1እናንተም ነገሥታቱና መኳንንቱ በሰይጣን ጎዳና አትሂዱ። ነገር ግን የፈጠራችሁን፥ እስከ ዛሬም ድረስ የጠበቃችሁን እግዚአብሔርን ፍሩት። 2ሁሉንም በሚገዛ በእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ ጸንታችሁ ኑሩ። 3የእስራኤል ልጆች የኬጤዎንንና የከናኔዎንን፥ የፌርዜዎንንም ሀገር ይወርሱ ዘንድ ወደ አማሌቅ በመጡ ጊዜ የሴፎር ልጅ ባላቅ፥ 4በለዓምን፥ “አንተ የረገምኸው የተረገመ፥ የመረቅኸውም የተመረቀ ነውና ትረግምልኝ ዘንድ ና፤ እኔም የሚያከብርህን ብዙ ወርቅና ብር እሰጥሃለሁ” ብሎታልና። 5በለዓምም የጥንቆላውን ዋጋ ተስፋ አድርጎ መጣ፤ የሴፎር ልጅ ባላቅም የእስራኤል ልጆች የሰፈሩበትን ቦታ አሳየው፤ 6ሟርቱንም አደረገ፤ መሥዋዕቱንም ሠዋ፤ የሰቡትንም ላሞችንና በጎችን አረደ፤ የእስራኤልንም ልጆች ይረግማቸው ዘንድ ወደደ። 7እግዚአብሔር ግን ይረግማቸው ዘንድ አልወደደም፤ ርግማንን ወደ ምርቃት በቃሉ መለሳት እንጂ። 8እንዲህም አለ፥ “አንተ እግዚአብሔር የመረጠው ሕዝብ ነህና፥ ከሰማይ የሚመጣ የፍቁር ማደሪያም ነህና የሚመርቁህ የተመረቁ ይሁኑ፤ የሚረግሙህም የተረገሙ ይሁኑ” አለ። 9ከዚህም በኋላ በፊቱ በመረቃቸው ጊዜ የሴፎር ልጅ ባላቅ አዘነ፤ ፈጽሞም ተቈጣ፤ ይረግማቸውም ዘንድ አዘዘ። 10በለዓምም፥ “እግዚአብሔር የመረቀው ወገን ወደዚህ ሀገር መጥትዋልና እግዚአብሔር የመረቃቸውን እኔ አልረግምም” አለው። 11የሴፎር ልጅ ባላቅም በለዓምን አለው፥ “እኔ ትረግምልኝ ዘንድ ወድጄ ነበር፤ አንተ ግን አልረገምኻቸውም፤ በፊቴም ፈጽመህ መረቅኻቸው፤ አንተም ብትረግምልኝና ስጠኝ ብትለኝ እኔ ቤት ሙሉ ወርቅና ብር በሰጠሁህ ነበር፤ አንተ ግን ፈጽመህ መረቅኻቸው፤ ለእኔም በጎ አላደረግህም፤ እኔም ለአንተ በጎ ነገር አላደርግም።” 12በለዓምም፥ “እግዚአብሔር በአንደበቴ ያደረገውን ቃል እርሱን እናገራለሁ እንጂ እኔስ የእግዚአብሔርን ቃል ቸል ማለትና መተላለፍ አልችልም። 13እኔስ ከነፍሴ ገንዘብን አልወድድም፤ ገንዘብን ብወድ የተመረቀ ወገንን እንዳልረግም እግዚአብሔር ይቈጣኛልና” አለ። 14እግዚአብሔር አባታቸው ያዕቆብን፥ “የሚመርቁህ የተመረቁ ይሁኑ፤ የሚረግሙህም የተረገሙ ይሁኑ” ብሎታልና፤ 15የሚመርቅህም ሁሉ የተመረቀ ነው፤ ያለ ፍርድም የሚረግምህ የተረገመ ነው፤ እግዚአብሔር አንተን ይወድህ ዘንድ ጎዳናህንና ሥራህን አከናውን። 16እግዚአብሔርንም በክፋታቸው እንዳሳዘኑት፥ እርሱም ቸል እንዳላቸው እንደ ቀደሙ ሰዎች አትሁን፤ በጥፋት ውኃም ያጠፋቸው አሉ። 17በጠላቶቻቸውም እጅ ያጠፋቸው አሉ፤ መከራ ያጸኑባቸው ክፉዎች ጠላቶችን አምጥቶ ነገሥቶቻቸውን ከካህናቶቻቸውና ከነቢያቶቻቸው ጋራ ማረኳቸው። 18ወደማያውቁት ወደ ባዕድ ሀገርም አደረሷቸው፤ ፈጽመውም ማረኳቸው፤ ገረፉአቸውም፤ ሀገራቸውንም አጠፉ። 19የቅድስቲቱን ከተማ አጥሯንና ቅጥሯን አፍርሰዋልና ኢየሩሳሌምን እንደ እርሻ አደረጓት። 20ካህናቱም ተማረኩ፤ ሕጉም ፈረሰ፤ አርበኞችም በጦር ወደቁ። 21ባልቴቶችም ተማረኩ፤ ለሞቱ ባሎቻቸውም አላለቀሱም፤ ተማርከዋልና ለራሳቸው አለቀሱ፤ 22ሕፃናትም አለቀሱ፤ ሽማግሎችም አፈሩ፤ የሽማግሌውንና የሽበታሙን ፊት አልራሩም። 23ለቆንጆዎችና በሕግ ላሉም አልራሩም፤ በአገራቸው ያገኙትንም ሁሉ አጠፉ፤ ቤተ መቅደስን አስቀድሞ ያፈርስ ዘንድ በወደደ ጊዜ እግዚአብሔር ወገኖቹን ተቈጥትዋልና ወደማያውቁት ወደ ባዕድ ሀገር ማርከው ወሰዷቸው። 24ስለዚህም እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች ቸል ባላቸው ጊዜ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንደ እርሻ እንድትታረስ አደረጋት፤ ሁልጊዜ ፈጣሪያቸውን ያሳዝኑታልና። 25እርሱ ግን በምንም አንድ ጊዜ አላጠፋቸውም፤ ስለ አባቶቻቸው ይራራላቸዋልና የሚራራላቸው ስለ ራሳቸው አይደለም። በእውነት የነገሡ፥ በፈጣሪያቸውም ፊት በቀና ሕግ ጸንተው የኖሩ አባቶቻቸውን አብርሃምንና ይስሐቅን ያዕቆብንም ይወዳቸዋልና ነው እንጂ። 26እርሱም እጥፍ በሆነ ክብር ላይ ሾማቸው፤ በሰማይና በምድር ያለ ሁለት መንግሥትንም አገኙ። 27እንዲሁም በሚያልፍ በዚህ ዓለም የምትኖሩ እናንተ ነገሥታቱና መኳንንቱ በሚገባ ሥራ ጸንተው የኖሩ ከእናንተ አስቀድሞ የነበሩ አባቶቻችሁ መንግሥተ ሰማያትን እንደ ወረሱ፥ ስማቸው ለልጅ ልጅ ያማረ እንደ ሆነ አስቧቸው። 28አንተም መንግሥትህን ያቀናልህ ዘንድ መልካም አኑዋኑዋራቸው እግዚአብሔርን እንዳገለገሉት ከአንተ አስቀድሞ እንደ ነበሩ እንደ ደጋጎች ነገሥታት ስምህን መልካም ያደርግልህ ዘንድ ሥራህን አቅና።