1በጎ ሥራቸውን ያገኙ ያንጊዜ ደስ ይላቸዋል፤ ሙታን አይነሡም እያሉ ቸል ያሉ ግን ሙታን ከማይጠቅም ክፉ ሥራቸው ጋራ እንደ ተነሡ በአዩ ጊዜ ያንጊዜ ያዝናሉ። 2ያም የሠሩት ሥራቸው ይፈርድባቸዋል፤ የሚከራከራቸውም ሳይኖር እንደሚፈረድባቸው እነርሱ ራሳቸው ያውቃሉ። 3በልቅሶና በፍርድ ቀን በቍርጥ ፍርድ ቀንና በእግዚአብሔር ቀን ዝንጉዎች በሚቆሙበት ቦታ ይቆማሉ። 4በፍጹም ጨለማ ቀን፥ በጉም ቀን፥ በብልጭልጭታ ቀን፥ በመብረቅ ቀን፥ 5በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ ቀን፥ በብርድና በሙቀት ቀን፥ በውርጭም ቀን፥ 6ክፉ ሰው ክፋትን እንደ ሠራ ፍዳን በሚቀበልባት ቀን፥ ንጹሕ ሰውም ንጹሕ ሥራን እንደ ሠራ ዋጋውን በሚቀበልባት ቀን፥ ኀጢአተኛም ኀጢአትን እንደ ሠራ ፍዳውን እንደሚቀበል፥ 7ጌታም ከባርያው በማይከብርባት ቀን፥ እመቤትም ከባርያዋ በማትከብርበት ጊዜ፥ 8ንጉሡም ከድሃው በማይከብርበት ጊዜ፥ ሽማግሌውም ከሕፃኑ በማይከብርበት ጊዜ፥ አባት ከልጁ በማይከብርበት ጊዜ፥ እናትም ከልጅዋ በማትከብርበት ጊዜ፥ 9ባለጸጋው ከድሃው በማይከብርበት ጊዜ፥ ትዕቢተኛም ከተዋረደው ሰው በማይከብርበት ጊዜ፥ ታላቁም ከታናሹ በማይከብርበት ጊዜ፥ የፍርድ ቀን ናትና፥ የፍዳና የቅጣት ቀን ናትና፥ ሁሉም እንደ ሠራው የሚቀበልባት ቀን ናትና። 10በጎ ሥራ የሠሩም ዋጋቸውን የሚቀበሉባት ቀን ናትና፥ ክፉ የሠሩም ክፉውን የሚቀበሉባት ቀን ናትና። 11ዋጋቸውን ያገኙም ደስ የሚሰኙባት ቀን ናትና፥ ክፉውንም የተቀበሉ የሚያዝኑባት ቀን ናትና። ሙታን አይነሡም እያሉ መጻሕፍትን የሚያሳብሉትም ያያሉ። 12ያንጊዜም የምድር ኃጥኣን ስለ ሠሩት ኀጢአታቸውና በምድር ሳሉ መልካም ባለማድረጋቸው ስለሚያገኛቸው መረጋጋት ስለሌለው ኀዘናቸው ያለቅሳሉ። 13እንደዚሁም በምድር ላይ ሳሉ በጎ ሥራን ሠርተዋልና በጎ ሥራን የሠሩ የደጋጎች ደስታ እስከ ዘለዓለም ድረስ አይፈጸምም። 14ከሞትም እንደሚነሡ አውቀዋልና ከፈጣሪያቸው ሕግ አልወጡም። 15ከትእዛዙም ስላልወጡ ሁለት ሕይወትን ይወርሳሉ፤ በምድርም ላይ ዘራቸውን አበዛ፤ ልጆቻቸውንም ባረካቸው። 16በሰማያትም በትንሣኤ ቀን ባለጸጎች በሚደኸዩበት ጊዜ ለአባቶቻቸው የማለላቸውን መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳቸዋል። 17ክፉ የሚሠሩና የሙታንን መነሣት የማያምኑ፥ የእግዚአብሔርን ሕግና የትንሣኤንም ቀን የማያስቡ ያለቅሳሉ። 18ያንጊዜም መጨረሻ የሌላት፥ ድኅነትና መረጋጋት የሌለባት የምታገኛቸውን መከራ ያያሉ፤ በልቡናቸውም መረጋጋትና ዕረፍት የሌለው ኀዘን ይሆናል። 19የማያንቀላፋ ትል፥ የማይጠፋም እሳት ያገኛቸዋል። 20ሥጋቸውም ባለበት ቦታ እሳትና ድኝ፥ ጥቅል ነፋስ፥ ውርጭና በረድ፥ ቀቅም በላያቸው ይዘንማል። 21የሙታንንም መነሣት በማያምኑ ሰዎች ላይ ገሃነመ እሳት አለባቸው።