1የእግዚአብሔር ጠላት ትዕቢተኛው ጺሩጻይዳን የሐሰት ካህናትንና የጣዖታቱን አገልጋዮች ሾመ። 2መሥዋዕት ይሠዉላቸው ነበር፤ ወይኑንም ያፈስሱላቸው ነበር። 3እነርሱም የሚበሉና የሚጠጡ ይመስለው ነበር። 4በየጧቱም ላሞችንና በጎችን፥ ፍየሎችንና ጊደሮችንም ይሰጣቸው ነበር፤ ማታና ጧትም መሥዋዕት ይሠዋ ነበር፤ ከዚያችም ከረከሰችው መሥዋዕት ይበላ ነበር። 5ዳግመኛም ለጣዖታቱ ይሠዉ ዘንድ ሌሎች ሰዎችን ያነሣሷቸውና ግድ ይሏቸው ነበር እንጂ እነርሱ ብቻ የሚያደርጉት አልነበረም። 6የመቃቢስንም ልጆች ያማሩ እንደ ሆኑና ፈጣሪያቸው እግዚአብሔርን እንደሚያመልኩት ባዩአቸው ጊዜ እንዲሠዉና ከረከሰችውም መሥዋዕት እንዲበሉ የጣዖታቱ ካህናት ያስትዋቸው ዘንድ ወደዱ፤ እነዚህ የተባረኩ የመቃቢስ ልጆች ግን እንቢ አሏቸው። 7የአባታቸውን ትእዛዝ ይጠብቃሉና፥ በጎ ሥራንም በመሥራት ጸንተዋልና፥ እግዚአብሔርንም ፈጽመው ይፈሩታልና እነርሱን እሺ ማሰኘት ተሳናቸው። 8ባሰሯቸውና በሰደቧቸው፥ በቀሟቸውም ጊዜ፥ 9ለጣዖቶችም መስገድንና መሠዋትን እንቢ እንዳሉ ለንጉሡ ለጺሩጻይዳን ነገሩት። 10ስለዚህም ንጉሡ ተቈጣ፤ አዘነም፤ ያመጧቸውም ዘንድ አዘዘ፤ አምጥተውም በፊቱ አቆሙአቸው፤ እርሱም “ለጣዖቶች ስገዱ፤ መሥዋዕትንም ሠዉ” አላቸው። 11እነርሱም መልሰው እንዲህ አሉት፥ “እኛስ በዚህ ነገር አንመልስልህም፤ ለረከሱ ለጣዖቶችህም መሥዋዕትን አንሠዋም።” 12በብዙ ሥራም አስፈራራቸው፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር አምነው ልባቸውን አስጨክነዋልና አልቻላቸውም። 13እሳትም አንድዶ ጨመራቸው፤ እነርሱም ነፍሳቸውን ለእግዚአብሔር ሰጡ። 14ከሞቱ በኋላም ሕያዋን ሆነው፥ የተመዘዙ ሰይፎቻቸውን ይዘው በመንግሥቱ ዙፋን ተኝቶ ሳለ በሌሊት ታዩት፤ እርሱም ፈጽሞ ፈራ። 15እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ጌቶች እሺ በሉኝ፤ ምን ላድርግላችሁ? ያዘዛችሁኝን ሁሉ አደርግ ዘንድ ነፍሴን አትውሰዷት፤” ፈጽመውም አስፈሩት። 16እነርሱም፥ “እግዚአብሔር ፈጣሪህ እንደ ሆነ አስብ” እያሉ የሚገባውን ሁሉ ነገሩት፤ “ከዚህም ትዕቢትህ የሚሽርህና ከአባትህ ከዲያብሎስ ጋራ ወደ ታች ወደ ገሃነም የሚያወርድህ አለ፤ በዚያም አንተን የበደልንህ በደል ሳይኖር፥ ፈጣሪያችን እግዚአብሔርንም እያመለክን ሳለን፥ እግዚአብሔርነቱንም በመፍራት እየሰገድንለት ሳለን በእሳት እንዳቃጠልኸን ፍዳህን ሁሉ ትጨርሳለህ። 17እርሱ ሁሉን የፈጠረ ነውና፥ ሰማይንና ምድርን፥ ባሕሩንና በውስጧ ያለውንም ሁሉ፥ 18ፀሐይንና ጨረቃንም፥ ከዋክብትንም፥ ፍጥረቱንም ሁሉ የፈጠረ እርሱ እግዚአብሔር ነውና። 19“በላይ በሰማይ፥ በታችም በምድር ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ ሁሉን የሚችል እርሱ ነው፤ የሚሳነውም የለም። የሚገድልና የሚያድን፥ የሚገርፍና ይቅር የሚል እርሱ ነው። 20ሰማይንና ምድርን የሚገዛ እርሱ ነውና ከእጁ የሚያመልጥ የለም። 21ከአንተ ከወንጀለኛውና አባትህ ሰይጣን ልቡናቸውን ካሳወራቸው እንደ አንተ ከአሉ ከወንጀለኞች በቀር እርሱ ከፈጠረው ፍጥረት ከትእዛዙ የሚወጣ የለም፤ አንተና እነዚያ ጣዖታቶችህም እስከ ዘለዓለም ድረስ መውጫ ወደሌለባት ወደ ገሃነም በአንድነት ትወርዳላችሁ። 22በእኛ ክፉ ነገርን ታደርግ ዘንድ ይኸን ክፉ ሥራ ያስተማረህ መምህርህ ሰይጣን ነው እንጂ ይኸን የምታደርግ አንተ ብቻ አይደለህምና። 23የፈጠረህ እግዚአብሔርንም አላሰብኸውም፤ ራስህንም እንደ ፈጣሪህ እንደ እግዚአብሔር ታደርጋለህ። 24እግዚአብሔር እስኪያዋርድህ ድረስ በእጅህ ሥራና በጣዖቶችህ ትታበያለህ፤ በምድር ላይም ስለ ሠራኸው ኀጢአትህና በደልህ ሁሉ ይበቀልሃል።”