መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 5
1ከዚህም በኋላ ይህን ነገር ተናግሬ በጨረስሁ ጊዜ ባለፈችው በዚያች ሌሊት አስቀድሞ ወደ እኔ የመጣው ያ መልአክ ወደ እኔ ተላከ። 2እንዲህም አለኝ፥ “ዕዝራ ሆይ፥ ተነሥ፤ እነግርህ ዘንድ ወደ አንተ የመጣሁ የእኔን ቃል ስማ።” 3እኔም አልሁት፥ “ጌታዬ ተናገር፤” እርሱም አለኝ፥ “በአንድ ሰፊ ቦታ ባሕር አለች፤ እርስዋም ሰፊና ጥልቅ ናት። 4ጠባብ የመግቢያ መንገድም አላት፤ የመስኖ ውኃ ቦይ ያህልም ትሆናለች። 5ያያትና ያገኛት ዘንድ ወደዚያች ባሕር ሊገባ የወደደ ቢኖር ያን ጠባቡን መግቢያዋን ካላለፈ ወደ አደባባይዋ መግባት እንዴት ይችላል? 6ወይም በሜዳ የተሠራች፥ ከበረከቱም ሁሉ የተመላች አንዲት ከተማ አለች። 7የመግቢያዋም መንገድ ጠባብ ነው፤ በገደል ውስጥም ናት፤ በቀኝዋ እሳት፥ በግራዋም ጥልቅ ውኃ አለ። 8አንዲት መንገድ በውኃና በእሳት መካከል አለች፤ መንገድዋም ከአንድ ሰው እግር ጫማ በቀር አትችልም። 9ይህች ከተማ የተሰጠችው የሚወርሳት ሰው ቢኖር ያን ጠባቡን መንገድ ካላለፈ ርስቱን እንዴት ያገኛል?” 10እኔም፥ “አቤቱ፥ እንደዚሁ ነው” አልሁት። እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “የእስራኤል ምድራቸው፥ ዕድል ፈንታቸውም እንዲሁ ነው። 11ዓለምን ስለ እነርሱ ፈጥሬዋለሁና። 12አዳምም ትእዛዜን ባፈረሰ ጊዜ የዚህ ዓለም ጎዳናው ሰንከልካላና ጠባብ፥ ጐድጓዳና የከፋ፥ መከራው የበዛ፥ ጻዕርና ጋርን የተመላ ሆነ። 13የዚያኛው ዓለም ግን ጎዳናው ታላቅ ነው፤ ሰፊም ነው፤ ብሩህም ነው፤ ሞት የሌለበት የሕይወት ፍሬንም ያፈራል። 14ሕያዋን የምትሆኑ እናንተም ያን ሰንከልካላና ያን ኀጢአት ካላለፋችሁት ለእናንተ የተዘጋጀውን ማግኘት አትችሉም። 15አሁንስ አፈር የምትሆን አንተ ለምን ትታወካለህ? ሟች የምትሆን አንተስ ለምን ትናወጣለህ? 16ያለውን ነው እንጂ የሚመጣውን በልብህ ለምን አታስብም?”
የኃጥኣን ዕድል ፈንታ
17እኔም መልሼ አልሁት፥ “አቤቱ ጌታዬ፥ ጻድቃን ይህን ዓለም እንደሚወርሱት፥ ኃጥኣን ግን እንደሚጠፉ አንተ በሕግህ እነሆ፥ ተናገርህ። 18ጻድቃን ሰፊውን ተስፋ እያደረጉ ጠባቡን ይታገሡታልና፤ ጠባቡን የሚታመኑ ኃጥኣን ግን ሰፊውን አያገኙትም።” 19እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “አንተ በፍርድ ከአንዱ ከእግዚአብሔር የምትሻል አይደለህም፤ ከልዑልም አንተ የምትራቀቅ አይደለህም። 20የሠራውን የእግዚአብሔርን ሕጉን ያቃለሉ እነዚያ ይጥፉ፤ 21እግዚአብሔር ሕጉን ሠርተው በሕይወት እንዲኖሩ አዟቸዋልና። ሕጉን ቢጠብቁ ግን ባልተፈረደባቸውም ነበር። 22ኃጥኣን ግን ካዱት፤ ተዉትም፤ ለራሳቸውም ክፉ አሳብን አሰቡ። 23ሽንገላንና ዐመፅን ለራሳቸው ገንዘብ አደረጉ፤ ከዚህም ሁሉ ጋር እግዚአብሔር የለም አሉ፤ መንገዱንም ተዉ። 24ሕጉንም ካዱ፤ ቃል ኪዳኑንም ቸል አሉ፤ በሥርዐቱም አልታመኑም፤ ሥራውንም ናቁ፤ አምልኮቱንም አላሰቡም። 25ስለዚህ የተራቈተው ለተራቈቱት ነው፤ የተሞላውም ለተሞሉት ነው።
