1መልአኩም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “ይህንስ ዓለም ልዑል ስለ ብዙዎች ፈጠረው፤ የሚመጣውን ግን ስለ ጥቂቶች ፈጠረው። 2“ዕዝራ! እነሆ በፊትህ ምሳሌውን እተረጕምልሃለሁ፤ ምድርን ጠይቃት፤ ትነግርሃለችም፤ ከእርሱ ሸክላ የሚገኝበትን መሬት ታስገኛለችና፥ መሬትም ወርቅ ከእርሱ የሚገኝበትን ታስገኛለችና፥ ከወርቅ ይልቅ ሸክላ እጅግ ይበዛል። 3የዚህ ዓለም ሥራም እንዲሁ ነው፤ በውስጡ የተፈጠሩ ብዙ ናቸው፤ የሚድኑ ግን ጥቂቶች ናቸውና።” 4እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “ልብ ከጥበብ የተነሣ ደስ ይበላት፤ ጆሮም ነገርን ትጠጣ። 5ጆሮ ለመስማት ተሠርትዋልና፥ ልብም ለማወቅ ተፈጥሯልና፥ ሰው ከጥቂት ሕይወት በቀር ሳይሰጠው ባልወደደው ይሄዳል። 6አቤቱ ለባሪያህ ከፈቀድህለት፥ ዓለም ሰውን በሚችለው ገንዘብ ሙታን ሁሉ መኖርን ይችሉ ዘንድ እንዲያፈራልን እናርስና እንዘራ ዘንድ ልብንና ሕሊናን ብትሰጠን በተሻለን ነበር። 7የእጆችህ ፍጥረት እኛ አንተ እንደተናገርህ ሁላችን የተካከልን ነንና። 8ዛሬ በማኅፀን ትፈጥረዋለህና፥ ሥጋንና ሕዋሳትንም ትቀርጽለታለህና፥ ማስተዋልንም ትሰጠዋለህና፥ በእሳትና በውኃ ትጠብቀዋለህና፥ ያን የፈጠርኸውንም በማኅፀን ዘጠኝ ወር ትሸከመዋለህና፥ ባንተም ቃል ይጠበቃልና። 9ዳግመኛም እናቱ በወለደችው ጊዜ፥ ከተወለደና ከተፈጠረ በኋላ፥ የሚጠባበትን ወራት እስኪጨርስ ድረስ ይህ ባሪያህ ሕፃኑ ያድግ ዘንድ፥ 10ከሰውነትዋ በላይ ካሉ ከጡቶችዋም የጡት ፍሬ ወተት ይፈስለት ዘንድ ታዝለታለህ፥ 11ይህ ባሪያህ እስከ ጊዜው ድረስ ያድግ ዘንድ በቸርነትህ ታሳድገዋለህ። 12በቸርነትህም ትመግበዋለህ፤ ሕግህንም ታስተምረዋለህ፤ በጥበብህም ትገሥጸዋለህ። 13ከዚህ በኋላ የፈጠርኸውንና ሕያው ያደረግኸውን ያን ባሪያህን ትገድለዋለህ። 14ፈጥረህ ይህን ያህል ዘመን ያኖርኸውን ያን ባሪያህን የምታጠፋው ከሆነ እንግዲያ ለምን ፈጠርኸው? 15አሁንም ነገርህ እውነት ነው፤ ስለ ሁሉም አንተ ታውቃለህ፤ ነገር ግን እናገር ዘንድ እኔን ያተጋኝ አይደለም። 16ይህን የማዝን ስለ ወገኖችህና ስለ ርስትህ ነው እንጂ። 17ይህንም በፊትህ እማልድ ዘንድ የጀመርሁት ስለ እኔም፥ ስለ እነዚያም ነው። የሚመጣውን ዓለም ሕጉን እየሰማን የምንኖር የእኛን መሰነካከል አያለሁና። 18ስለዚህም ቃሌን ስማ፤ በፊትህ የምናገረውንም ልመናዬን አድምጥልኝ።”
የዕዝራ ጸሎት
