1“የጌላቡሄ ሸለቆዎችና የሊባኖስ ተራሮች ከእግዚአብሔር ዘንድ የምሕረት ዝናም ካልዘነመላቸው ለእንስሳዎችና ለአውሬዎች ሣርን አያበቅሉም። 2የገለዓድ ተራራዎችና የኤላም ሸለቆዎች ለሚሠማሩ ለፍየሎችና ለበጎች፥ ለዱር እንስሳት ለፌቆና ለቶራትም፥ ለዋሊያዎችም ልምላሜን አይሰጡም። 3እንደዚሁም ክሕደትንና ስሕተትን አስቀድሞ ገንዘብ ያደረጓት ከሓዲዎችና መናፍቃን ከእግዚአብሔር የምሕረት ጠል ካልወረደላቸው ሙታን አይነሡም፤ ጣዖት የሚያመልኩና ሥር የሚምሱ፥ ነገር ሠርተው የሚያጣሉ፥ ቆጵሮስና ዲማሶ፥ 4ሥር የሚምሱ፥ ጥንቆላንና ሥራይን የሚያደርጉ፥ ሰውንም የሚያጋድሉ፥ 5ከሕግም ወጥተው የሚሰስኑ፥ በጣዖታቸውም የሚታመኑ የአቴናና የሜዶን ሰዎች፥ በመሰንቆና በከበሮ፥ በበገናም የሚጫወቱላቸውና የሚዘፍኑላቸውም፥ 6በጣዖታቸው የሚስቱ፥ በእጃቸውም ሥራ የሚሰስኑ፥ በትንሣኤ ጊዜ በፍርድ ቀን ራሳቸውን የማያድኑና የሚፈረድባቸው እነዚህ ናቸው። 7“አንተ ሰነፍና ልበ ባካና ሙታን የማይነሡ ይመስልሃልን? 8በሙታን ትንሣኤ በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል አፍ መለከት በሚነፋ ጊዜ በዚያ እንደ አንቀላፋህ አትቀርምና እንዲህ አታስብ። 9ተራሮችና ኮረብቶች ዝቅ ይላሉ፤ ወንዞችና ጥልቆች ይስተካከላሉ፤ ጥርጊያ ጎዳናም ይሆናሉ። 10ለሥጋ ለባሽም ሁሉ ትንሣኤ ይሆናል።