1እግዚአብሔር ያይደለህ አንተ ደካማ ሰው ሆይ! ለምን ትኰራለህ? ዛሬ ሰው ነህ፤ ነገም መሬትና ዐመድ ነህ፤ በመቃብርህም ትልና ብስባሽ ትሆናለህ። 2ዳግመኛም አንተንና የአንተን ሥራ የሚሠሩትን ሲኦል ትከተላቸዋለች፤ የአንተ መምህር አባታችን አዳምን ስለ አሳተ የዐለምን ሁሉ ኀጢአት ወደ ራሱ የሚመልስ ሰብልያኖስ ነውና፤ 3ራሱንም በማኵራትና ልቡናውን በማደንደን ለፈጣሪው ሥራ መስገድን እንቢ ብሏልና። 4አንተም እንደ መምህርህ ለፈጣሪህ ለእግዚአብሔር መስገድን እንቢ ብለሃል። 5አንተም ፈጣሪያቸው እግዚአብሔርን የማያውቁት የቀደሙህ እንደ ሄዱት ትሄዳለህ፤ 6በምድር ስለ ሠሩት ስለ ክፉ ሥራቸው እንደ ተበቀላቸውና ወደ ሲኦል እንደ ወረዱ፥ 7አንተም እንደ እነርሱ ወደ ገሃነም ትወርዳለህ። 8ቍጣውንም አነሣሥተሃልና፥ በአምስቱም መንግሥታት ላይ ሥልጣንን የሰጠህ እግዚአብሔርን ማምለክ ቸል ብለሃልና፥ ከእግዚአብሔር እጅ የምታመልጥ ይመስልሃልን? 9ፈቃዱንም ታደርግ እንደ ሆነ፥ አታደርግም እንደ ሆነ መረመረህ፤ በምድርም መንገድህን ብታሣምር እግዚአብሔር መንገድህን ያከናውንልሃል፤ እጅህንም ያኖርህበትን ሁሉ ያከናውንልሃል፤ ይባርክልሃልም፤ ጥንተ ጠላቶችህንና የዕለት ጠላቶችህንም ያስገዛልሃል። 10በመውጣትህና በመግባትህ፥ በሆድህም ፍሬ፥ በመንጋዎችህና በድልቦችህም፥ በጣቶችህም በአመለከትህበት ሥራ ሁሉ፥ በልብህም ባሰብኸው ሁሉ ደስ ይልሃል፤ እንዲህ ታደርግ ዘንድ፥ ትሠራና ትተክል፥ ታፈርስም ዘንድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሥልጣን ተሰጥቶሃልና ሁሉ ይታዘዝልሃል። 11ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃልና ሕግ መስማትን እንቢ ብትል፥ በፍርዱም ባትኖር ፍርዱ ሁሉ እውነት ነውና ከአንተ አስቀድሞ እንደ ነበሩ፥ በሚገባም እግዚአብሔርን እንደማያመልኩት፥ በቀና ፍርዱም ጸንተው እንዳላመኑ ወንጀለኞች ከእግዚአብሔር እጅ የምታመልጥበት የለም። 12ከፊቱም የሚሰወር የለም፤ ነገር ግን ሁሉ በፊቱ ፈጽሞ የተገለጠ ነው። 13የነገሥታቱን ሥልጣን የሚይዝና የኀይለኞችን ዙፋን የሚገለብጥ እርሱ ነው። 14የተዋረዱትንም ከፍ ከፍ የሚያደርግ፥ የወደቁትንም የሚያነሣ እርሱ ነው። 15የታሰሩትን የሚፈታ እርሱ ነው፤ የሞቱትንም የሚያስነሣ እርሱ ነው፤ የይቅርታ ጠል ከእርሱ ዘንድ ነውና ሥጋቸው የፈረሰና የበሰበሰ፥ እንደ ትቢያም የሆነ ሰዎችን በወደደ ጊዜ ያስነሣቸዋል። 16አሳዝነውታልና ክፉ ሥራ የሠሩ ሰዎችንም የደይን ትንሣኤን ያስነሣቸዋል፤ ይበቀላቸዋልም። 17በምድርም ዘራቸውን ያጠፋል፤ እነርሱ የእግዚአብሔርን ሕጉንና ሥርዐቱን ያፈረሱ ናቸውና፤ 18የጻድቃን መንገድ ከኃጥኣን መንገድ ይልቅ ጭንቅ ነውና ኃጥኣን በጻድቃን ምክር ይኖሩ ዘንድ አይወድዱም። 19ሰማይ ከምድር የራቀ እንደ ሆነ እንደዚሁ የጻድቃን መንገድ ከኀጥኣን መንገድ የራቀ ነው። 20የኃጥኣን መንገድ ግን የቅሚያና የክፋት፥ የዐመፅና የዝሙት፥ የስስትና የክዳት ነው፤ በዐመፅም መስከርና የሰውን ገንዘብ መቀማት ነው። 21የሰውን ደም ወደ ማፍሰስ ፈጥኖ መሔድ፥ በማይጠቅም ጥፋት ማድረግ፥ ድሃአደጉን ማስለቀስ፥ ደምንና ሞቶ ያደረውን መብላት፥ የግመልና የእሪያም ሥጋ መብላት፥ ወደ አራስና ሳትነጻ በደሟ ወዳለች ሴት መሔድ ነው። 22ይህም ሁሉ የኃጥኣን ሥራ ወደ ዘለዓለም ጥፋትና ቅጣት የሚወስድ ሰፊ መንገድና የተዘረጋ የሰይጣን ወጥመድ ነው። 23ጠባብና ቀጭን የምትሆን የጻድቃን ጎዳና ግን ወደ ሕይወት፥ ወደ የዋህነትና ወደ ትሕትናም፥ ወደ ፍቅርና ሰላም፥ ወደ ጾምና ጸሎት፥ ወደ ሥጋም ንጽሕና፥ ከማይጠቅም፥ አባላ የተመታውንና ሞቶ ያደረውን ከመብላት፥ ወደ ጐልማሳ ሚስት ከመሔድና ከዝሙትም ወደ መጠበቅ የምትወስድ ናት። 24ኀጢአተኞች ሰዎች ይኸን ሁሉ ያደርጋሉና በሕግ ከአልታዘዘ ከተጠላ ሥራ ሁሉና ርኩስ መብልን ከመብላት፥ እግዚአብሔርም ከማይወደው ሥራ ሁሉ ይጠበቃሉ። 25ጻድቃን እግዚአብሔር ከማይወደው መንገድ ሁሉ ይርቃሉ። 26እርሱም ይወድዳቸዋል፤ ከመከራቸውም ሁሉ እንደ አደራ ገንዘብ ይጠብቃቸዋል፤ ያድናቸዋልም። 27ኃጥኣንን ግን ሰይጣን ይገዛቸዋል። ሕጉንና ሥርዐቱን፥ የሚወደውንም ሁሉ ይጠብቃሉና።