1የራሳቸው ገንዘብና የእጃቸው ሥራ ያልሆነውን የሌላውን ገንዘብ በዐመፅ የሚሰበስቡ ሰዎች ወዴት አሉ? 2ያለ ዋጋ የሌላውን ገንዘብ ይወስዳሉና፥ የምትደርስባቸው ዕለተ ሞታቸውንም ሳያውቁ ይሰበስባሉና፥ ገንዘባቸውንም ለባዕድ ይተዋሉና። 3ልጆቻቸውም በአባቶቻቸው ገንዘብ ደስ አይላቸውም፤ እንደ አባቶቻቸው እንደ እነርሱ ያሉ ኃጥኣንን በስርቆትም ቢሆን በቅሚያም ቢሆን፥ አስጨንቀው የሚይዙ የኃጥኣን ወገኖች ናቸውና። 4የአባቶቻቸውም ገንዘብ አይጠቅማቸውም፤ በንጥቂያና በግፍ ሰብስበውላቸዋልና፤ እንደ ጉም ሽንትና ነፋስ እንደሚበትነው ጢስም፥ እንደሚረግፍ ሣርም፥ በእሳትም ፊት እንደሚቀልጥ ሰም እንዲሁ የኃጥኣን ክብራቸው ይጠፋል። 5ዳዊትም እንደ ተናገረ፥ “ኀጢአተኛን እንደ ሊባኖስ ዛፍ ለምልሞና ከፍ ከፍ ብሎ አየሁት፤ በተመለስሁ ጊዜ ግን አጣሁት፤ ፈለግሁ፤ ቦታውንም አላገኘሁም።” 6የማይሞቱ መስሏቸው የሌላውን ገንዘብ በግፍ ስለሚሰበስቡ ዛሬ ባልንጀሮቻቸውን የሚበድሉ ሰዎች እንዳይመኩ የኃጥኣን ጥፋታቸው እንደዚህ በአንድ ጊዜ ነው። 7እናንተ ሰነፎች፥ እንደምታልፉ፥ ገንዘባችሁም ከእናንተ ጋር እንደሚያልፍ አስቡ፤ ወርቃችሁና ብራችሁ ቢበዛ የዛገ ይሆናል። 8ልጆችን ብታበዙም የመቃብር ብዛት ይሆናል፤ ቤቶችንም ብታበዙ የፈረሰ ይሆናል። 9የአምላካችሁ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አልፈጸማችሁምና ከብት ብታበዙም ለጠላቶቻችሁ ምርኮ ይሆናል፤ ያልተባረከ ሆኗልና፥ እጃችሁን ያኖራችሁበት ገንዘብ ሁሉ አይገኝም። 10በቤትም ያለ ቢሆን፥ በዱርም ያለ ቢሆን፥ በመሰማሪያና በእርሻም ያለ ቢሆን፥ በእህል አውድማና በወይን መጭመቂያም ያለ ቢሆን አይገኝም። 11በሆዳችሁም ፍሬ ቢሆን ደስ አይላችሁም፤ ነገር ግን ከጠላቶቻችሁ የተነሣ ኀዘን ይሆንባችኋል። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስላልጠበቃችሁ፥ እግዚአብሔር ከቤተ ሰባችሁ ሁሉ ጋር አያድናችሁምና። 12ሕጉንና ሥርዐቱን፥ ትእዛዙንም የጠበቁ ሰዎችን ግን ከበረከቱ አያሳጣቸውም፤ የለመኑትንም ሁሉ ይሰጣቸዋል፤ የምድራቸውን ፍሬና የሆዳቸውን ፍሬም ይባርክላቸዋል። 13እንዲገዙ እንጂ እንዳይገዙ፥ በዙሪያቸው ከአሉ አሕዛብም ሁሉ በላይ ያደርጋቸዋል፤ በመሰምሪያቸውም ቦታ በረከቱን ሁሉ ይሰጣቸዋል። 14እጃቸውን ያኖሩበትን ሁሉ፥ የእርሻቸውን ፍሬ ሁሉና የከብቶቻቸውን ቦታ ሁሉ ይባርክላቸዋል፤ በሆዳቸውም ፍሬ ደስ ያሰኛቸዋል። 15ከብቶቻቸውንም አያሳንስባቸውም፤ ከመከራቸውም ሁሉ ከበሽታና ከድካምም፥ ከጥፋትም፥ ከሚያውቁትና ከማያውቁትም ያድናቸዋል። 16በፍርድም ጊዜ ይከራከርላቸዋል፤ ከክፉ ነገርና ከመከራም፥ ከሚቃወማቸውም ሁሉ ያድናቸዋል፤ በመጀመሪያ የድንኳኑን ሥራ በአደራ የተቀበለ ሌዋዊ የድንኳኑን ሥራ ቢጠብቅ፥ በእግዚአብሔርም ፈቃድ ቢሄድ፥ በመጀመሪያው ሕግ እንደ ሕጉ ሁሉ ዐሥራቱንና ከሰው ጀምሮ እስከ ከብት ድረስ በኵራቱን ይሰጡት ነበር። 