1የሙታንን መነሣት የማታምኑ ሰዎች፥ ምን ያህል ስሕተትን ትስታላችሁ? ወደማታውቁትም ቦታ በወሰዷችሁ ጊዜ፥ በነፍስና በሥጋ በአንድነት የሙታንን መነሣት ስለ አላመናችሁ ወደ ገሃነም በጣሏችሁ ጊዜ ያንጊዜ የማይረባ ጸጸትን ትጸጸታላችሁ። 2ትቢያና ዐመድ የሆኑ ሙታን እንደማይነሡ እኛ እናውቃለን እያላችሁ የባልንጀሮቻችሁን ልቡና ታስታላችሁና በጎውንም ቢሆን፥ ክፉውንም ቢሆን እንደ ሠራችሁ ዋጋችሁን ትቀበላላችሁ። 3ስለዚህም ባልንጀሮቻቸውን ያስታሉ፤ ለሞታቸው ዕረፍት የለውምና፥ ለመቅሠፍታቸውም ኀይል የለውምና፥ በድካማቸውም የጸኑ አልሆኑምና፥ በእግዚአብሔር አደባባይም ይቆሙ ዘንድ አላቸውና። 4በመዓቱም በሚገሥጻቸው ጊዜ፥ ክፉም ስለ አደረጉ በሚቈጣቸው ጊዜ እጅግ ያፍራሉ፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ሳያውቁ ይናገራሉና። ከየት እንደ መጡም አያውቁምና። 5የሚሄዱበትንም ገሃነም አያውቁም፤ ቍጡዎች፥ በሥራቸውም ጠማሞችና ክፉዎች ስለ ሆኑ እንደ ልቡናቸው ጥመት ለባልንጀሮቻቸው ያስተምራሉና፤ ትንሣኤ ሙታንም የለም እያሉ ጠማማ ነገርን የሚያስተምሩ ናቸውና። 6ያንጊዜም ሙታን እንደሚነሡ ያውቃሉ፤ ለሰው ልጆች ወገን ሁሉ የሚሆነውን የሙታን ትንሣኤ ስለ አላመኑ እንደሚፈረድባቸው ያውቃሉ። 7ሁላችን የአዳም ልጆች ስለ ሆንን በአዳምም ምክንያት ሞተናልና፥ ሁላችንም በአባታችን በአዳም ስሕተት ከእግዚአብሔር ዘንድ የሞት ፍርድ አግኝቶናልና። 8ዳግመኛም በሠራነው ሥራችን ፍዳችንን እንቀበል ዘንድ ከዚያ ከአባታችን ከአዳም ጋራ እንነሣለን፤ በአባታችን በአዳም አለማወቅ ዓለም ለሞት ተገዝትዋልና። 9ስለዚህም በአዳም መተላለፍ ፍዳን እንቀበላለን፤ ሥጋችንም በመቃብር ውስጥ ቀለጠች፤ አጥንቶቻችንም ደቀቁ። 10ምድርም ቅልጥማችንን ጠጣች፤ ጠፋንም፤ ደም ግባታችንም በትቢያ ጠፋ፤ ሥጋችንም በመቃብር ተቀበረ፤ የአማረ ቃላችንም በመሬት ተቀበረ። 11ከሚያበሩ ዐይኖቻችንም ትሉ ወጣ፤ መልካችንም በመቃብር ጠፋ፤ ትቢያም ሆንን። 12መልከ መልካም የነበሩ፥ ቁመታቸውም ያማረ፥ የቃላቸውም ንግግር የተቀላጠፈ የጐልማሶች የመልካቸው ደም ግባት ወዴት አለ? የአርበኞችስ ገናናነታቸው ወዴት አለ? 13የነገሥታቱ ኀይላቸው፥ የመኳንንቱስ ክብራቸው ወዴት አለ? በፈረስ መጠረር፥ በወርቅና በብርም ማጌጥ፥ በሚያንጸባርቅ የጦር መሣሪያም መጠረር ወዴት አለ? 14የመባልዕት ጣዕምና ጣፋጩ የወይን መጠጥ የት አለ?