1በኢያሱም እነርሱን ያዳነበት ጊዜ አለ። 2በጌዴዎን እነርሱን ያዳነበት ጊዜ አለ። 3በሶምሶን፥ በባርቅና በዲቦራ፥ በዮዲትም እነርሱን ያዳነበት ጊዜ አለ፤ በሴትም ቢሆን፥ በወንድም ቢሆን አድሮ ከሚያሠቃዩአቸው ጠላቶቻቸው እጅ ያድኗቸው ዘንድ መሳፍንትን ያስነሣላቸው ነበር። 4እግዚአብሔርም እንደ ወደደ ከሚያሠቃዩአቸው ሰዎች እጅ ያድናቸው ነበር። 5በአደረገላቸውም በጎ ነገር ሁሉ በምድራቸው ዘር፥ በምድረ በዳ ያለ መንጋቸውን ሁሉና ከብታቸውንም በማብዛት ደስ ይላቸው ነበር። 6ከብታቸውንና ተክላቸውን ይባርክላቸው ነበር፤ በቤትና በምድረ በዳ የያዙትንም ሁሉ ይባርክላቸው ነበር፤ በዐይነ ምሕረት ይመለከታቸው ነበርና እንስሶቻቸውን አያሳንስባቸውም ነበር፤ የጻድቃን ልጆች ናቸውና ፈጽሞ ይወዳቸው ነበር። 7እነርሱ ግን በሥራቸው ክፉ በሆኑ ጊዜ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር። 8በሚያጠፋቸውም ጊዜ ወዲያውኑ ይሹት ነበር፤ ተመልሰውም ወደ ፈጣሪያቸው ወደ እግዚአብሔር ይገሠግሡ ነበር። 9በፍጹም ልቡናቸውም በተመለሱ ጊዜ ኀጢአታቸውን ያስተሰርይላቸው ነበር፤ ሥጋና ደም እንደ ሆኑ ያውቃቸዋልና የሚያስት የዚህ ዓለም አሳብና፥ አጋንንትም አሉባቸውና የቀደመ ኀጢአታቸውን አያስብባቸውም ነበር። 10ያ መቃቢስ ግን እግዚአብሔር በቅዱሱ ተራራ የሠራውን ይህን ሥርዐት በሰማ ጊዜ በንስሓ ተጋደለ። 11ይኸን ነገር ከአየና ከሰማ በኋላም በጎ ሥራ መሥራትን አላቃለለም፤ እግዚአብሔር ይቅር ብሎአቸዋልና የእስራኤል ልጆች የሚሠሩትን ቸርነት ሁሉ መሥራት አላቃለለም፤ ትእዛዙንም ሲተላለፉ እግዚአብሔር በሚቀሥፋቸው ጊዜ ያለቅሱና ይጮሁ ነበር፤ ዳግመኛም ይቅር ይላቸው ነበር፤ ሕጉንም ይጠብቁት ነበር። 12መቃቢስም እንደዚሁ መንገዱን ያቀና ነበር፤ ትእዛዙንም ይጠብቅ ነበር፤ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ትእዛዝም ይሔድ ነበር። 13ያንጊዜም የእስራኤል ልጆች የሚመኩበትን ሁሉ ከሰማ በኋላ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመጠበቅ እንደ እነርሱ ይመካ ነበር። 14ቤቱንና ልጆቹንም በእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ ሁሉ ይሄዱ ዘንድ ይሠራራ ነበር። 15አይሁድ የሚከለከሉትን ሥርዐት እርሱም ይከለከል ነበር፤ አይሁድም የሚጠብቁትን ትእዛዝ ሰምቶ ይጠብቅ ነበር፤ እርሱ ልዩ ሞዓባዊ ወገን ሲሆን አይሁድ የሚከለከሉትን ምግብም ይከለከል ነበር። 16ዐሥራትም ያወጣ ነበር፤ ከበጎቹና ከላሞቹ፥ ከአህዮቹም መጀመሪያ የተወለደውንና የገዛውን ሁሉ ይሰጥ ነበር፤ እንዲሁም አይሁድ የሚሠዉትን መሥዋዕት ፊቱን ወደ ኢየሩሳሌም መልሶ ይሠዋ ነበር። 17የስእለቱንና የኀጢአቱን፥ የፈቃዱንና የሰላሙን መሥዋዕትና የዘወትሩን መሥዋዕት ይሠዋ ነበር። 