1የፈጠራችሁ እግዚአብሔርን የማታውቁ፥ ትእዛዙንና ቃሉንም የማትጠብቁ አንተና እንደ አንተ ያሉት ወዮላችሁ! በሲኦል ጭንቅም ተይዛችሁ በተገረፋችሁ ጊዜ በማይረባ ጸጸት ትጸጸቱ ዘንድ አላችሁና። 2ነፍስና ትንፋሽ ለሌላቸው፥ ክፉ ነገር ያደረገባቸውን ለማይበቀሉ፥ በጎ ነገር ላደረገላቸውም በጎ ነገርን ለማያደርጉ ለጣዖቶችህ እንደ ፈጣሪያችሁ እንደ እግዚአብሔር የምትሠዉላቸውና የምትሰግዱላቸው አንተና ካህናትህ እስከ ዘለዓለም ድረስ ከእርሷ መውጫ የላችሁም። 3እናንተንና የአማልክቶቻችሁን አገልጋዮች፥ እናንተንም የሚያዝዙ አጋንንትን ወደ ገሃነመ እሳት ያወርዳችሁ ዘንድ እንደ እናንተ ያሉ የሰነፎችን ልቡና ለማሳት ሰይጣን በውስጣቸው የሚናገርባቸው የሰው እጅ ሥራ ናቸውና። 4የሚረባችሁ እንደሌለ አታውቁምና ትበድላላችሁ፤ ትስታላችሁም። 5ከእናንተስ ለምግባችሁ እግዚአብሔር የፈጠራቸው እንስሳት፥ አውሬዎችና ውሾችም ይሻላሉ። እነርሱ ከአንዲት ሞት በቀር ዳግመኛ ኵነኔ የለባቸውምና። 6እናንተ ግን ትሞታላችሁ፤ ዳግመኛም እስከ ዘለዓለም ድረስ መውጫ በሌለባት በገሃነም እንቅጥቅጥ ይፈርድባችኋል። 7ይኸንም ተናግረው ሄዱ፤ ከእርሱም ተሰወሩ። 8ያ ጺሩጻይዳን ግን በጽኑ ፍርሀት ተይዞ ሲንቀጠቀጥ አደረ፤ እስኪነጋም ድረስ አልተወውም። 9ከዚህም በኋላ የጻድቃንን ሬሳዎች ወደ ጣለበት ቦታ ሄደ፤ ነገር ግን አላገኛቸውም፤ ይቀብራቸው ዘንድ ወድዶአልና። ነገር ግን ሄዶ ሬሳቸውን እንዳይነካ እግዚአብሔር ሰውሯቸዋልና አጣቸው።