1መቃቢስ አይሁድን በሶርያ በሁለቱ ወንዞች መካከል አግኝቶ ከኢያቦቅ ጀምሮ እስከ ኢየሩሳሌም አደባባይ ድረስ በሸለቆዎቻቸው እንደ ገደላቸው፥ ቅድስቲቱንም ከተማ እንዳጠፋት የሚናገር መጽሐፍ ይህ ነው። 2ከሰማርያ ጀምሮ እስከ ኢየሩሳሌም አደባባይ ድረስ፥ እስከ አውራጃዋም ሁሉ ድረስ ሰፍረዋልና ከጥቂቶች በቀር ሳያስቀሩ በጦር ገደሉ። ኤዶማውያንና ሶርያውያን፥ አማሌቃውያንም የኢየሩሳሌምን ከተማ ካጠፋው ከሞዓብ ሰው ከመቃቢስ ጋር አንድ ሆነዋልና። 3የእስራኤልም ልጆች በበደሉ ጊዜ ሞዓባዊውን መቃቢስን አስነሣባቸው፤ እርሱም ሁሉን በሰይፍ ገደላቸው። 4ስለዚህም ነገር የእግዚአብሔር ጠላቶች በቅድስት ከተማው ላይ ደነፉ፤ በወንጀላቸውም ተማማሉ። 5ኤዶማውያንና ኢሎፍላውያንም ሰፈሩ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ተገዳደሩ እርሱ ልኳቸዋልና የእግዚአብሔርን ከተማ ይበቀሉ ጀመር። 6የዚያም የመቃቢስ ሀገሩ የሞዓብ ሬማት ናት፤ ከሀገሩም በኀይል ተነሥቶ አብረውት ከአሉ ሰዎች ጋራ ተማማለ። 7የእግዚአብሔርንም ከተማ ያጠፉ ዘንድ በመስጴጦምያ-ጌላቡሄ ሸለቆዎች እስከ ሶርያ ድረስ ሰፈሩ፤ በዚያም ኢሎፍላውያንንና አማሌቃውያንን ለመነ፤ በወንጀልም ከእርሱ ጋራ አንድ ይሆኑ ዘንድ ብዙ ወርቅንና ብርን፥ ፈረሶችንና ሠረገላዎችን ሰጣቸው። 8በአንድነትም መጥተው አንባዪቱን ናዷት፤ በውስጧ የሚኖሩ ሰዎች ደምንም እንደ ውኃ አፈሰሱ። 9ኢየሩሳሌምንም እንደ ተክል ጠባቂ ጎጆ አደረጓት፤ በውስጧም ድምፅ አሰማባት፤ እግዚአብሔርም የማይወድደውን የክፋት ሥራ ሁሉ አደረገ፤ ጽድቅንና ቅድስናን የተመላች የእግዚአብሔርንም ከተማ አረከሱ። 10“የባሮችህን እሬሳ ለሰማይ ወፎች ምግብ አደረጉ። የጻድቃንህንም ሥጋ ለምድረ በዳ አራዊት መብል አደረጉ።” 11ባልቴቲቱንና የሙት ልጁን ቀሙ፤ ሰይጣን እንዳስተማራቸው እግዚአብሔርን ሳይፈሩ አድርገዋልና ኵላሊትንና ልቡናን የሚመረምር እግዚአብሔር እስኪቈጣ ድረስ በፀነሱ ሴቶች ሆድ ያለውን ፅንስ አወጡ። 12በእግዚአብሔር ሕዝብም ላይ ክፉን ስለ አደረጉ ደስ እያላቸው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፤ ከቅድስት ከተማ የማረኩትንም ምርኮ ወሰዱ። 13ተመልሰውም ወደ ቤታቸው በገቡ ጊዜ ደስታን፥ ዘፈንንና ጭብጨባን አደረጉ።