18የአዝመራውንም መጀመሪያ ይሰጥ ነበር፤ አይሁድም የሚያቀርቡትን የወይኑን ቍርባን ያቀርብና ለሾመው ለሌዋዊው ይሰጥ ነበር፤ አይሁድም የሚያደርጉትን ሁሉ እንዲሁ ያደርግ ነበር፤ ዕጣኑንም ያጣፍጥ ነበር። 19መቅረዝንና ጋኖችን፥ ጠረጴዛዎችንና ድንኳኖችን፥ አራቱን ኅብርና ቀለበቶችን፥ ለቅድስተ ቅዱሳኑም መብራት የተጣራ ዘይትን፥ እግዚአብሔርን በሚያገለግሉበት ጊዜ እስራኤል በቅድስተ ቅዱሳኑ እንደሚያደርጉት መጋረጃን አሠራ። 20በሕጉና በሥርዐቱ በኖሩ ጊዜ፥ እግዚአብሔርም ቸል ብሎ በጠላቶቻቸው እጅ ባልጣላቸው ጊዜ፥ መቃቢስም እንደ እነርሱ በመንገዱ ሁሉ በጎ ሥራ ይሠራ ነበር። 21መሪ እንዲሆነው፥ ከመረጣቸውና ፈቃዱን ከአደረጉ ከእስራኤል ወገኖችም እንዳይለየው ሁልጊዜ ወደ እስራኤል ፈጣሪ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር። 22በጽዮን ልጅን፥ በኢየሩሳሌምም ቤትን ይሰጠው ዘንድ፥ በነቢዩ አንደበት ከተናገረው ከጥፋትም ያድነው ዘንድ ንስሓ በገባበትና በእግዚአብሔር ፊት በአለቀሰው ልቅሶ ሁሉ ንስሓውን ይቀበለው ዘንድ፥ 23ዘሩንም ከምድር እንዳያጠፋበት፥ በመግባቱና በመውጣቱም ይጠብቀው ዘንድ ዳግመኛ ይጸልይ ነበር። 24በመቃቢስ ሥልጣን በታች ከአሉ ከሞዓብ አሕዛብም ያምኑ ዘንድ ደስ አላቸው፤ አለቃቸው በቀናች መንገድ ይሄድ ነበርና፥ ፍርዱንም ይመለከቱ ነበር፤ ፈቃዱንም ያደርጉ ነበር፤ የአገራቸውን ፍርድና ያገራቸውን ቋንቋ ይንቁ ነበርና የመቃቢስም ሥራ እንደሚቀናና እንደሚሻል ያስተውሉ ነበር። 25ወደ እርሱም መጥተው የመቃቢስን የቸርነቱንና የእውነቱን ፍርድ ይሰሙ ነበር። 26ብዙ ገንዘብም ነበረው፤ ወንዶች ባሮችና ሴቶች ባሮች፥ ግመሎችና አህዮችም ነበሩት፤ ጥሩር የሚለብሱ አምስት መቶ ፈረሶችም ነበሩት፤ ኢሎፍላውያንንና አማሌቃውያንን፥ ሶርያውያንንም ፈጽሞ ድል ይነሣቸው ነበር፤ ቀድሞ ጣዖት ሲያመልክ ግን ድል ሲነሡት ኖረ። 27እግዚአብሔርን ከአመነ ወዲህ ግን ወደ ሰልፍ ሲሄድ እርሱ ድል ይነሣ ነበር እንጂ እርሱን ድል የነሣው አልነበረም። 28እነርሱ ግን ይወጉት ዘንድ በጣዖቶቻቸው ኀይል ይመጡ ነበር፤ በጣዖቶቻቸውም ስም ጠርተው ይረግሙት ነበር፤ ነገር ግን እምነቱን በፈጣሪው በእግዚአብሔር ላይ አድርጓልና ድል የሚነሣው አልነበረም። 29እንዲህም እያደረገና ጠላቶቹንም ድል እየነሣ፥ አሕዛብንም በሥልጣኑ እየገዛ ኖረ። 30ስለ ተበደሉትም ይበቀል ነበር፤ የድሃአደጉንም ፍርድ ያጸድቅ ነበር፤ 31ባልቴቶችንና ድሃአደጎችንም በችግራቸው ጊዜ ይቀበላቸው ነበር፤ የተራቡትንም ከምግብ ያጠግባቸው ነበር፤ የተራቈቱትንም ከልብሱ ያለብሳቸው ነበር። 32በጥበቡና በእጁም ሥራ ደስ ይለው ነበር፤ ከአለውም ሳይነፍግ ይሰጥ ነበር፤ ለቤተ መቅደስም ዐሥራትን ይሰጥ ነበር፤ መቃቢስም ይኽን እያደረገ ሳለ በመልካም ዐረፈ።