የመሲሕ መንግሥት
26“እኔ የነገርሁህ ምልክት የሚገለጥበት ወራት እነሆ፥ ይመጣልና፥ ዛሬ የምትታይ ከተማ ታልፋለች፤ ዛሬ የተሰወረች ምድርም ትገለጻለች። 27እኔ ከነገርሁህ ከክፉ ሥራ የዳነ ሁሉ ክብሬን የሚያይ እርሱ ነው። 28የእኔ መሲሕ አብረውት ካሉት ጋር ይገለጣልና፥ የሚነሡትንም ደስ ያሰኛቸዋል። 29ከዚህ በኋላ ልጄ መሲሑ ይፈጽማል፤ አእምሮ ያለውም ሰው ሁሉ ይፈጽማል፤ 30ዓለምም እንደ ቀድሞው ሰባት ቀን ዝም ያለውን ያህል ወደ ቀድሞ አነዋወሩ ይመለሳል፤ የሚቀርም የለም። 31ከሰባት ቀን በኋላም የነቃበት ጊዜ የሌለ ሰው ይነሣል፤ የመዋቲ ሰው ዓለምም ያልፋል። 32ምድርም የተቀበሩባትን ሰዎች ትመልሳለች፤ መሬትም በውስጡ ያረፉትን ሰዎች ይመልሳል፤ ከዚህም በኋላ አብያተ ነፍስ በውስጣቸው የተቀመጡ ነፍሳትን ይመልሳሉ። 33ያንጊዜም ልዑል በፈጠረው በዙፋኑ ላይ ይገለጣል፤ ቸርነቱም ትመጣለች፤ ይቅርታውም ትመለሳለች፤ ትዕግሥቱም ትሰበሰባለች። 34ቍርጥ ፍርድ ብቻ ይቀራል፤ ጽድቅ ትጸናለች፤ ሃይማኖትም ትገለጣለች። 35ሰውን ሥራው ይከተለዋል፤ ዋጋውም ይገለጣል፤ ቅንነቱም ትነቃለች፤ ኀጢአቱም አታንቀላፋም። 36የቍርጥ ፍርድ ጕድጓድ በዕረፍት ቦታ አንጻር ይከፈታል። በደስታ ገነትም አንጻር እሳተ ገሃነም ይገለጣል። 37“ያንጊዜም ልዑል ከሙታን የተነሡ አሕዛብን፦ ‘እነሆ እዩ፤ የካዳችሁትም ማን እንደ ሆነ ዕወቁ፤ ያልተገዛችሁ ለማን ነው? የናቃችሁትስ የማንን ትእዛዝ ነው?” ይላቸዋል። 38እነሆ፥ ወደ ፊታችሁ እዩ፤ በወዲህ ደስታና ዕረፍት አለ፤ በወዲያም ፍርድና እሳት አለ።’ 39“ልዑል በፍርድ ቀን አሕዛብን እንዲህ ይላቸዋል፦ ‘የፍርድ ቀንስ እንዲህ ናት፤ ፀሐይ፥ ጨረቃም፥ ከዋክብትም የሉአትም። 40ደመናም፥ መብረቅም፥ ነጐድጓድም፥ ነፋስም፥ ውኃም፥ ሰማይም፥ ጨለማም፥ ሌሊትም፥ መዓልትም የሉአትም፤ 41ክረምት፥ በጋም፥ መከርም፥ ብርድም፥ ሐሩርም፥ ጥቅል ነፋስ፥ በረድ፥ ውርጭ፥ ጉም፥ ዝናም፥ ጠል የለባትም። 42ማታና ጧት፥ ብርሃንና ብልጭልጭታ፥ ፋናና መብራት፥ ሁሉ ለእርሱ የተጠበቀለትን ያይበት ዘንድ ከእግዚአብሔር ከጌትነቱ ብርሃን ብቻ በቀር ይህ ሁሉ የለም። 43የዚያች ሰዓት ርዝመቷ እንደ ሰባት ዓመት ይሆናል። 44ፍርዱም፥ ቅጣቱም ይህ ነው’ ይህንም ለአንተ ብቻ ነገርሁ።”
የሚድኑ ጥቂቶች ስለመሆናቸው
