1የሞዓብ ሬማት ለሶርያ ቅርብ ናትና ነቢዩ ነገረው። 2ጕድጓድም ቈፍሮ እስከ አንገቱ ገባ፤ መራራ ልቅሶንም አለቀሰ፤ በእግዚአብሔር ፊት ስለ ሠራው ኀጢአቱም ንስሓ ገባ። 3እግዚአብሔርም ነቢዩን እንዲህ አለው፤ “ከይሁዳ ሀገር ወደ ሬማት ወደ ሞዓቡ ሹም ወደ መቃቢስ ተመለስ። እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል በለው፦ በኀይሌ ጽናትና በሠራዊቴ ቅድስቲቱን ከተማ አጠፋኋት እንዳትል ከተማዬን ታጠፋ ዘንድ የአንተ ፈጣሪ እኔ እግዚአብሔር በፈቃዴ ላክሁህ እንጂ ይህን ነገር ያደረግኸው አንተ አይደለህም፤ 4በስስትዋ ሁሉ፥ በክዳትዋና በሴሰኝነትዋም አሳዝናኛለችና። 5እኔም ቸል ብዬ በአንተ እጅ አሳልፌ ሰጠኋት፤ አንገትህን ስለ አደነደንህ፥ ከተማዪቱንም በእጄ ብርታት ከበብኋት ስለምትል ስለ አንተ አይደለም። አሁንም ስለ ወለድሃቸው ልጆችህ እግዚአብሔር ኀጢአትህን ይቅር አለህ። 6አሁንም በፍጹም ልቡናህ ጨክነህ ንስሓ ግባ። የሚጠራጠሩ ሰዎች ንስሓ ለመግባት አይጨክኑምና ተጠራጣሪ አትሁን። 7ነገር ግን በፍጹም ልቡናቸው ንስሓ የሚገቡ፥ ስለ ክፋታቸውም ንስሓ በገቡበት ሁሉ ወደ ጥመትና ወደ ኀጢአት የማይመለሱ ሰዎች ብፁዓን ናቸው። 8በልቅሶና በኀዘን፥ በብዙ ልመናና በስግደትም ወደ ፈጠራቸው ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ የሚጨክኑም ብፁዓን ናቸው፤ ንስሓ የገቡትን ከሳታችሁ በኋላ ንስሓ የገባችሁ እናንተ የእኔ ናችሁ ብሏቸዋልና፤ 9ትዕቢተኛውንም ከሳተ በኋላ በንስሓ ወደ እርሱ በተመለሰ ጊዜ ስለ ፍርሀትህና ስለ ድንጋጤህ ኀጢአትህን ይቅር እልሃለሁ አለው፤ የአባትን ኀጢአት በልጆች ላይ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ የማመጣ፥ ለሚወድዱኝ፥ ሕጌንም ለሚጠብቁ ግን ለእነርሱ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ ፈጣሪህ እግዚአብሔር እኔ ነኝና። 10አሁንም ስለ ወለድኻቸው ስለ እነዚህ ልጆች ከአንተ ጋራ ያለውን ቃል ኪዳኔን እጠብቃለሁ፤ ስለ ሠራኸው ኀጢአትህም ያደረግኸውን ንስሓ እቀበላለሁ ይላል ሁሉን የሚችል የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር።” 11ያንጊዜም ከጕድጓዱ ወጣ፤ “እኔ እግዚአብሔርን አሳዝኜዋለሁና የወደድኸውን አድርገኝ እንጂ ከአንተ እንዳልለይ እግዚአብሔር እንዲህና እንዲህ ያድርገኝ ብሎ ለነቢዩ ሰገደ፤ ለእኛ ሕግ የለንምና እንደ አባቶች በትእዛዙ አልሄድሁም፤ አባቶቻችንም እንዳስተማሩን ጣዖት እንደምናመልክ አንተ ታውቃለህ። 12እኔ በኀጢአቴና በልቡናዬ ትዕቢት የሔድሁ፥ በአንገቴ ደንዳናነትም ፈጣሪዬን ያሳዘንሁ ኀጢአተኛ ነኝና። እስከ አሁንም ድረስ የእግዚአብሔርን ነቢያት ቃል አልሰማሁም ነበር፤ ባዘዘኝም በሕጉና በትእዛዙ አልኖርሁም።” 13ነቢዩም መልሶ፥ “ከእናንተ አስቀድሞ ከወገናችሁ ኀጢአቱን የታመነ የለምና ዛሬ ንስሓህን እንደ ተቀበለ ዐወቅሁ” አለ። 