ 12የትዕግሥቴም ቦታ ክፍት ሆኖላቸው ሳለ ልብ ያላደረጉኝ፥ የናቁኝም ሁሉ፥ ከሞቱ በኋላ ያውቁኝ ዘንድ አላቸው። 13አንተ ግን ኃጥኣን እንዴት እንደሚፈረድባቸው አትመርምር፤ ጻድቃን በዓለማቸው እንዴት እንደሚድኑ መርምር እንጂ፤ የሚመጣው ዓለም ስለ እነርሱ ነውና።” 14እኔም መለስሁለት፤ እንዲህም አልሁት፦ 15“ዝናም ከካፊያ እንደሚበዛ ከሚድኑት ኋለኞች ይልቅ የሚጠፉት እንደሚበዙ ቀድሞ ተናገርሁ፤ ዛሬም እናገራለሁ።” 16እርሱም መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “ዘሩ በእርሻው መጠን እንደ ሆነ ፍርዱም እንደ ሥራው ነው፤ አጫጁም በአራሹ መጠን ነው። 17ዛሬ በውስጡ የሚኖሩበት ዓለማቸው ሳይፈጠር ያዘጋጀሁት ዓለም በጊዜው ነውና። 18ያንጊዜም የተከራከረኝ የለም፤ ማንም የነበረ የለምና። 19አሁንም በምግብና ፍለጋ በሌለው በዘለዓለማዊ ሕግ በተዘጋጀው ዓለም ከተፈጠሩ በኋላ በሥራቸው ሞት ነበር። 20ዓለሙንም ባየሁት ጊዜ እነሆ፥ እነርሱ ጠፉ። በምድር በተዘራው ሥራቸውም እነሆ፥ ዓለም ይጨነቃል። 21ሄጄም ለጥቂቶቹ ራራሁላቸው፤ ከዘለላውም ውስጥ ፍሬዎችን ለእኔ አስቀረሁ። ከብዙ ዛፍም አንድ ተክል መረጥሁ። 22በከንቱ የተወለዱ ብዛታቸው ይጠፋል፤ በብዙ ሥራ የጸናች ፍሬዬም፥ ተክሌም ትጠበቃለች። 23አንተ ግን ዳግመኛ ሰባት ቀን ብትጾምና ብትጸልይ፥ 24ግንብ ወደአልተሠራባት ምድረ በዳ ብትሄድና ከእንጨት ፍሬ ብቻ ብትበላ፥ ሥጋም ባትበላ፥ ከእንጨቱ ፍሬ ብቻ በቀርም ወይን ባትጠጣ፥ 25ወደ ልዑል ሁልጊዜ ብትጸልይ መጥቼ እነግርሃለሁ።”
አራተኛው ራእይ
26ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ ስሙ አርፋድ ወደሚባል ምድረ በዳ ሄድሁ። 27በሣር ውስጥ ተቀመጥሁ፤ የምድረ በዳንም ፍሬ ተመገብሁ፤ የበላሁትም ያጠግበኝ ነበር። 28ከዚህም ከሰባተኛው ቀን በኋላ በሣር ውስጥ ተኝቼ ሳለሁ ልቤ እንደ ቀድሞው ታወከብኝ። 29አንደበቴንም አቅንቼ በልዑል ፊት እናገር ጀመርሁ፤ 30እንዲህም አልሁ፥ “አቤቱ ጌታዬ፥ ዛፍና ሣር በሌሉበት ምድረ በዳ ለአባቶቻችን ፈጽመህ ታየሃቸው። 31እንዲህም አልሃቸው፦ ‘አንተ እስራኤል ስማኝ፤ ቃሌንም አድምጠኝ፤ 32እነሆም እኔ ሕጌን በውስጣችሁ እዘራለሁና፥ በላያችሁም ፍሬን ያፈራልና፥ ለዘለዓለሙም ትከብሩበታላቸሁና።’ 33አባቶቻችንም ሕግህን ተቀብለው አልጠበቁም፤ በሥርዐትህም አልጸኑም፤ የሕግህ ፍሬ ግን አልጠፋም፤ የአንተ ገንዘብ ስለሆነ ይጠፋ ዘንድ አይቻልምና። 34ሕግ ያንተ ገንዘብ ስለሆነች በውስጣቸው የተዘራውን ተግባራቸውን አልጠበቁምና ሕግህን ተቀብለው ያልጠበቁ ጠፉ። 35ምድርም ዘርን ከተቀበለች በኋላ፥ ባሕርም መርከብ በውስጧ ከገባ በኋላ፥ ዕቃም በውስጡ መብልና መጠጥን ከጨመሩበት በኋላ፥ 36ያንጊዜ የዚያ የዘሩ፥ የዚያም የመርከቡ፥ የዚያም የመብሉና የመጠጡ ይጠፋ ዘንድ ጊዜው ቢሆን እንደዚሁ የሚጠፋ ይሆናል። ነገር ግን የያዙት ይቀራሉ። ለእኛስ እንደዚሁ አይደለም። ሕግን ተቀብለን የበደልን እኛ እንጠፋለንና፥ የተቀበለው ልባችንም እንዲሁ ነው፤ ሕጉ ግን በክብሩ ይኖራል እንጂ አይጠፋም።”
ስለምታለቅሰው ሴት የዕዝራ ራእይ
37በዐይኖችም በተመለከትሁ ጊዜ በቀኝ በኩል እነሆ፥ አንዲት የምታለቅስ ሴትን አየሁ፤ በታላቅ ድምፅም ትጮኽ ነበር፤ እጅግም አዝና ነበር፤ ልብሷም ተቀድዶ ነበር፤ በራሷም ላይ ዐመድ ነስንሳ ነበር። 38ያ ቀድሞ የማስበው አሳቤም ተለየኝ፤ ወደ እርሷም ተመልሼ፥ “ምን ያስለቅስሻል? ልቡናሽንስ ለምን ታሳዝኛለሽ? አልኋት።” 39እርስዋም አለችኝ፥ “ጌታዬ ለራሴ አለቅስ ዘንድ በመከራዬም ላይ መከራን እጨምር ዘንድ ተወኝ፤ ፈጽሜ እኔ አዝኛለሁና፥ ልቡናዬም ተጨንቃለችና።” 40እኔም፥ “ምን ሆነሻል? ንገሪኝ” አልኋት። 41እርስዋም አለችኝ፥ “እኔ ባሪያህ ከጥንት ጀምሮ መካን ነበርሁ፤ ሠላሳ ዘመን ከባሌ ጋር ስኖር ልጅ አልወለድሁም። 42እኔም በዚያ በሠላሳው ዘመን ሁልጊዜ በየጊዜውና በየሰዓቱ በመዓልትና በሌሊት ወደ ልዑል እጸልይ ነበር። 43ከዚህም ከሠላሳ ዓመት በኋላ እግዚአብሔር የባሪያውን ልመና ሰማ፤ መከራዬንም አየ፤ ድካሜንና ሥቃዬን ተመልክቶ አንድ ልጅ ሰጠኝ፤ በእርሱም ፈጽሞ ደስ አለኝ፤ እኔም፥ ባሌም፥ ያገሬም ሰዎች ሁሉ ደስ አለን፤ እግዚአብሔርንም አመሰገንነው። 44በብዙ ድካምም አሳደግሁት። 45ከዚህም በኋላ አካለ መጠን ባደረሰ ጊዜ ሚስት አጋባሁት፤ ሰርግንም ሰረግሁለት።