1በድንኳኑ ውስጥ ያዘዛችሁን ያልጠበቃችሁ፥ ከራሳችሁም ፈቃድ በቀር ፈቃዱን ያላደረጋችሁ የእስራኤል ኀያላን ወዮላችሁ! ይኸውም ትዕቢትና ትዝኅርት፥ ዝሙትና ስስት፥ ስካርና መጠጥ፥ በሐሰትም መማል ነው። 2ስለዚህም ቍጣዬ በእሳት ፊት እንደ አለ ገለባ በእናንተ ላይ ይነድዳል፤ ተራራውንም እንደሚያቃጥል እሳት፥ የደቀቀውንም ትቢያ ከምድር አፍሶ ከሥራው የተነሣ ፍለጋው ወደማይገኝበት ወደ ሰማይ እንደሚበትነው፥ እንደ ዐውሎ ነፋስ፥ 3እንዲሁ ክፋትን የሚሠሩአትን ሁሉ አጠፋቸዋለሁ ይላል የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር። ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔርንም አስቡት፤ የሚሳነውም የለም። 4የሚወድዱትንም ይወድዳቸዋል፤ በትእዛዙም የሚሄዱትን በደላቸውንና ኀጢአታቸውን ያስተሰርይላቸዋል፤ በአለማመንም ደንቆሮዎችና የልብ ፈዛዞች አትሁኑ። 5ልቡናችሁንም ለእግዚአብሔር የቀና አድርጉ፤ ነፍሳችሁን ታድኑ ዘንድ በእርሱ እመኑ፤ በመከራችሁም ቀን ከጠላታችሁ እጅ አድናችኋለሁ። 6በምትጠሩኝም ጊዜ እነሆ ከእናንተ ጋር አለሁ እላችኋለሁ፤ ከጠላቶቻችሁም እጅ አድናችኋለሁ፤ በእኔም አምናችኋልና፥ ትእዛዜንም አድርጋችኋልና፥ ከሕጌም አልወጣችሁምና፥ እኔ የምወደውን ወዳችኋልና በመከራችሁ ቀን ቸል አልላችሁም ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር። 7የሚወድዱትንም ይወድዳቸዋል፤ ርኅሩህና ይቅር ባይ ነውና፥ ትእዛዙን የሚጠብቁትን ይጠብቃቸዋል። 8ቍጣውንም ብዙ ጊዜ ይመልስላቸዋል፤ ሥጋዊና ደማዊ እንደ ሆኑ የሚያውቃቸው ስለ ሆነ ይቅር ባይ ነውና፥ በመቅሠፍቱ ሁሉ አያጠፋም፤ ነፍሳቸውም ከሥጋቸው በተለየች ጊዜ ወደ መሬትነታቸው ይመለሳሉ። 9ካለመኖር ፈጥሯቸዋልና፥ ካለመኖር ያመጣቸው ዘንድ እግዚአብሔር እስኪወድ ድረስ የሚኖሩበትን ቦታ አያውቁም፤ ዳግመኛም እርሱ ነፍሳቸውን ወሰደ፤ የመሬት ባሕርይንም ወደ መሬትነቱ መለሰ። 10ዳግመኛም ፈቃዱ ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣቸዋል። 11እግዚአብሔርን የካደ ጺሩጻይዳን ግን በእግዚአብሔር ፊት መታበይን አበዛ፤ እስከ ወደደባትም ቀን ድረስ በተወው ጊዜ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ። 12እንዲህም አለ፥ “ዘመኔ እንደ ሰማይ ዘመን ሆነ፤ ፀሐይንም የማወጣ እኔ ነኝ፤ እስከ ዘለዓለምም ድረስ አልሞትም።” 13ይህንም ነገር ተናግሮ ሳይጨርስ ስሙ ጥልምያኮስ የሚባል መልአከ ሞት ወርዶ ልቡን መታው፤ በዚያችም ሰዓት ሞተ፤ ፈጣሪውን አላመሰገነውምና ከትዕቢቱ ብዛት፥ ከሥራውም ክፋት የተነሣ ከአማረ ኑሮው ተለይቶ ጠፋ። 14የከለዳውያን ንጉሥ ሠራዊት ግን ሊወጉት ወድደው፥ ከከተማውና ከአገሩ አደባባይ ውጭ ሰፍረው ሳሉ በሞተ ጊዜ ወጥተው ሀገሩን አጠፉ፤ ከብቱንም ሁሉ ዘረፉ፤ ከቅጥር እስከሚጠጋ ወንድ ድረስ አላስቀሩም። 15ገንዘቡን ሁሉ ዘረፉ፤ ቈሳቍሱንም ወሰዱ፤ ከተማውንም በእሳት አቃጥለው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።