17ሙሴም የነዌ ልጅ ኢያሱን እንዳዘዘው በሚፈርዱበትና ለሚፈርዱለት ፍርድን እስኪሰጡ ድረስ ባለማወቅ ወይም በማወቅ ነፍስ የገደለ ሰው ቢኖር በዚያ ይድን ዘንድ በከተሞቻቸው ሁሉ መማጸኛ ከተማ ነበር። 18“ቀድሞ ከእርሱ ጋር ጠብ እንዳለው በልቡናችሁ መርምሩ አላቸው፤ 19ምሳርም ቢሆን፥ ድንጋይም ቢሆን፥ እንጨትም ቢሆን፥ ባለማወቅ ከእጄ ስለ ወደቀ ያ የወደቀበት ሰው ሞተብኝ ቢል፥ መርምራችሁ አድኑት፤ ባለማወቅ አድርጎታልና ይድናል። 20በማወቅ ቢያደርገው ግን እንደ በደሉ ፍዳውን ይቀበላል፤ የሚምረውም የለም፤ ባለማወቅ ቢያደርግና ቢገድለው ግን ባለማወቅ አድርጎታልና እንዳይሞት መርምራችሁ አድኑት።” 21ሙሴም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንዳይተላለፉ ለእስራኤል ልጆች እንደዚህ ሥርዐት ሠርቶላቸው ነበር፤ ከክፋትም ሁሉ እንዲርቁ ሥርዐት ሠርቶላቸው ነበር። 22በፍርዱና በሕጉ ይኖሩ ዘንድ፥ ጣዖት ከማማለክ፥ ሙቶ ያደረውንና አባላ የተመታውን ከመብላትም፥ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ለሚኖሩና እንደ ሠራላቸው ከክፉ ሥራ ሁሉ ለሚርቁ ለሰው ልጆች ከማይገባው ሁሉ ፈጽመው ይርቁ ዘንድ አዘዛቸው። 23ነፍሳቸውንም ያድኑ ዘንድ፥ በጎ ከሠሩ ከአባቶቻቸው ጋራ ማደሪያቸውን ያገኙ ዘንድ በሰማይ ባለች ድንኳን አምሳል ከሠራላቸው ትእዛዝ እንዳይወጡ አዘዛቸው። 24በእግዚአብሔር ቃል ያመኑና በትእዛዙ የሄዱም እነርሱ የጻድቃን ልጆች ይባላሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከአደረጉ ከአዳምና ከሴት ናቸውና። 25የአዳም ልጆች ነንና፥ በጎ ሥራንና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም ሁሉ እንሠራ ዘንድ በመልኩና በምሳሌው ፈጥሮናልና አይንቀንም። 26በጎ ሥራን ብንሠራም በጎ ሥራን ከሠሩ ጋራ መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳታለን፤ የሚወዱትን አይለያይምና። 27በንጹሕ የሚለምኑትን ሰዎች እጅግ ይወዳቸዋል፤ ጸሎታቸውንም ይሰማቸዋል፤ ቈርጠው ንስሓ የሚገቡትንም ንስሓቸውን ይቀበላቸዋል፤ ሕጉንና ሥርዐቱን፥ ትእዛዙንም ለሚጠብቁ ሰዎች ኀይልንና ጽናትን ይሰጣቸዋል። 28ፈቃዱንም ያደረጉ ሰዎች ለዘለዓለሙ በመንግሥቱ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል፥ ፊተኞችም ቢሆኑ፥ ኋለኞችም ቢሆኑ ምስጋናን ያቀርቡለታል። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም አሜን።