ለዕዝራ ጥያቄ የተሰጠ መልስ
1መልአኩም መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “ልዑል ይህን ዓለም፥ አዳምንና ከእርሱ የተወለዱትንም ሁሉ በፈጠራቸው ጊዜ ቍርጥ ፍርድንና ቅጣቱን አስቀድሞ አዘጋጀ። 2አሁንም ከቃልህ የተነሣ አስተውል፤ እንዲህ ብለሃልና፦ ‘ክፉ ልብ ከእኛ ጋር ያድጋል፤ 3በምድር የሚኖሩም ስለ እርሱ ይፈረድባቸዋል፥ አእምሮ ሳላቸው ይበድላሉና፥ ሕጉንም በልቡናቸው ተቀብለው ትእዛዙን አልጠበቁምና፥ ሕጉንም ተምረው የተቀበሉትን ሕጉንና ትእዛዙን ትተዋልና። 4እንግዲህ በቍርጥ ፍርድ ቀን ምን ይሉ ዘንድ አላቸው? በኋለኛው ዘመንስ ምን ይናገራሉ? 5ልዑል በዚህ ዓለም የሚኖሩ ሰዎችን ምን ያህል ታገሣቸው? ነገር ግን ስለ ወሰነው ጊዜ ነው እንጂ ስለ እነርሱ አይደለም።”
ከፍርድ በፊት ያለ የሙታን ሁኔታ
6እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “በፊትህ ባለሟልነትን ካገኘሁ ይህንም ለባሪያህ ንገረው፤ በሞትን ጊዜ፥ ከእኛ ከእያንዳንዳችንም ነፍሳችን በምትወጣበት ጊዜ ቍርጥ ፍርዱን የሚያደርግበት ጊዜው እስኪደርስ ድረስ ይጠብቁናል? ወይስ ከዛሬ ጀምሮ ይፈረድብናል?” 7እርሱም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “ይህንም እነግርሃለሁ፤ አንተ ግን ከከሓድያን ጋር አትጨመርም፤ ከሚፈረድባቸውም ጋር አትቈጠርም። 8በልዑል ዘንድ የተዘጋጀ መዝገብ ለአንተ አለህና፥ ነገር ግን እስከ ኋለኛው ቀን ድረስ አልገልጥልህም። 9የሞትስ ነገር እንዲህ ነው፤ ከልዑል ዘንድ የትእዛዝ ቃል ከመጣ በኋላ፥ እገሌ ይሙት ባለ ጊዜ ነፍሱ ከሥጋው ትለያለች፤ ዳግመኛም ወደ ሰጣት ትመለሳለች፤ ለልዑል ጌትነትም አስቀድማ ትሰግዳለች። 10የልዑልን መንገዶች ካልጠበቁ፥ የልዑልን ሕግ ካቃለሉ፥ እርሱንም መፍራትን ካላሰቡ ከከሓድያን ወገን ከሆኑ ግን፥ 11እነዚያ የኃጥኣን ነፍሳት ይዞራሉ እንጂ ወደ ጻድቃን ማደሪያ አይገቡም፤ ከዚህ በኋላ መከራ ይቀበላሉ፤ ይጨነቃሉ፤ ያዝናሉም፤ ሰባቱንም ሥርዐታት ያሳዩአቸዋል። 12መጀመሪያዪቱ ሥርዐት ይህች ናት፤ የልዑልን ሕግ ክደዋልና። 13ሁለተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፤ ከእንግዲህ ወዲህ ዳግመኛ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ መመለስ አይቻላቸውምና። 14ሦስተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፥ በልዑል ሥርዐት ላመኑ የተዘጋጀላቸውን ዋጋ ያያሉና። 15አራተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፤ በኋላ ዘመን የሚጠብቃቸውን ፍርድ ያያሉና። 16አምስተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፤ መላእክት የጻድቃንን ነፍስ በማደሪያቸው ውስጥ በብዙ ዕረፍት ሲጠብቋቸው ያያሉና። 