1በሥጋህ፥ በእጅህና በእግርህ ጥፍር፥ በራስህም ጠጕር ያለውን እስኪ አንተ ራስህ አስበው፤ በቈረጥሃቸው ጊዜ ፈጥነው ይወጣሉና፥ ለማመን ልብና አእምሮ ከአለህ በዚህ ዕወቅ። 2እነዚህ የእጅህና የእግርህ ጥፍር፥ የራስም ጠጕር ከወዴት ይወጣሉ ትላለህ? ከሞት እንደምትነሣ ታውቅ ዘንድ በሌላ ሥጋ ያይደለ በአንተ ሥጋ የሚደረግ ትንሣኤን እንድታውቅ ይበቅሉ ዘንድ እግዚአብሔር ያዘጋጀው አይደለምን? 3አንተም የሙታን ትንሣኤ የለም እያልህ ሕዝቡን ስለአሳትህ ኀጢአትንና በደልን እንደ ሠራህ በሙታን ትንሣኤ ጊዜ ፍዳህን ትቀበላለህ። 4አሁንም የፍዳህ ቀን በደረሰችብህ ጊዜ ታያታለህ፤ ስንዴም ቢሆን፥ ገብስም ቢሆን አንተ ስንኳ የዘራኸው ይበቅል ዘንድ እንቢ አይልምና። 5ዳግመኛም አንተ የተከልኸው ተክል አልበቅልም አይልም፤ የወይን ተክልም ቢሆን፥ የበለስ ተክልም ቢሆን ቅጠሉና ፍሬው አይለወጥም። 6ወይን ብትተክልም በለስ ይሆን ዘንድ አይለወጥም፤ በለስም ብትተክል ወይን ይሆን ዘንድ አይለወጥም፤ ስንዴም ብትዘራ ገብስ ይሆን ዘንድ አይለወጥም፤ 7ገብስም ብትዘራ ስንዴ ይሆን ዘንድ አይለወጥም። ነገር ግን ሁሉ በየዘሩና በየወገኑ፥ በየፍሬውና በየእንጨቱ፥ በየቅጠሉና በየሥሩ፥ ከእግዚአብሔር በሚገኝ የምሕረት ጠል በረከትን ተቀብሎ ፍሬን ያወጣል። 8እንደዚሁም ምድር እግዚአብሔር እንደ ዘራባት ነፍስንና ሥጋን ታስገኛለች፤ እግዚአብሔር የዘራቸው ሥጋና ነፍስ ተዋሕደው ይነሣሉ እንጂ በጎ ሥራ የሠሩ ሰዎች ክፉ ሥራ በሠሩ ሰዎች አይለወጡም፤ ክፉ ሥራም የሠሩ ሰዎች በጎ ሥራን በሠሩ ሰዎች አይለወጡም። 9መለከት የሚነፋበትም ሰዓት በደረሰ ጊዜ ሙታን ከእግዚአብሔር በሚገኝ የጠል ምሕረት ይነሣሉ፤ በጎ ሥራ የሠሩ ሰዎች የሕይወት ትንሣኤን ይነሣሉ፤ ዋጋቸውም እግዚአብሔር ለደጋጎች ያዘጋጀው፥ መከራና ደዌ የሌለበት፥ ከዚህም በኋላ ዳግመኛ የማይሞቱበት የንጹሓን ማደሪያ የደስታ ገነት ነው። 10ክፉ ሥራ የሠሩ ግን የደይን ትንሣኤ ተነሥተው ከአሳታቸው ከዲያብሎስ ጋራ፥ 11ከሰው ልጆች ሁሉ አንድ ሰው ስንኳ ይድን ዘንድ ከማይወዱ ከሠራዊቶቹ ከአጋንንትም ጋራ ወደ ዘለዓለም ቅጣት ይሄዳሉ፤ 12የጨለማ ዳርቻ ወደ ሆነ፥ ጥርስ ማፋጨትና ልቅሶ ወዳለበት፥ ይቅርታና ምሕረት ወደሌለበት፥ እስከ ዘለዓለም ድረስ መውጫ ወደሌለበት ወደ ገሃነም ይወርዳሉ። በሥጋቸው ሳሉ በምድር ላይ በሕይወታቸው በጎ ሥራ አልሠሩምና። 13ስለዚህም ነፍስና ሥጋ በትንሣኤ ጊዜ ይፈረድባቸዋል። 14እግዚአብሔር የተአምራቱን ብዛት የሚያሳይባት የነፍስና የሥጋን በአንድነት መነሣት ለማያምኑ ሰዎች ወዮላቸው! 15ሁሉም እያንዳንዱ እንደ ሥራውና እንደ እጁ ድካም ዋጋውን ይቀበላል።