1የአይሁድና የሳምራውያን፥ የፈሪሳውያንና የሙታንን ትንሣኤ የማያምኑ የሰዱቃውያን ነገር እኔን እጅግ ያሳዝነኛል፤ ልቡናዬም ያውቀዋል። አይሁድ፦ እንብላ፤ እንጠጣም፤ ነገም እንሞታለን፤ በዚያም የምናየው የለም ይላሉ። 2ሳምራውያን ግን ሥጋችን ትቢያ ይሆናልና አይነሣም ይላሉ። 3ትንሣኤም በተደረገ ጊዜ የነፍሳችንን መነሣት እናምናለን። ነፍስ እንደ ነፋስ የማትታይና እንደ ነጐድጓድ ድምፅ ስለ ሆነች እነሆ እዚህ አለች የማይሏትና የማትታይ ስለ ሆነች ሥጋ ቢሞት አትሞትምና። 4ሥጋችን ግን በሁሉ ትታያለች፤ ዐመድና ትቢያም ትሆናለች። አውሬዎች ይበሏታልና፥ ትሎችም በመቃብር ይበሏታልና። 5እነዚያም የበሏት እንደ ሣር ይሆናሉና፥ እንዳልተፈጠሩም ትቢያ ይሆናሉና ዐመድ ይሆናሉ፤ ፍለጋቸውም አይገኝም። የፈረሱ ሥጋዎች የት ይገኛሉ? 6ፈሪሳውያንም እንዲህ ይላሉ፥ “የሙታንን መነሣት እናምናለን፤ ነገር ግን ነፍሳትን በምድር ያይደለ በሰማያት ሌላ ሥጋ ያለብሳቸዋል።” 7ሰዱቃውያንም እንዲህ ይላሉ፥ “ነፍሳችን ከሥጋችን ከወጣች በኋላ ከሞት አንነሣም፤ ለነፍስና ለሥጋም ትንሣኤ የላቸውም፤ ከሞትንም በኋላ አንነሣም።” 8ስለዚህም እጅግ ፈጽመው ይስታሉ፤ በእግዚአብሔርና በጌትነቱም ላይ ጽርፈትን ይናገራሉና የእነርሱ ነገር ያሳዝነኛል። 9የሚያጸድቃቸው እግዚአብሔርንም አላመኑትምና ለመዳን ተስፋ የላቸውም፤ ለመዳንና ከሙታን ለመነሣትም ተስፋ የላቸውም። 10አንተ ዕውር አይሁዳዊ ካለመኖር የፈጠረህን፥ እንደ ምራቅም ስትሆን ሰው ያደረገህን እግዚአብሔርን አላዋቂ ታደርገዋለህን? በምሳሌውና በመልኩ የፈጠረህ ነፍስህንና ሥጋህን አዋሕዶ ማስነሣት ይሳነዋልን? 11ከእግዚአብሔር እጅ አታመልጥምና እንደዚህ አታስብ፤ ሳትወድ ትነሣለህ፤ በሞትህም ጊዜ የተያዝህባት የሲኦል ገመድ በአንገትህ አለችና ሳትወድ ይፈረድብሃል። 12በአንገትህ የታሠረች ያች ገመድም በእናትህ ማኅፀን ከሲኦል ግንድ ለአንተ ትበቅላለችና። አንተም ባደግህ ጊዜ እርሷም ታድጋለችና። 13አንተም በሞትህ ጊዜ በአንገትህ ያኖሯታል፤ ግንዷንም በሳቧት ጊዜ እርስዋ ታመጣቸዋለች፤ ቅርንጫፎችዋንም ትስባለች። 14ኃጥኣን ሁሉ በአንገታቸው ገመድ እንዳለ በውስጧ ተይዘው አሉና። 15የኃጥኣንም ነፍሳት ሁሉ ከአሉበት ከሰማይ ዳርቻ ይመጣሉ፤ እንደዚሁም ገመድህ ነፍስህን ካለህበት ስባ አምጥታ ወደ ሲኦል ታገባሃለች። 16ሥጋህም ከነፍስህ ከተለየ በኋላ እንደ አባታችን እንደ አዳም ሥጋ ፍጹም ሆኖ በእግዚአብሔር በቸርነቱ ጠል ይነሣል። በዚያም በደልንና ኀጢአትን እንደ ሠራህ እንደ አለማመንህ ፍዳህን ትቀበላለህ። 17ሌላውን ብቻ የምታስት አይምሰልህ፤ ራስህም ትስታለህ፥ በስሕተትህም በመቃብር ትኖራለህ፤ ከእግዚአብሔርም ትእዛዝ ወጥተው ይስቱ ዘንድ የሙታን ትንሣኤ የለም ትላለህ። 18እንደ ሠራኸው ሥራህ ፍዳህን ይሰጥህ ዘንድ ያስነሣሃል እንጂ በትቢያና በዐመድ ውስጥ ማን ይተውሃል? 