17“ስድስተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፤ ከዛሬ ጀምሮ የሚያገኛቸውን መከራ እያዞሩ ያሳዩአቸዋልና። 18ከነገርሁህ ሥርዐታት ሁሉ የምትበልጥ ሰባተኛዪቱ ሥርዐት እንዲህ ናት፤ በፊቱ ይፈረድባቸው ዘንድ ያላቸው ዛሬ በሕይወታቸው ሳሉ እርሱን የበደሉ በፊታቸው የልዑልን ጌትነት ባዩ ጊዜ በኀሣር ይቀልጣሉና፥ በኀፍረትም ይጐሳቈላሉና፥ በፍርሀትም ይጠወልጋሉና። 19“የልዑልን ሕግ የጠበቁ ግን ከመዋቲ ሥጋቸው በሚለዩበት ጊዜ ሥርዐታቸው እንዲህ ናት። 20በኖረበት ዘመን ሁሉ ያስተማራቸው የልዑልን ሕግ ይፈጽሙ ዘንድ መከራቸውን ታግሠው ሁልጊዜ በድካም ለእግዚአብሔር ተገዝተውለታልና። 21ስለዚህ ነገራቸው እንዲህ ነው። 22መጀመሪያ የተቀባያቸውን የእግዚአብሔርን ጌትነት በብዙ ደስታ ያያሉ፤ ወደ ሰባቱም ሥርዐታት ይወስዷቸዋል። 23መጀመሪያዪቱ ሥርዐት እንዲህ ናት፤ በዛሬው ሕይወታቸው በሞት እንዳያስታቸው በእነርሱ ያለ ክፉ አሳብን ድል ይነሡ ዘንድ በብዙ ድካም ተጋድለዋልና። 24ሁለተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፤ የኃጥኣንን ነፍሳት በሚዞሩበት ያዩአቸዋልና፤ የሚጠብቃቸውንም ፍርድ ያያሉና። 25ሦስተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፥ በሕይወት ሳሉ በሃይማኖት የተቀበሉትን ሕጉን እንደ ጠበቁ የፈጠራቸው ምስክር ይሆንላቸዋልና። 26አራተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፥ መላእክት እየጠበቋቸው ብዙ ደስታ ባለባቸው ማደሪያዎቻቸው ከዛሬ ጀምሮ የሚያርፉትን ዕረፍትና የሚቈያቸውን ክብር ያያሉና። 27አምስተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፤ ዛሬ ያለውን ሞት እንዴት ድል እንደነሡትና ኋላ ያገኙት ዘንድ ያላቸውን እንደ ወረሱ አይተው ደስ ይላቸዋልና፤ ዳግመኛም ድካምን ከተመላ ከዚህ ከጠባቡ የተነሣ እንደታገሡ፥ ያን ሰፊውን ሕይወት እንደሚያገኙ ያያሉ። ሞት በሌለበትም ለዘለዓለም ደስ ይላቸዋል። 28ስድስተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፤ ፊታቸው እንደ ፀሐይ እንደሚያበራ፥ ብርሃናቸውም እንደ ከዋክብት እንደሚያንጸባርቅ ያሳዩአቸው ዘንድ አላቸውና፥ ከእንግዲህ ወዲህም አይሞቱምና። 29ከሁሉ የምትበልጥ ሰባተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፤ በእርሱ ዘንድ ይከብሩና ዋጋ ያገኙ ዘንድ ያላቸው በሕይወት ሳሉ የተገዙለትን ፊቱን ያዩ ዘንድ የሚቸኩሉ ስለ ሆነ ሳያፍሩ በብዙ ደስታ ተማምነው በግልጥ ይመካሉና። 30“ከዛሬ ጀምሮ ያገኙ ዘንድ ያላቸው የጻድቃን ነፍሳት ሥርዐታቸው ይህ ነው፤ ከሓድያንም መከራ ይቀበሉ ዘንድ የነገርሁህ ሥርዐታቸው፥ መንገዳቸውና ፍርዳቸው ይህ ነው።” 31እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “ከሥጋዋ ከተለየች በኋላ ይህን የነገርኸኝን ታይ ዘንድ ለነፍስ ቀን ይሰጣታልን?” 32“በእነዚያም በሰባቱ ቀኖች ይህን የነገርሁህን ሥራቸውን ሁሉ ያዩ ዘንድ ለሰባት ቀን ነጻ ናቸው፤ ከዚያም በኋላ ወደ ቦታቸው ይመለሳሉ” አለኝ። 33እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “አቤቱ ጌታዬ፥ በፊትህ ባለሟልነትን ካገኘሁ ይህንም ለባሪያህ ዳግመኛ ንገረው፤ በፍርድ ቀን ጻድቃን በልዑል ዘንድ ለኃጥኣን መለመን ይችላሉን? 34አባቶችም ለልጆቻቸው፥ ልጆችም ለአባቶቻቸው፥ ወንድሞችም ለወንድሞቻቸው፥ ዘመዶችም ለዘመዶቻቸው፥ ወዳጆችም ለወዳጆቻቸው መለመን ይችላሉን?” 35እርሱም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “በፊቴ ባለሟልነትን አግኝተሃልና ይህንም እነግርሃለሁ፦ የፍርድ ቀንስ ለአንድ ጊዜ ናት፤ በሁሉም ትእዛዝ ላይ የእውነት ማኅተምን ያሳያቸዋል። 36ዛሬ አባት ልጁን ስለ እርሱ፥ ልጅም አባቱን፥ ጌታም አገልጋዩን፥ ወዳጅም ወዳጁን ስለ እርሱ ታሞ ይተኛ ዘንድ፥ በልቶና ጠጥቶም ደስ ይለው ዘንድ፥ ይፈወስም ዘንድ እንደማይልከው፥ 37እንደዚሁ አንዱ ለሌላው መለመን ፈጽሞ የሚችል ማንም የለም፤ የራሱንም ሸክም በባልንጀራው ላይ የሚመልስ ማንም የለም። ሁሉም ዋጋውን ያገኛልና፥ ሥራውም የየራሱ ነውና።” 38እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “ቀድሞ አብርሃም ስለ ሰዶምና ገሞራ፥ ሙሴም በምድረ በዳ በበደሉ ጊዜ ስለ አባቶቻችን እንደ ለመነ ዛሬ እንዴት አገኘን? 39ኢያሱ በአካን ዘመን ስለ እስራኤል፥ ሳሙኤልም በሳኦል ዘመን፥ 40ዳዊትም ስለ ቸነፈር፥ ሰሎሞንም ስለ ቤተ መቅደስ፥ ኤልያስም ስለ ዝናምና ስለ ሙታን ይድኑ ዘንድ፥ 41ሕዝቅያስም በሰናክሬም ዘመን ለሕዝቡ፥ ብዙ ሰዎችም ስለ ብዙዎች ለመኑ። 42እንግዲህ ዛሬ መዋቲው በሕይወት ሳለ፥ ኀጢአትም በዝታ ሳለች ጻድቃን ስለ ኃጥኣን ከለመኑ ያንጊዜስ እንደዚሁ እንደ ምን አይሆንም?” 43እርሱም መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “የዚህ የዛሬው ዓለም ፍጻሜው ገና አልሆነምና፤ የእግዚአብሔርም ክብር በውስጡ ለዘለዓለም ተገልጦ የሚኖር አይደለምና-። ስለዚህም ጽኑዓን ለድኩማን ለመኑ። 44የፍርድ ቀንስ የዚህ ዓለም መጨረሻ ናት፤ መዋቲው ያልፍ ዘንድ፥ የማያልፈውም ይተካ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዓለም መጀመሪያ ናት። 45ከዚህ በኋላ ድካም ይሻራል፤ ጠብም ይጠፋል፤ ጽድቅም ታብባለች፤ ቅንነት ትጸናለች። 