1የስንዴ ቅንጣት ካልፈረሰች አትበቅልም፤ ፍሬም አታፈራም። የስንዴ ቅንጣት ብትፈርስ ግን ወደ ምድር ሥር ትሰዳለች፤ ቅጠልም ታወጣለች፤ ዝርዝርም ይሆናል፤ ፍሬም ያፈራል። 2አንዲቱ የስንዴ ቅንጣት ብዙ ቅንጣት እንደምትሆን እናንተ ታውቃላችሁ። 3እንደዚሁ ይህች ቅንጣት ከነፋስና ከውኃ፥ ከመሬትም የተነሣ ትበቅላለች፥ ፀሐይ ግን በእሳት ፋንታ ነው። ስንዴ ያለ ፀሐይ ፍሬ ማፍራት አይችልምና። 4ነፋስም ስለ ነፍስ ፋንታ ነው፥ ያለ ነፋስም ስንዴ ማፍራት አይችልም፤ ውኃውም ምድርን ያጠጣታል፤ ያረካታልም። 5መሬትም ውኃን ከጠጣች በኋላ ሥርን ታስገኛለች፤ ጫፏም ወደ ላይ ከፍ ከፍ ትላለች፤ እግዚአብሔርም የባረካትን ያህል ታፈራለች። 6የስንዴ ቅንጣት ግን እግዚአብሔር የፈጠራት ነባቢት ነፍስ ያደረችበት የአዳም አምሳል ነው፤ የወይን ግንድም እንደዚሁ ውኃ ይጠጣል፤ ሥርም ይሰድዳል፤ ቀጫጭኑ የሥሩ ገመድም ውኃን ይስባል። 7ውኃዋንም ወደ ቅጠሎች ጫፍ ያወጣታል፤ ከእግዚአብሔር የተገኘ ጠል ረጃጅም የሐረጎችን ጫፎች ያጠጣቸዋልና። በፀሐይም ሙቀት ይዘረዝራል፤ በእግዚአብሔርም ፈቃድ ፍሬን ያፈራል። 8ልብን ደስ የሚያሰኝ በጎ መዓዛንም ያደርጋል፤ በበሉትም ጊዜ እንደማያስርብ እህልና እንደማያስጠማ ውኃ ያጠግባል፤ በጠመቁትም ጊዜ የወይን ጠጅ ይሆናል። 9በጠጡትም ጊዜ “ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል” ተብሎ በመዝሙር እንደ ተነገረ የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፤ ፈታ ፈታ ያለ ሰውም አፉን ከፍቶ በጠጣ ጊዜ ይሰክራል፤ በሳምባውም ይመላል፤ ደሙም ወደ ልቡ ይፈስሳል። 10የወይን ስካር እጅግ ያስታልና አእምሮውን ያሳጣዋል፤ ጐጻጕጹንና ገደሉንም እንደ ሰፊ ሜዳ ያደርገዋል፤ በእጁና በእግሩ ያለውንም እንቅፋትና እሾህ አያውቅም። 11እግዚአብሔርም ፈቃዱን በሚያደርጉና የሙታንን ትንሣኤ በሚያምኑ ስሙ ይመሰገን ዘንድ በወይን ግንድና በፍሬዋ እንዲሁ አደረገ። 12የሙታንን መነሣት የሚያምኑትንም በሕይወት ማደሪያ ደስ ያሰኛቸዋል።