1በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ በፊቱ በቆምን ጊዜ በምድር የሠራነው ሥራችን ሁሉ እንደማይቀርና እንደማይሰወር እመኑኝ። 2ለመንገዳችንም ስንቅ ባልያዝን ጊዜ፥ ለሰውነታችንም ልብስ በሌለን ጊዜ፥ 3ለእጃችንም ምርጕዝ፥ ለእግራችንም ጫማ በሌለን ጊዜ፥ 4ድጥም ቢሆን፥ ጐጣጕጥም ቢሆን፥ ጨለማም ቢሆን፥ እሾህም፥ አሜኬላም ቢሆን፥ የባሕር ጥልቅም ቢሆን፥ የጕድጓድም ጥልቅ ቢሆን እኛን የሚወስዱበትን ጎዳናውን በማናውቅበት ጊዜ። 5የሚወስዱንንም አናውቃቸውም፤ ነገራቸውንም አንሰማም። 6እነርሱ ጥቋቍሮች ናቸውና፥ ወደ ጨለማም ይመሩናልና፥ ፊታቸውን አናይም። 7ነቢዩ ዳዊት እንደ ተናገረ፥ “ነፍሴ በላዬ በአለቀች ጊዜ አቤቱ ጌታዬ ጎዳናዬን አንተ ታውቃለህ፥ በዚች በሔድሁባትም ጎዳና ወጥመድ ሰወሩብኝ፤ ወደ ቀኜም ተመልሼ አየሁ፤ የሚያውቀኝም አጣሁ፤ የማመልጥበትም የለኝም።” 8ይህንም በተናገረ ጊዜ፦ አጋንንት እንደሚዘባበቱበትና ወደማያውቀው ጎዳና እንደሚመሩት ስለሚያውቅ ነው። ወደ ቀኝና ወደ ግራም ቢመለስ የሚያውቀው ሰው አላገኘም። 9እርሱንም የሚያውቀው አልነበረም፤ ነገር ግን በጨለማ መላእክት መካከል ነበረ። 10የጻድቃንን ነፍሳት ይቀበሉ ዘንድ፥ ወደ ሕይወት ብርሃን ቦታም ይወስዱ ዘንድ ወደ ደጋጉ የሚላኩ ረቂቃን መላእክተ ብርሃን ናቸው። 11ይቀበሏቸው ዘንድ፥ በሠሩት ኀጢአታቸውም ፍዳቸውን ሊቀበሉ ወደ ተዘጋጀላቸው ዘለዓለማዊ ቅጣት ይወስዷቸው ዘንድ ወደ ኃጥኣን ነፍሳት የሚላኩ ግን መላእክተ ጽልመትና አጋንንት ናቸው። 12ወደ ጥፋት ለሚወስዷቸው ዕረፍትና ድኅነት ካገኛቸውም መከራ እስከ ዘለዓለም ድረስ ማምለጥና መውጣት ለሌላቸው ለኃጥአን ነፍሳት ወዮላቸው። 13በቃየን መንገድ ሄደዋልና፥ በበለዓምም በደል ዋጋ ጠፍተዋልና፥ የሚያደርጉትንም አጥተዋልና። ገንዘባቸው ያልሆነውን የባዕድ ገንዘብ በግፍ ይወስዱ ዘንድ መማለጃንና አራጣን ለመቀበል ያመካኛሉና። 14እነርሱም እንደ ሠሩት ሥራቸው በገሃነም እሳት ፍዳቸውን ይቀበላሉ።