19ያንጊዜ ግን በነፋስ ውስጥ ያለ ነፋስ ባሕርይህም ቢሆን፥ በውኃ ውስጥ ያለ ውኃ ባሕርይህም ቢሆን፤ በመሬት ያለ መሬት ባሕርይህም ቢሆን፥ በእሳትም ውስጥ ያለ እሳት ባሕርይህም ቢሆን ይመጣል። 20በአንተ ያደረች፥ በጨለማ ቦታ የምትኖር ነፍስም ብትሆን ትመጣለች። 21በገነት በደስታ የሚኖሩ የጻድቃን ነፍሳትም ይመጣሉ። 22አንተም አይሁዳዊ፥ አንተም ሳምራዊ፥ አንተም ፈሪሳዊ፥ አንተም ሰዱቃዊ እስኪፈረድብህ ድረስ በጨለማ ትኖራለህ። 23ያንጊዜም ሰውን ስለ አሳትህ እንደ ሥራህ እግዚአብሔር እንደሚከፍልህ ታያለህ። 24እንዲህም ትላቸዋለህ፦ የሞቱ ሰዎች አይነሡም፤ ነገ እንሞታለንና እንብላ፤ እንጠጣም፤ በሙሴም ወንበር ተቀምጠህ በቃልህ የሙታን ትንሣኤ የለም ትላለህ። 25ስለዚህም የኦሪትን መጽሐፍ እያወቅህ፥ የመጻሕፍትንም ቃል እያስተማርህ ሳትህ፤ ሰውን ከምታስት ሳትማር በቀረህ ይሻል ነበር። 26በክፉ ትምህርትህና በማይጠቅም ቃልህ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከምታስክድ የመጻሕፍትን ቃል በአላወቅህ ይሻልህ ነበር። 27አንተ ግን እንደ ሥራህና እንደ ከንፈርህ ፍሬ ይሰጥሃል፤ እግዚአብሔር ፊት አይቶ አያዳላምና፥ በጎ ሥራንም ለሚያስተምሩ ለወዳጆቹ ከአዘጋጀው ጸጋ ይሰጣቸዋልና። 28አንተም ከሚፈረድብህ ከእግዚአብሔር እጅ የምታመልጥበት የለም፤ እንደ ሥራህም ይከፍልህ ዘንድ አለው፤ አንተና ያስተማርሃቸውም በአንድነት ይፈረድባችኋል። 29ሙታን እንደሚነሡም ዕወቅ፤ ሕጉን የጠበቁ ቢሆኑም ይነሣሉ፤ በመቃብር መቈየት አይችሉም፤ ዝናም በዘነመ ጊዜ ምድር ሣርን እንደምታወጣ ትእዛዙ ያወጣቸዋልና። 30ዝናም ምድርን ባጠገባት ጊዜ ርጥብ እንጨት ቅጠልን እንደምታወጣ፥ ስንዴም ፍሬን እንደምታፈራ፥ እህልም ዝርዝርን እንደምታስገኝ፥ እግዚአብሔርም ከወደደ ፍሬዋን ትከለክል ዘንድ እንደማትችል፥ 31የፀነሰችም ሴት ምጥ በያዛት ጊዜ ማኅፀኗን መዝጋት፥ ሳትወልድም ማምለጥ እንደማትችል። 32ምድርም እንደዚሁ በእርስዋ የተሰበሰቡትን ታወጣለች፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ከሰማች በኋላ ማኅፀንዋን መዝጋት አትችልም፥ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የታዘዘ ጠል ወደ እርስዋ ይወርዳልና በአንድ ጊዜ ትወልዳቸዋለች። 33ሥጋዎችም ሬሳዎቻቸው በወደቁባቸው ቦታዎች ይሰበሰባሉ፤ የነፍሳት መዛግብት ቤቶችም ይከፈታሉ፤ ነፍሳትም ቀድሞ ወደ ተለዩበት ወደ ሥጋ ይመለሳሉ። 34መለከትም በተነፋ ጊዜ ሙታን እንደ ዐይን ጥቅሻ ይነሣሉ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ይቆማሉ፥ እንደ እጃቸውም ሥራ ይሰጣቸዋል። 35ያንጊዜም ከሙታን ጋራ እንደምትነሣ ታያለህ፤ በምድር ላይ የሠራኸውንም ሥራ ሁሉ ታደንቃለህ፤ በዐይኖችህም ፊት ተጽፈው ባየሃቸው ጊዜ ያንጊዜ የማይረባ ጸጸትን ትጸጸታለህ። 36ከሙታን ጋራም እንደምትነሣ፥ እንደ ሠራኸውም ሥራ እንደምትቀበል ታውቃለህ።