19ሳይወስዱት የዕዝራ የጸሎቱ ቃል መጀመሪያ ይህ ነው። 20“ለዘለዓለሙ የምትኖር አቤቱ፥ በልዑል አርያም ሁነህ የምታይ፥ በሰማይ ያለህ፥ 21ሥልጣንህ የማይሸነፍ፥ መንግሥትህ የማያልፍ፥ ሠራዊተ መላእክት በፍርሀት የሚቆሙልህ፥ 22ነፋስና እሳት በትእዛዝህ የተፈጠሩ፥ ቃልህ ጽኑ የሆነ፥ የተናገርኸውም ጸንቶ የሚኖር፥ 23ሥርዐትህ ጽኑ የሆነ፥ ትእዛዝህም የሚያስፈራ፥ ትእዛዝህም ጥልቆችን የሚያደርቅ፥ ቍጣህም ተራራዎችን የሚያቀልጥ፤ ሕግህም እውነት የሆነ፥ 24አቤቱ፥ የባሪያህን ቃል ስማ፤ የባሪያህን ልመና አድምጥ፤ ነገሬንም አድምጥ። 25እኔ በሕይወት ሳለሁ እነግርሃለሁ፤ ልቡናዬም እንዳሰበ መጠን እነግርሃለሁ፤ እመልስልሃለሁም። 26የወገኖችህን በደል አትመልከት፤ ለአንተ የተገዙልህን ጽድቃቸውን ተመልከት እንጂ። 27የኃጥኣንን ሥራቸውን አትመልከት፤ በመከራቸው ሥርዐትን የጠበቁትን ተመልከት እንጂ። 28በፊትህ ክፉ ሥራን ስለሠሩ አትቈጣ፤ በፍጹም ልባቸው በሕግህ የታመኑትን አስብ እንጂ። 29በሥራቸው እንደ እንስሳ የሆኑ ሰዎችን ጥፋት አትውደድ። ሥርዐትህን በብሩህ ልቡና ያጸኗትን አስባቸው፤ ተመልከታቸውም እንጂ። 30ከአራዊት የከፉ ሰዎችን አትቈጣቸው። በጌትነትህ መታመን ያዘወተሩትን ውደዳቸው እንጂ። 31ነገር ግን እኛና ከእኛ አስቀድሞ የነበሩ ሞትን የሚያመጣ ሥራን ሠራን። 32አንተ ግን ስለ እኛ፥ ስለ በደሉ ሰዎችም ይቅር ባይ ሁን፤ በጎ ሥራ የሌለን እኛን ይቅር ብትለን ያንጊዜ ይቅር ባይ ትባላላህና። 33በአንተ የተዘጋጀ በጎ ሥራ ያላቸው ጻድቃንን ግን በሥራቸው ይቅር ትላቸዋለህ። 34ትቈጣው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ስለ እርሱስ ታዝን ዘንድ የመዋቲ ወገን ምንድን ነው? 35አሁንም ከተወለደው ወገን የማይበድል እንደሌለ እውነት እናገራለሁ። 36ነገር ግን ጌታ ሆይ፥ ስለዚህ በጎ ሥራ የሌላቸውን ይቅር ብትላቸው ቸርነትህ ፈጽሞ ይታወቃል።” 37እርሱም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “በእኔ ዘንድ እውነትን ተናገርህ፤ አንተ እንደ ተናገርኸው እንዲሁ ነው። 38ለሚበድሉ ሰዎች ሞትን፥ ፍርድንም፥ ጥፋትንም በእውነት አልወድላቸውም። 39ነገር ግን ስለ ጻድቃን ደስ ይለኛል፤ የሚድኑ ዋጋቸውን ያገኛሉና። 40እንደ ተናገርኸውም እንዲሁ ይሆናል። 41ገበሬ ብዙ ዘር እንደሚዘራ፥ ብዙ ተክልንም እንደሚተክል፥ ጊዜውም ቢሆን ዘሩ ሁሉ የሚበቅል እንደ አይደለ፥ ተክሉም ሁሉ ሥር የሚሰድድ እንደ አይደለ፥ በዚህ ዓለም ያሉ ሰዎችም እንዲሁ ናቸው፤ ሁሉም የሚድኑ አይደሉም።” 