1እርሱም ታናናሽ ልጆቹን ትቶ ሞተ፤ አባታቸውም ሥርዐት እንደ ሠራላቸው አደጉ፤ የቤታቸውንም ሥርዐት ጠበቁ፤ ወገናቸውንም ሁሉ ይጠብቁ ነበር፤ ድሃውንና ባልቴቶችን፥ የሙት ልጆችንም አያስጮሁም ነበር። 2እግዚአብሔርንም ይፈሩት ነበር፤ ገንዘባቸውንም ለድሆች ይመጸውቱ ነበር፤ አባታቸውም አደራ ያላቸውን ሁሉ ይጠብቁ ነበር፤ ባልቴትዋንና የሙት ልጆችንም በችጋራቸው ጊዜ ያረጋጓቸው ነበር፤ አባትና እናትም ይሆኗቸው ነበር፤ ከሚበድሏቸው ሰዎች እጅ ያስጥሏቸው፥ ካገኛቸው ሁከትና ኀዘንም ሁሉ ያረጋጓቸው ነበር። 3እንዲህም እያደረጉ አምስት ዓመት ኖሩ። 4ከዚህም በኋላ የከለዳውያን ንጉሥ ጺሩጻይዳን መጣ፤ ሀገራቸውንም ሁሉ አጠፋ፤ የመቃቢስንም ልጆች ማረካቸው፤ መንደራቸውንም ሁሉ አጠፋ። 5ገንዘባቸውንም ሁሉ ዘረፈ፤ እነርሱንም በእግዚአብሔር ትእዛዝና ፍርድ የማይሔዱ፥ ነገር ግን በክፋት ሁሉና በዝሙት፥ በርኵሰትና በስስት፥ በፅርፈትና አምላካቸውን ባለማሰብ የሚሔዱ ጣዖት አምላኪዎች ይዘው ወደ ሀገራቸው ወሰዷቸው። 6የሞተውንና ደሙን፥ አውሬ የበላውንና የበከተውን፥ እግዚአብሔርም የማይወድደውን ሁሉ ይበላሉ፤ በኦሪት ከተጻፈው ከእውነተኛው ትእዛዝም ሁሉ ሕግ የላቸውም። 7እግዚአብሔርንም ከእናታቸው ማኅፀን ያወጣቸውና በሚገባ የመገባቸው፥ ፈጣሪያቸውና መድኀኒታቸውም እንደ ሆነ አያውቁትም። 8በፍርድ ጊዜም ሕግ የላቸውም፤ የእንጀራ እናታቸውንና አክስታቸውን አግብተው ወደ ቅሚያና ወደ ክፉ ነገር፥ ወደ ኀጢአትና ወደ ዝሙትም ይሄዳሉ እንጂ። ክፉውንም ሁሉ ያደርጋሉ፤ እኅቶቻቸውንና ዘመዶቻቸውንም ያገባሉ፤ ሕግም የላቸውም። 9መንገዳቸውም ሁሉ ድጥና ጨለማ፤ ርኵሰትና ዝሙት ነው። 10እነዚያ የመቃቢስ ልጆች ግን በሥርዐታቸው ሁሉ ይጠበቁ ነበር፤ ሞቶ ያደረውንና አባላ የተመታውን አይበሉም ነበር፤ የከለዳውያንንም ልጆች ርኵሰትና ኀጢአታቸውን ሁሉ አይሠሩም ነበር። በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ የኃጥኣንና የወንጀለኞች፥ የመናፍቃንና የከዳተኞች፥ ፍጹም ርኩሰትንና ቅሚያን የተሞሉ የአረማውያን ልጆች የሚሠሩት ሥራቸው ክፉና ብዙ ነበርና። 11ፈጣሪያቸው እግዚአብሔር የሚወድደው ሥራ ሁሉ በእነርሱ ዘንድ አልነበረም። 12ዳግመኛም ስሙ ብኤል ፌጎር የሚባል ጣዖትን ያመልኩ ነበር፤ እንደ ፈጣሪያቸው እንደ እግዚአብሔርም ያመልኩትና ይታመኑት ነበር። እርሱ ግን ደንቆሮና ዲዳ ስለሆነ የሚያየውና የሚሰማው የለም፤ የሰው እጅ ሥራ ጣዖት ነውና፤ ብርና ወርቅን የሚሠራ አንጥረኛ የሠራው፥ ትንፋሽና ዕውቀት የሌለው የሰው እጅ ሥራ ነው፤ 13አይበላም፤ አይጠጣምም። 14አይገድልም፦ አያድንምም። 15አይተክልም፦ አይነቅልምም። 16መልካም አያደርግም፤ ክፉም አያደርግም። 17አያደኸይም፦ አያከብርምም። 18አይቀሥፍም፤ ይቅርም አይልም። ነገር ግን ሰነፎች የከለዳውያንን ሕዝብ ለማሳት ዕንቅፋትን ይሆናል።