1የእግዚአብሔርን ሰው ሙሴን አስበው፤ በጸሎቱና በትሕትናው ይህን ያህል ሕዝቡን ሲጠብቅ አልተበሳጨም፥ አላጠፋምም፤ ነገር ግን ላሙትና እግዚአብሔርም በአንድ ጊዜ ያጠፋቸው ዘንድ ለወደደ ለወንድሙና ለእኅቱ በየዋህነቱ በእግዚአብሔር ዘንድ ኀጢአታቸውን እንዲህ ሲል አስተሰረየላቸው፥ “አቤቱ ወገኖችህ በፊትህ በድለዋልና ወገኖችህን ይቅር በል፤ ቸልም አትበል፥ 2በፊትህ በድያለሁና ኀጢአተኛ የምሆን እኔን ባርያህን ይቅር በለኝ፤ አንተ መሓሪ ነህና፥ ይቅር ባይም ነህና ለእነርሱም አስተስርይላቸው።” 3እንደዚህም ሙሴ ለአሙት አስተሰረየላቸው። 4ስለዚህም የዋህ ተባለ። 5እግዚአብሔርም ከወንድሞቹ ከሌዋውያኑ ልጆች ሁሉ ይልቅ እጅግ ወደደው፤ ካህናቱንም ይሾማቸዋልና በእነርሱ ዘንድ እንደ እግዚአብሔር አስመሰለው። 6የተደፋፈሩ የቆሬን ልጆች ግን በምድር በታች አሰጠማቸው፤ በሥጋና በነፍስ ሕያዋን ሳሉ ከከብቶቻቸውና ከድንኳኖቻቸው ጋራ ወደ ሲኦል አወረዳቸው፤ ፈጣሪው እግዚአብሔርን ወድዶታልና ከትእዛዙም አልወጣምና የተናገረው ቃል ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይደረግለት ነበር። 7አንተም እንዲሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባትተላለፍ እግዚአብሔር ፈቃድህን ያደርግልሃል፤ ነገርህንም ይወድልሃል፤ መንግሥትህንም ይጠብቅልሃል። 8ከሙሴ ትእዛዝ የወጡ የቆሬና የአሳፍ ልጆችም ለእግዚአብሔር ልቡናችሁን አቅኑ ስላላቸው በእርሱ አንጐራጐሩ። 9“እኛስ በምስክሩ ድንኳን የክህነት ሥራ የምንሠራ የሌዊ ልጆች አይደለንምን?” አሉት። 10ያጥኑም ዘንድ ጥናቸውን ያዙ፤ ሄደውም አጠኑ፤ እግዚአብሔር ግን ጸሎታቸውን አልተቀበለም፤ በጥናቸው እሳትም ተቃጠሉ፤ በእሳት እንደሚቀልጥ ሰምም ቀለጡ፤ ከእነርሱም አንድ ሰው ስንኳ አልቀረም፤ “በሰውነታቸው መቃጠል ጥናቸው ከብሯል” ብሏልና በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ ከገቡት ከጥናቸው በቀር ልብሶቻቸውና አጥንቶቻቸው አልቀሩም። 11ስለዚህም እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፥ “ጥናቸውን ወደ ድንኳን ሰብስቡ፤ ከውጭ ጀምሮ እስከ ውስጥ ድረስ ሁሉን ላዘጋጀሁለት ለቤቴ መሣሪያ ይሁን።” 12የተቀደሰች የድንኳንዋንም መሣሪያ አዘጋጀ፤ መክደኛውንና ቀለበቱን፥ የኪሩቤልን ሥዕልና ባሕሩን አዘጋጀ። 13ሰኑንና መጋረጃውን፥ ስክተቱንና የድንኳኑን ዙሪያ ዕድሞ፥ ጋኖችንና በምስክሩ ድንኳን የሚሠዉበት መሠዊያውን ሠራ። 14የፈቃዱን መሥዋዕትና የሰላሙን መሥዋዕት፥ የስእለቱንና የኀጢአቱን መሥዋዕት፥ የማታውንና የጧቱንም መሥዋዕት ሠዉ። 15ሥራ ይሠሩባት ዘንድ በምስክሩ ድንኳን ለሙሴ ያዘዘውን ሁሉ አዘዛቸው። 16ማርና ወተትን የምታስገኝ፥ ለአብርሃም የማለለትን፥ ያባቶቻቸውን ርስት ይሰጣቸው ዘንድ ተስፋ በሰጣቸው በፈጣሪያቸው በእግዚአብሔር በሕጉ ድንኳን ውስጥ ስሙ በእነርሱ ይመሰገን ዘንድ ለአምላካቸው መገዛትን አላቃለሉም። 17ለይስሐቅ ማለለት፤ ለያዕቆብም አምልኮቱን አጸናለት። 18በምስክሩ ድንኳንም ለሙሴና ለአሮን አጸናላቸው፥ 19በኢየሩሳሌም በድንኳኑና ሰሎሞን በሠራው ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔር ማደሪያ፥ የልዑልም የስሙ ማረፊያ፥ የእስራኤልም ቅዱስ ማደሪያ እስኪሆን ድረስ ለሳሙኤልና ለኤልያስ አምልኮቱን አጸናላቸው። 20በየዋህነት ለሚኖሩ ለካህናቱ የሚገለጥባት መለመኛና የኀጢአት ማስተስረያ ናትና። 21ፈቃዱንም ለሚያደርጉ ሰዎች ልመናቸውን የሚሰማባት ቦታ ናት። 22የእስራኤልም ቅዱስ የእግዚአብሔር ሕጉ የሚሠራባት ናትና። 23ለእስራኤል ቅዱስ ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ ሊሆን መሥዋዕት የሚሠዋባት፥ ዕጣንም የሚታጠንባት ናትና። 24በምስክሩ ድንኳን ውስጥም ይቅር በሚልበት በመክደኛው ላይ ሆኖ ይናገር ነበር፤ ለመረጣቸው ለያዕቆብ ልጆች፥ በእግዚአብሔር በሕጉና በትእዛዙ ጸንተው ለሚኖሩ ለቅዱሳኑም የእግዚአብሔር ብርሃኑ ይገለጥላቸው ነበር። 25የሚገዳደሩ ግን ምድር እንዳሰጠመቻቸው እንደ ቆሬ ልጆች ይሆናሉ፤ እንዲሁም ኃጥኣን እስከ ዘለዓለም ድረስ መውጫ ወደሌላት ወደ ገሃነም እሳት ይገቡ ዘንድ አላቸው።