1የአመኑ እሊያ አምስቱ የመቃቢስ ልጆች ግን ለጣዖት የተሠዋውን መሥዋዕት መብላትን እንቢ ብለው ሰውነታቸውን ለሞት ሰጡ። 2ይህ ዓለም እንደሚያረጅና እንደሚያልፍ፥ ተድላውም ለዘለዓለም እንደማይኖር ዐውቀው በሰማይ ከአለው እሳት ይድኑ ዘንድ ሰውነታቸውን ለእሳት ሰጡ። 3ሰውን ከመገዳደር እግዚአብሔርን መገዳደር እንደሚከፋ፥ ከንጉሥም ቍጣ የእግዚአብሔር ቍጣ እንደሚከፋ አውቀዋልና። 4“አቤቱ፥ በምድር ላይ ብዙ ዘመን ከመኖር በገነት አንዲት ቀን ደስ መሰኘት ይሻላል፤ ከብዙ ዘመኖችም የአንዲት ሰዓት ይቅርታህ ይሻላል፤ 5የእኛ የሰዎች ዘመናችን ምንድን ነው? እንደ ጥላ የሚያልፍ፥ በእሳት ዳርም እንደ አለ ሰም አይደለምን? 6አቤቱ አንተ ግን ለዘለዓለም ትኖራለህ፤ ዘመንህም የማይፈጸም ነው፤ ስም አጠራርህም ለልጅ ልጅ ነው።” 7የመቃቢስ ልጆችም ይኸንና የሚመስለውን ሁሉ ዘመሩ፤ በእግዚአብሔር መታመንን መረጡ፤ ርኩስ መሥዋዕትን መብላትንም እንቢ አሉ፤ 8ስለዚህም ሙታን እንደሚነሡ፥ ከትንሣኤም በኋላ ፍርድ እንደሚፈረድ ዐውቀው ስለ እግዚአብሔር ብለው ሰውነታቸውን ለሰማዕትነት ሰጡ። 9የሙታንን ትንሣኤ የማታውቁና የማታምኑ ሰዎች! ከዚች ከምታልፍ ከምድራዊት ሕይወታቸው ይልቅ ኋለኛዪቱ ሕይወታቸው እንደምትበልጥ ዐውቀው ሰውነታቸውን በአንድነት ለሞት ከሰጡና ወንድማማችነታቸው ከአማረ ከእነዚህ ከአምስቱ ሰዎች የተነሣ ዕወቁ፤ 10ሁሉ እንዲያልፍ ዐውቀው ስላመኑበት፥ ለጣዖትም ስላልሰገዱ፥ የሞተውንና የረከሰውንም መሥዋዕት ስላልበሉ፥ ከእግዚአብሔር ምስጋናን ያገኙ ዘንድ ሰውነታቸውን ለሞት ሰጡ። 11ስለዚህም በኋለኛዪቱ ቀን በነፍስና በሥጋ ደስ እንደሚያሰኛቸው ዐውቀው ሚስትና ልጆች እያሏቸው የዚህን ዓለም ጣዕምና የሞትን ምሬት አላወቁም፤ በኋለኛዪቱም ቀን በነፍስና በሥጋ ትንሣኤ እንዲደረግ ዐውቀው ሰውነታቸውን ለሞት ሰጡ። 12የእግዚአብሔርን ሥርዐት የጠበቁ ሕማምና ኀዘን፥ ሞትም በሌለበት በሚመጣው ዓለም ለልጅ ልጅና ለረጅም ዘመን፥ 13የእግዚአብሔርን ቃል ከአመኑ ደጋግ ነገሥታትና መኳንንት ጋር እንደሚነግሡ ዐውቀው፥ ኋላም የሚደረገውን በልቡናቸው አይተው፥ በእሳት መካከል እንደ ሰም ሰውነታቸውን ለሞት ሰጡ። 14ፊታቸውም ከፀሐይ ሰባት እጅ እንደሚያበራ፥ ሁሉም በነፍስና በሥጋ በሚነሣ ጊዜ በፍቅሩ ደስ እንደሚላቸው ተስፋ አድርገው ሰውነታቸውን ለሞት ሰጡ።