ምዕራፍ 19
1ነገሥታትንና መኳንንትን፥ ታላላቆችንና ክቡራንንም፥ የተዋቡ ሴቶችንና መልካማ ቆነጃጅትንም የሰበሰብሻቸው ምድር ሆይ፥ ከአንቺ የተነሣ ወዮ! 2ደም ግባት ያላቸውን፥ ባተ መልካሞች የሆኑትን፥ ዕውቀትና ልቡናም ያላቸውን፥ ቃላቸውም እንደምታንጐራጕር በገና፥ እንደ ክራርና እንደ መሰንቆም አመታት ያማረ ቃል ያላቸውን፥ 3እንደ ጣፋጭ የወይን መጠጥም ደስ የሚያሰኝ ዜማ ያላቸውን፥ ዐይኖቻቸውም እንደ አጥቢያ ኮከብ የሚያበሩትን፥ 4ቀኝ እጃቸውም እንደሚሰጥና እንደሚነሣ ጽኑዕ የሆነላቸውን፥ የሚነድፉ፥ እግሮቻቸውም ለማየት ያማሩና እንደተስተካከሉ መንኰራኩሮች የሚሮጡ ኀያላን ሰዎችን የሰበሰብሻቸው ምድር ሆይ፥ ከአንቺ የተነሣ ወዮ! 5በእግዚአብሔር ፈቃድ ተልከሃልና የመልከ መልካም ሰዎችን ነፍሳት ከሥጋቸው የለየህ ሞት ሆይ! ከአንተ የተነሣ ወዮ! 6አንችም ምድር! እግዚአብሔር ከአንቺ ያስገኛቸውንና ወደ አንቺ የመለሳቸውን ብዙዎች ሥጋዎችን ሰብስበሻልና ከአንቺ የተነሣ ወዮ! በፈቃደ እግዚአብሔር ከአንቺ ወጣን፤ ወደ አንቺም እንመለሳለን፤ በእግዚአብሔርም ፈቃድ በአንቺ ላይ ደስ አለን። 7ለሬሳዎቻችን ምንጣፍ ሆንሽ፤ በላይሽ ተመላለስን፤ በውስጥሽም ተኛን፤ ፍሬሽን በላን፤ አንቺም ሥጋችንን በላሽ። 8ከምንጭሽም ውኃ ጠጣን፤ አንቺም ከደማችን ምንጭ ጠጣሽ፤ ከመሬትሽ ስባት በላን፤ አንቺም የአጥንቶቻችንን ስባት በላሽ። 9ምግባችን ልትሆኝ እግዚአብሔር እንዳዘዘሽ ያማረ ጠል ከአለው ከመሬትሽ እህልን በላን፤ አንቺም የሥጋችንን ደም ግባት ተቀበልሽ፤ እግዚአብሔርም እንዳዘዘሽ ለምግብሽ ትቢያን አደረግሽው። 10ብዙዎች ኀያላን ነገሥታትንና መኳንንትን የሰበሰብህ፥ የፈጠራቸው እግዚአብሔርም እንዳዘዘህ ከገናናነታቸውና ከግርማቸው የተነሣ ያልፈራህ፥ ጦም አዳሪውንም ያልናቅህ ሞት ሆይ! ከአንተ የተነሣ ወዮ! 11መልካቸውም ለአማረ ሰዎች አልራራህም፤ ኀይለኞችንና አርበኞችንም አልተውህም፤ ባለጸጎችንና ድሆችን፥ መልከ ክፉዎችንና መልከ መልካሞችን፥ ሽማግሌዎችንና ልጆችን፥ ሴቶችንና ወንዶችንም አልተውህም። 12በጎ የሚያስቡትንና ከትእዛዙ ያልተላለፉትንም አልተውህም፤ በሥራቸውም እንደ እንስሳ የሆኑ ክፉ ነገር የሚያስቡትንም አልተውህም። በመልካቸው ደም ግባት፥ በቃላቸውና በነገራቸው ጣዕም ፍጹማን የሆኑትን አልተውህም። 13ቃላቸው ቁጡ የሆነና አፋቸውም ርግማንን የተመላ ሰዎችን አልተውህም፤ ነፍሶቻቸውንም በብርሃንና በጨለማ መዛግብትህ ሰበሰብህ። 14ምድርም መለከት እስከሚነፋበትና ሙታን እስከሚነሡበት ጊዜ ድረስ በዋሻም ቢሆን፥ በመሬትም ቢሆን ሥጋቸውን ሰበሰበች። 15ክፉ አድራጊዎች እንደ ሠሩት ሥራቸው ዋጋቸውን ይቀበላሉ፤ በመለከት ድምፅና በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሙታን እንደ ዐይን ጥቅሻ ይነሣሉና፥ በጎ ሥራ የሠሩም ደስ ይላቸዋል።