14ከእንግዲህ ወዲያ ግን ጣዖት ማምለክን ተው፤ መመለስህ እውነተኛ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ ተመለስ፤ ከነቢዩም እግር በታች ሰገደ፤ ነቢዩም አነሣው፤ የሚገባውንም በጎ ሥራ ሁሉ አዘዘው። 15እግዚአብሔርም እንዳዘዘው አደረገ፤ ወደ ቤቱም ተመለሰ። 16ያም መቃቢስ አእምሮውን አስተካከለ፤ ከቤቱም ጣዖቱንና ጥንቆላውን፥ ጣዖት የሚያመልኩ ሰዎችንና ሟርተኞችን፥ ጠንቋዮችንም አስወገደ፤ 17ከኢየሩሳሌም ያመጣቸውንም የምርኮ ልጆች አባቶቻቸው እንደሚያደርጉ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ፥ ሥርዐቱንና ሕጉንም ያደርጉ እንደ ሆነ ጧትና ማታ ይመረምራቸው ነበር። 18ከተማረኩትም ልጆች ከዐዋቂዎቹ በቤቱ ሾመ። 19ዳግመኛም የእስራኤል ልጆች የሚያደርጉትን የእግዚአብሔርን ሕግ ያስተምሯቸው ዘንድ ወደ መኝታው የሚገቡ፥ ታናናሽ ቅምጥል ልጆቹን የሚጠብቁ ዐዋቂዎችን ከታናናሾቹ ሾመ፤ ሥርዐቱንና ሕጉን፥ አምልኮቱንና ፍርዱን፥ ሞዓባውያንም የሚያደርጉትን ሥርዐት ሁሉ ከምርኮ ልጆች ይሰማ ነበር። 20መስጊዳቸውን፥ ጥንቆላቸውንና ጣዖቶቻቸውን፥ ጧትና ማታ ከሰቡት ከፍየሎች ጠቦቶችና ከበጎች መንጋዎች፥ ለጣዖታቱ የሚሠዋውን መሥዋዕቱንና ወይኑንም ያጠፋ ነበር። 21በቀትርና በሰዓት በሥራው ሁሉ ይሰግድላቸውና ያመልካቸው ነበር፤ ይለምናቸውና ይተማመናቸውም ነበር፤ እንዲሁም ከመንገዱ በተመለሰ ጊዜ ይለምናቸው ነበር፤ የጣዖታቱ ካህናትም በነገሩት ሁሉ ፈቃዳቸውን ያደርግ ነበር። 22በነገሩ ሁሉ የሚያድኑት ይመስለው ነበርና የነገሩትን ሁሉ አይንቅም ነበር። 23ያ መቃቢስ ግን የእነርሱን መንገድ ተወ። 24ነቢይ የሚሉት የረኣዩን ነገር ከሰማ በኋላም በንስሓ መንገዱን አሣመረ፤ በዚያም ወራት ወገኖቹ ሁሉ ከእስራኤል ልጆች ይልቅ መንገዳቸውን አሣመሩ፤ የእስራኤል ልጆች አንድ ጊዜ ያሳዝኑት ነበርና በቀሠፋቸውም ጊዜ ዐውቀው ወደ እግዚአብሔር ይጮኹ ነበርና። 25መከራ በሚያጸኑባቸው በአሕዛብ እጅ ተይዘው እንደ ተዋረዱ፥ ወደ እርሱም እንደ ጮሁ በሰማ ጊዜ የአባቶቻቸውን መሐላ አስቦ የዚያን ጊዜ ስለ አባቶቻቸው ስለ አብርሃምና ስለ ይስሐቅ፥ ስለ ያዕቆብም ይቅር ይላቸው ነበር። 26በአዳናቸውም ጊዜ ያዳናቸውን ይረሱት ነበር፤ ጣዖታቱንም ወደ ማምለክ ይመለሱ ነበር። 27ያንጊዜም በመከራ የሚያሠቃዩአቸው አሕዛብን ያስነሣባቸው ነበር፤ በአሠቃዩአቸውና ባሳዘኑአቸውም ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ይጮሁ ነበር፤ የዚያን ጊዜም ራርቶ ይቅር ይላቸው ነበር። የእጁ ፍጥረት ስለ ሆኑ ይወድዳቸው ነበርና። 28ዳግመኛም በሚጠብቃቸው ጊዜ በዙሪያቸው ያለ ጣዖትን በማምለክና በክፉው የእጃቸው ሥራ ያሳዝኑት ዘንድ ይመለሱ ነበር። 29እርሱ ግን የኢሎፍሊንና የሞዓብን፥ የምድያምንና የሶርያን፥ የግብፅንም ሕዝብ ያስነሣባቸው ነበር፤ ጠላቶቻቸውም ድል በነሷቸው ጊዜ፥ መከራ በአጸኑባቸውና በአስገበሯቸው ጊዜ፥ በገዟቸውም ጊዜ ይጮሁና ያለቅሱ ነበር፤ እግዚአብሔርም በወደደበት ጊዜ ያድኗቸው ዘንድ መሳፍንትን ያስነሣላቸው ነበር፤ መሳፍንቱም ያድኗቸው ነበር።