46ያንጊዜ በፍርድ ድል የተነሣ ሰውን ይቅር ማለት የሚቻለው የለም፤ ድል የነሣውንም መከራ ሊያጸናበት የሚችል የለም።” 47እኔም መለስሁለት፤ እንዲህም አልሁት፥ “ቃሌ እንደ ቀደመው ነው፤ አሁንም እንዲህ እላለሁ፦ ምድር አዳምን ባታስገኘው በተሻለ ነበር፤ ከአስገኘችውም እንዳይበድል ባስተማረችው ነበር። 48ሁላችን የምንኖረው ሕይወት ምን ይጠቅመናል? በኀዘን እንኖራለንና፤ ከሞትንም በኋላ ዳግመኛ ፍርድ ይቈየናልና። 49አዳም ሆይ! ምን አደረግንህ? አንተ ባትበድል ይህች መከራ በእኛ ላይ ባልመጣችብን ነበር። 50ተስፋ ያስደረግኸን፥ ሞት የሌለበት የሚመጣው ዓለም ምን ይጠቅመናል? እኛ ግን ሞትን የሚያመጣ ሥራን ሠራን። 51የነገሩንን በጎውን ተስፋ አልሠራንም፤ እኛ ግን ክፉ ሥራን ሠራን። ዐመፅንም ተከተልን። 52ኀዘንና ደዌ የሌለባቸውን፥ ለእኛ የተዘጋጁትን ቤቶች አልተከተልንም። እኛ ግን ኀጢአትን ሠራን። 53ያጸናቸው ዘንድ መከራ የተቀበሉ ጻድቃን የልዑልን ጌትነት ያዩ ዘንድ አላቸውና፤ እኛ ግን በበደላችን ኖርን። 54ፍሬው የማይጠወልግ ገነት ይገለጣልና፥ በውስጡም የሚገኘው ፍሬ ደስታና ሕይወት ነውና። 55እኛ ግን አንገባም፤ የማንመሰገንበትን ሥራ እንሠራለንና። 56ትዕግሥትን ያጸኗት ፊታቸው ይበራልና፥ የእኛ ፊት ግን ከጨለማ ይልቅ ይጠቍራል። 57እነሆ፥ ከሞትን በኋላ በእኛ ላይ ምን እንዳለ ሳናውቅ እንኖራለን።” 58መልአኩም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “በዚህ ዓለም ለሚጋደል፥ በምድር ለተወለደ ሰው የታሰበለት ይህ ነው። 59ድል ያደረገ እኔ ያልሁትን ያገኛል፤ ድል የተነሣ ግን አንተ ያልኸውን ያገኛል። 60ትድኑ ዘንድ ሕይወትን ምረጧት ብሎ ሙሴ ለሕዝቡ የነገራቸው መንገድ ይህች ናት። ነገር ግን እርሱን አልተቀበሉትም፤ ከእርሱም በኋላ ነቢያትን የተናገርኋቸው እኔንም አልተቀበሉም። 61በሚያምኑ ሰዎች ደስታ እንዳለ በሚጠፉት ሰዎች ኀዘን የለም።” 62እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “አቤቱ፥ ምንጊዜም እንደ ኢምንት የሆኑትን ይቅር ባላቸው ጊዜ ልዑል ዛሬ ይቅር ባይ እንዲባል ፈጽሜ አውቃለሁ። 63ይቅር ባይ ነው፤ ወደ ሕጉ የተመለሱትን ይቅር ይላቸዋልና። 64ታጋሽም ነው፤ የበደሉትን ሰዎች እንደ ልጆች ይታገሣቸዋልና። 65ለጋስም ነው፤ እንደ ሥራቸው እንደሚገባቸው መጠን ለነገርሁህ ሰዎች ይሰጣቸዋልና። 66ምሕረቱም የበዛ ነው፤ ላሉት፥ ለሚታዘዙትም፥ ይመሰገኑ ዘንድ ላላቸውም ቸርነቱን ፈጽሞ ያበዛልና። 67ቸርነቱን ፈጽሞ ካላበዛ ይህ ዓለም ባልኖረ ነበርና፥ በእርሱም ያሉ ባልኖሩ ነበርና። 68ለጋስም ነው፤ ኃጥኣን ከኀጢአታቸው ይመለሱ ዘንድ ከቸርነቱ ካልሰጣቸው ሰው ሁሉ ባልዳነ ነበርና። 69ፈራጅም ነው፤ እርሱ የፈጠረውን ፍጥረት ካልጠበቀ የከሓድያን ብዛታቸው ይጠፋልና፤ ከቍጥራቸውም ብዛት አይቀርምና። ያም ባይሆን በጣም ጥቂት ነው።”