42እኔም መለስሁለት፤ እንዲህም አልሁት፥ “በፊትህ ባለሟልነትንስ ካገኘሁ ልናገር። 43የገበሬ ዘርስ ባይበቅል ምናልባት ዝናም ባያገኝ ይሆናል፤ ስለዚህም ይጠፋል። 44ነገር ግን በእጅህ የፈጠርኸው፥ በአምሳልህም የመሰልኸው ሰው አምሳልህ ነውና፥ ስለ እርሱም ሁሉን ፈጥረሃልና፥ እንግዲህ እንደ ገበሬ ዘር ለምን ታደርገዋለህ? 45አቤቱ አገባብህም አይደለም፤ ለወገኖችህ ራራ፤ ርስትህንም ይቅር በል እንጂ፤ ፍጥረትህን ይቅር ትለዋለህና።” 46እርሱም መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “በዚህ ዓለም ያለው በዚህ ዓለም ላሉት ምሳሌያቸው ነው፤ የወዲያው ዓለም ግን በወዲያው ዓለም ለሚኖሩ ምሳሌያቸው ነው። 47ነገር ግን ዕውቀት ያነሰህ አንተ ከእኔ ይልቅ ፍጥረቴን ፈጽመህ ትወድድ ዘንድ፥ ይልቁንም አንተ ኃጥእ ሳትሆን በብዙ ወገን ኃጥእን ትመስላለህ። 48ነገር ግን ስለዚህ በልዑል ዘንድ ትመሰገናለህ፤ 49ራስህን አዋርደሃልና፥ ፈጽመህም ትመሰገን ዘንድ እንደሚገባህ ራስህን እንደ ጻድቃን አላደረግህምና። 50አሁንም በዚህ ዓለም የሚኖሩ ጐስቋሎች በኋላ ዘመን ብዙ መከራን ይቀበላሉ። በብዙ ትዕቢት ኖረዋልና። 51አንተ ግን ለራስህ ዕወቅ፤ እንደ አንተ ያሉትንም ክብር መርምር፤ 52ገነት ለእናንተ ተከፍታለችና፥ ዕፀ ሕይወትም ተተክሏልና፥ የሚመጣውም ዓለም ተዘጋጅቶ ተሠርትዋልና፥ ደስታም ተሠርታለችና፥ ዕረፍትም ተነጥፋለችና፥ በጎ በረከትም ጸንታለችና፥ የጥበብ ሥርዋ ተገኝትዋልና። 53እንግዲህ ወዲህ ደዌ አበቃ፤ ሞትም ጠፋ፤ መቃብርም ተሰወረች፤ ሙስናም ጠፋ። 54መከራም ተዘነጋ፤ የሕይወት መዝገብም ተገለጠ። 55እንግዲህ ወዲህ ስለሚጠፉት ሰዎች ብዛት መመራመርን አትድገም። 56እነርሱ ነጻነትን አግኝተው ልዑልን ንቀውታልና፥ ሕጉንም አቃልለዋልና፥ ሥርዐቱንም ትተዋልና። 57ጻድቃኑንም ረግጠዋቸዋልና። 58እንደሚሞቱም እያወቁ በልቡናቸው እግዚአብሔርን አንፈልገውም ብለዋልና። 59ስለዚህም ይህ በጎው ለእናንተ እንደ ሆነ እንዲሁም ይህ ጥፋት ለእነርሱ ነው። 60እነርሱ ከተፈጠሩ በኋላ የፈጣሪያቸውን ስም አሳድፈውታልና፥ ያዘጋጀላቸውን እግዚአብሔርንም አላመሰገኑትምና። 61አሁንም ፍርዳቸው ይደርስባቸዋል። 62ለአንተና እንደ አንተ ለአሉ ለጥቂቶች እንጂ ይህን ለብዙዎች አልተናገርሁም።” 63እኔም መለስሁለት፤ እንዲህም አልሁት፥ “አቤቱ! እነሆ፥ እስካሁን ድረስ በኋላ ዘመን ታደርገው ዘንድ ያለህን ብዙ ምልክት ነገርኸኝ፤ ነገር ግን ጊዜው መቼ እንደ ሆነ አልነገርኸኝም።”