1ረአይ የሚሉት ነቢይ እንዲህ አለው፥ “በጊዜው ብርሃን ዛሬ ጥቂት ደስ ይበልህ፤ የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔርም ባልተጠራጠርኸው መቅሠፍት ይበቀልህ ዘንድ አለው። 2ፈረሶች ፈጣኖች ናቸው፤ ስለዚህም በሩጫ አመልጣለሁ ትላለህን? 3እኔስ የሚከተሉህ ሰዎች ከአሞሮች ይፈጥናሉ፤ ከጥፋትና ከሚመጣብህ ከእግዚአብሔር ቍጣ አታመልጥም እልሃለሁ። 4የብረት ልብስ እለብሳለሁ፤ የጦር መወርወርና የቀስትም መንደፍ አይችለኝም ትላለህን? የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔርም የምበቀልህ በጦር መወርወር አይደለም ይላል፤ ነገር ግን ከጦር መወርወርና ከቀስት ንድፈት የሚከፋ ጽኑ የልብ በሽታን፥ እከክንና ቍርጥማትን አመጣብሃለሁ፤ 5ቍጣዬን አነሣሥተሃልና፥ የልብ በሽታን አመጣብሃለሁ፤ የሚረዳህም ታጣለህ፤ ስም አጠራርህንም ከምድር እስካጠፋው ድረስ ከእጄ አታመልጥም። 6አንገትህን አደንድነሃልና ራስህንም በከተማዬ ላይ ከፍ ከፍ አድርገሃልና፥ ይህን ነገር እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥኜ ባደረግሁ ጊዜ እኔ ፈጣሪህ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቀኛለህ፤ አንተ በፊቴ እሳት እንደሚበላው በነፋስ ፊት እንዳለ ሣር ነህና፥ ዓውሎ ነፋስም ከምድር አፍሶ እንደሚበትነው ትቢያ ነህና አንተ በእኔ ዘንድ እንዲሁ ነህ። 7ቍጣዬን አነሣሥተሃልና፥ ፈጣሪህንም አላወቅህምና እኔም የአንተ የሆነውን ሁሉ ቸል እለዋለሁ፤ በአንባህም ሁሉ ላይ የሚጠጋውን አላስቀርም። 8አሁንም ከሠራኸው ክፋት ሁሉ ተመለስ፤ ብትመለስ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ፈጽመህ በልቅሶና በኀዘን ብትናዘዝ፥ በንጹሕ ልቡናም ወደ እርሱ ብትለምን በፊቱ የሠራኸውን ኀጢአትህን ሁሉ እግዚአብሔር ይቅር ይልሃል።” 9የዚያን ጊዜም መቃቢስ ትቢያ ለብሶ ስለ ኀጢአቱ በእግዚአብሔር ፊት አለቀሰ። እግዚአብሔር ተቈጥቶታልና። 10እግዚአብሔርም በነቢዩ ቃል የተናገረውን መቅሠፍት እንደማያዘገይ ዐወቀ። ዐይኖቹ የተገለጡ ናቸውና አይተኛም፤ ዦሮውም የተከፈተ ነውና ቸል አይልም፤ የተናገረውንም ቃል ሐሰት አያደርግምና በአንዲት ጊዜ እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥኖ ያደርጋታል። 11ልብሱንም ጥሎ ማቅ ለበሰ፤ በራሱም ላይ ትቢያ ነሰነሰ፤ ስለ ሠራውም ክፋት በፈጣሪው በእግዚአብሔር ፊት ጮኸ፤ አለቀሰም።