1በትዕቢትና በልብ ተንኰል ሄደ። 2በመንግሥቱም ዳንኤል እንዳየው ብረት ፅኑ ተብሏልና በዙሪያው ያሉ የአሕዛብ ሀገሮችን ዞረ። 3በስንፍናና በክፋት ሁሉ፥ በሁከትም ይኖራል። 4ቀድሞም የተናገርነውን ይሰብራል፥ ያደቅቃል፤ ይበላልም። 5አንገቱን እንደ አደነደነ እንደ አባቱ እንደ ዲያብሎስም መርዝ የሚተፋ ነውና የቀረውን በእግሩ ይረግጣል። 6እግዚአብሔርንም ፈጣሪው እንደ ሆነ አያውቀውም፤ ነገር ግን ዘመኔ እንደ ሰማይ ዘመን ሆነ ይላል። 7በልቡናውም ፀሐይ ከእርሱ እንደሚወጣ ያስባል። 8በኀይልም ይነሣል፤ በዛብሎን ዕጣ ይሰፍራል፤ በመቄዶንያም ሰልፍን ያስነሣል፤ ከሰማርያም ቀለቡን ይቀበላል፤ ከሶርያም እጅ መንሻን ይሰጡታል። 9በዘላኖች አውራጃ ይሰፍራል፤ እስከ ሲዶናም ይደርሳል፤ በአካይያም ግብርን ይጥላል፤ እስከ ፈሳሹ ባሕርም ድረስ አንገቱን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ተመልሶም እስከ ሕንደኬ ባሕር ድረስ መልእክቱን ይልካል። 10እንዲሁም አንገቱን እስከ ሰማይ ድረስ ከፍ ከፍ ያደርጋል። 11በመታበይና በክፋት ጸንቶ ይኖራል እንጂ ራሱን ማዋረድ የለውም። 12መንገዱም ሁሉ ወደ ጨለማና ወደ ድጥ፥ ወደ ወንጀልና ወደ መታበይም፥ ደም ወደ ማፍሰስና ወደ መከራም ነው። 13መንገዱ ሁሉ እግዚአብሔር የሚጠላው ነው፤ የቅሚያና የክፋት፥ የኀጢአትም መምህር ሰብላንዮስ እንደ አስተማረው ያደርጋል፤ ድሃአደጉንም ያስጮሃል፤ ለድሃም አይራራም። 14የአሕዛብንም ነገሥታት በእጁ አግብቶ ገደላቸው። 15የጠላቶች አለቆችንም ገዛ፤ ብዙ አሕዛብንም ገዛ፤ እንደ ወደደም አስገበራቸው። 16ምሕረትም አላደረገም፤ ከተርሴስ ባሕር ጀምሮ እስከ ኢያሪኮ ባሕር ድረስ ያልነጠቀው የለም። 17ለጣዖትም ይሰግድ ነበር፤ ሙቶ ያደረውንና ደሙን፥ አባላ የተመታውንና ለጣዖቶች የተሠዋውን ይበላ ነበር፤ በሥራውም ሁሉ ያለ ፍርድ ፍጹም ቍጣና ክርክር ነበር እንጂ ፍርድ አልነበረውም። ከሥልጣኑ በታች ላሉ አሕዛብም የሚያስደነግጥ ሆኗልና እንደ ወደደ ግብርን ያስገብራቸው ነበር። 18በፊቱ የወደደውን ሁሉ ያደርጋልና በፊቱ እግዚአብሔርን መፍራት አልነበረውም፤ በፈጣሪው በእግዚአብሔርም ፊት በተንኰል ይኖር ነበር። 19እንደ ፈጣሪውም አያደርገውም ነበር። እግዚአብሔርም ተቈጥቶ በያዘው ጊዜ በባልንጀራው ላይ ክፉ ነገርን እንደ አደረገ ፍዳውን ይከፍለዋል። 20እግዚአብሔር ከዚህ ዓለም ስም አጠራራቸውን አጠፋ ዘንድ በትእዛዜ የማይኖሩ ትዕቢተኞችን እኔ ተበቅዬ አጠፋቸዋለሁ ብሏልና፥ ከእርሱ አስቀድሞ የነበሩ ኃጥኣንን እንዳጠፋቸው በጊዜው ይበቀለዋል። 21ክፉዎችም ክፉ እንደ አደረጉ ፍዳቸውን ይቀበላሉ። 22በጎ አድራጊዎችን ግን በጎነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ትከተላቸዋለች። 23ኢያሱ አምስቱን የከነዓን ነገሥታትን በአንዲት ቀን በአንዲት ዋሻ እንደ አጠፋቸው፥ ሠራዊቶቻቸውንም ያጠፋቸው ዘንድ በጸሎቱ ፀሐይን በገባዖን እንደ አቆመ፥ የኤዌዎንንና የከናኔዎንን፥ የፌርዜዎንንና የኬጤዎንን፥ የኢያቡሴዎንንም ሠራዊት እስኪያጠፋቸው ድረስ ፀሐይ በሰማይ መካከል ቆሟልና በአንድ ጊዜ ሃያ ሺህ ያህል ሰውም እንደ ገደለ፥ እነርሱንም እንደ ገደላቸው፥ እግር ከአንገትም አድርጎ እንደ አሰራቸው፥ በዋሻም በጦር እንደ ገደላቸው፥ ደንጊያም እንደ ገጠመባቸው፥ 24በክፉ ሥራቸው እግዚአብሔርን የሚያሳዝኑትንም ሰዎች እንደዚህ ያለ መከራ ያገኛቸዋል።