45እኔም እንዲህ አልሁት፥ “አሁንም አቤቱ፥ ትእዛዝህን ጠብቀው የኖሩ ብፁዓን ናቸው። 46ነገር ግን ስለ ጠየቅሁህ ነገር ከሕያዋን መካከል የማይበድል ማንነው? ከተወለደስ ወገን ሕግህን ያልተወ ማንነው? 47አሁንም በሚመጣው ዓለም ደስ ታሰኛቸው ዘንድ ያለህ ጻድቃን ጥቂት እንደ ሆኑ፥ የሚፈረድባቸውም ብዙዎች እንደ ሆኑ አያለሁ። 48ከዚህም ያሳተን፥ ወደ ጥፋትም የመራን፥ ወደ ሞት ጎዳናና ወደ ጥፋት መንገድም የወሰደን፥ ከዛሬ ጀምሮ ከእኛ ሕይወትን ያራቃት፥ ክፉ ልቡና በእኛ ጸንትዋልና። ይህም በተወለዱ ሁሉ ላይ ነው እንጂ በጥቂቶች ብቻ አይደለም።” 49መልአኩም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “ስማኝ ልንገርህ፤ ዳግመኛም አስተምርሃለሁ። 50ስለዚህ ነገር ልዑል ሁለት ዓለምን እንጂ አንድ ዓለምን ብቻ አልፈጠረም። 51አንተ ግን የጻድቃን ቍጥራቸው ጥቂት ነው፤ ብዙዎችም አይደሉም፤ የኃጥኣን ግን ቍጥራቸው ብዙ ነው ብለሃልና፥ 52እርሳሱን ከሸክላ ጋር ሥራ።” 53እኔም አልሁት፥ “አቤቱ፥ ይህ እንዴት ይቻለኛል።” 54እንዲህም አለኝ፥ “ይህን ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ምድርን ጠይቃት፤ ትነግርሃለችም፤ ተናገራት፤ ትመልስልሃለችም። 55እነሆ፥ ወርቁን፥ ብሩንም፥ ናሱንም፥ ብረቱንና እርሳሱን፥ ሸክላውንም አንቺ ታስገኚዋለሽ በላት። 56ብር ከወርቅ፥ ናስም ከብር፥ ብረትም ከናስ፥ እርሳስም ከብረት፥ ሸክላም ከእርሳስ ይበዛል። 57እንግዲህ አንተ ራስህ ዕወቅ፥ የትኛው ይከብራል? የትኛውስ ይወደዳል? የሚበዛው ነውን? ወይስ የሚያንሰው ነው?” 58እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “ጌታዬ ሆይ የሚያንሰው ይወደዳል፤ የሚበዛውም ይረክሳል።” 59እርሱም መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “ያሰብኸውን አንተ ራስህ መዝነው፤ ከብዙው ካለው ይልቅ፥ ከጥቂቱ ያለው እጅግ ደስ ይለዋልና ከእኔ ዘንድ የሚገኝ የጻድቃን ደስታቸው እንደዚሁ ነው። 60ስለሚድኑ ስለ ጥቂቶች ደስ ይለኛል፤ ክብሬን ያገኛሉና። ስሜም በእነርሱ ተመስግኖአልና። 61ስለሚጠፉ ስለ ብዙዎች ልቡናዬን አላሳዝነውም። እነርሱ ዛሬ በእሳት ተመስለዋልና፥ እንደ እሳት ነበልባልም ሆነዋልና፥ እንደ ጢስም ነድደውና ተንነው ጠፍተዋልና።”
የዕዝራ ልቅሶ
62እኔም መለስሁለት፤ እንዲህም አልሁት፥ “ምድር ሆይ እንዳንቺ ያለ ልዩ ፍጥረት ከመሬትሽ ለምን ተገኘ? 63ነገር ግን ክፉ ልቡና ከሚፈጠርልን ይልቅ ባይፈጠርልን በተሻለን ነበር። 64ክፉ ልብም ከእኛ ጋር ያድጋል፤ ስለ እርሱም ይፈረድብናል፤ ሳናውቀው እንጐዳለንና። 65የሰው ልጆች ያልቅሱ፤ የምድረ በዳ አውሬዎች ግን ደስ ይበላቸው፤ ከአዳም የተወለዱ ሁሉም ያልቅሱ፤ የእንስሳ መንጋዎችም ደስ ይበላቸው። 66የሚጠብቃቸው ቍርጥ ፍርድ ስለሌለ፥ ፍርድንም ገሃነምንም ስለማያውቁት፥ ከሞቱም በኋላ መነሣትን ተስፋ ስለማያደርጉ እነርሱ ከእኛ እጅግ ይሻላሉና። 67የምንነሣው ትንሣኤ ምን ይጠቅመናል? 68የተወለድን ሁሉ በኀጢአት ተሰጠምን፤ ዐመፅንም ተሞላን፤ በደላችንም ጸና። 69ከሞትን በኋላ ወደ ፍርድ ባንሄድ በተሻለን ነበር አልሁት።”