1“ስለ ሙታን ትንሣኤም ስማኝ ልንገርህ፤ ዛፎች ይተከላሉ፤ ቅርንጫፎችንም ያወጣሉ፤ ወይንም ሐረግ ያወጣል፤ እግዚአብሔር ፍሬውን ካለመኖር ያመጣዋልና ከእርሱ የወይን ጠጅ ይጥላሉ። 2እስኪ ተመልከት፤ ያች የተከልሃት ዛፍ ታናሽ ነበረች። ዛሬ ግን ጫፎችን፥ ቅጠልንና ፍሬን አውጥታለች። 3እግዚአብሔርም ከሁለት ጡቶች ከውኃና ከመሬት ሥርዋን ያጠጣል። 4እንጨቶችዋን ግን ከነፋስና ከፀሐይ ይመግባቸዋል፤ ሥር ለቅጠል ውኃ ታጠጣለች፤ መሬትም ለእንጨቶች ጽናትን ትሰጣለች። 5እግዚአብሔር የፈጠረው ነፋስም በመካከላቸው ፍሬን ይሰጣል። የሞቱ ሰዎችም ትንሣኤ እንደዚሁ ነው። 6“ነፍስ ከሥጋ በተለየች ጊዜ እየራሱ ሂዷልና ከውኃና ከመሬት፥ ከእሳትና ከነፋስ፥ ከአራቱ ማዕዘናት ነፍሳትን ሰብስብ አለ። 7የመሬት ባሕርይ ግን በራስዋ ጸናች፤ ዐመድም ሆነች፤ የውኃ ባሕርይም በራሷ ጸናች፤ ጠልም ሆነች። 8የነፋስ ባሕርይም በራስዋ ጸናች፤ ነፋስም ሆነች፤ የእሳት ባሕርይም በራስዋ ጸናች፤ የሚሞቅ እሳትም ሆነች። 9እግዚአብሔር የፈጠራት ነፍስ ግን ወደ ፈጣሪዋ እጅ ተመለሰች፤ በወደደም ጊዜ ይመልሳታልና በወደደው ቦታ ያኖራታል። 10የጻድቃንን ነፍሳት በብርሃን ቤት ያኖራቸዋል፤ የኃጥኣንን ነፍሳት ግን ያወጣቸው ዘንድ እስከ ወደደበት ጊዜ ድረስ በጨለማ ቤት ያኖራቸዋል። 11“ነቢዩ ሕዝቅኤልንም እንዲህ አለው፦ ይሰበሰቡና አንድ አካል ይሆኑ ዘንድ ከአራቱ ማዕዘን ጥራ። 12እንዲህም ብሎ ባንድ ቃል በተናገረ ጊዜ ከአራቱ ማዕዘን ተሰበሰቡ። 13የውኃ ባሕርይም ጠልን አመጣ፤ ዳግመኛም የእሳት ባሕርይ ሙቀትን አመጣ። 14የመሬት ባሕርይም ዳግመኛ መሬትን አመጣ፤ የነፋስ ባሕርይም እስትንፋስን አመጣ። 15እግዚአብሔርም ነፍስን ካኖረበት ከማደሪያዋ አመጣ፤ በአንድ ቃል ተሰበሰቡ፤ ትንሣኤም ሆነ። 16“ዳግመኛም በአንተ ዘንድ ያለ ምሳሌን አሳይሃለሁ፤ ቀኑ ይመሻል፤ ትተኛለህም፤ ሌሊቱ ይነጋል፤ ከመኝታህም ትነሣለህ፤ አንተ ግን በተኛህ ጊዜ የሞትህ ነህ። 17በነቃህም ጊዜ የትንሣኤ ምሳሌ ነው፤ ሌሊቱ ግን ሁለንተናው ጨለማ የሆነ የዚህ ዓለም ምሳሌ ነው። ዓለም ሁሉ ይተኛበታል፤ የሌሊት ጨለማ ሸፍኖአቸዋልና። 18ጨለማ የሚወገድበት፥ በዓለሙም ሁሉ ብርሃን የሚሆንበት፥ ሰውም ተነሥቶ ወደ ሥራው የሚሠማራበት የጧት ብርሃን ግን የሙታን ትንሣኤ ምሳሌ ነው። 19ይቺ የዓለም መታደስና የሙታን ትንሣኤ እንደዚህ ናት፤ ይህ ዓለም በዚህ ሌሊት አምሳል ኀላፊ ነውና። 20“ዳዊትም ምሳሌውን በፀሐይ አኖረ ብሎ እንደ ተናገረ ፀሐይ በወጣና በአበራ ጊዜ የዚህ ዓለም ምሳሌው ነው። 21ዛሬ በዚህ ዓለም እንደሚያበራው ፀሐይ እርሱ እግዚአብሔር በሚመጣ ጊዜ ለሐዲሲቱ ዓለም ያበራላታል፤ እንደ ፀሐይ ያበራል፤ የማይጠልቅ ፀሐይ፥ የማይጠፋም ፋና እኔ ነኝ ብሏልና እርሱ እግዚአብሔር ብርሃንዋ ነው። 22ዳግመኛም የሞቱትን ሰዎች እንደ ዐይን ጥቅሻ ያስነሣቸዋል፤ ዳግመኛም ከምትዘራው፥ አንተም በሕይወት ከምትኖርበት ከምግብህ አንዲት ምሳሌ አመጣልሃለሁ፤ የስንዴም ቅንጣት ቢሆን፥ የገብስም ቅንጣት ቢሆን፥ የምስርም ቅንጣት ቢሆን በምድር የሚዘራ የሰው ተግባር ሁሉ ካልፈረሰ የሚበቅል የለም። 23እንደምታየው እንደ ሰው ሥጋ ሁሉ በሚፈርስበት ጊዜ ፍሬው ከገለባው ጋር በመሬት ይበላል። 24ፍሬውም በተበላ ጊዜ የቅንጣት ሰባተኛ እጅ ያህል ሆኖ ይበቅላል፤ እግዚአብሔርም እንደ ወደደ የሕይወት ነፋስን ይሰጣል፤ ሥርም በምድር ውስጥ ትበቅላለች፤ ቅጠልንም በምድር ላይ ታወጣለች። 25እስቲ ተመልከት፤ እርሷ ካልፈረሰች መብቀል አትችልም፤ ከበቀለች በኋላ ግን ብዙ ዝርዝር ታወጣለች። 26ላደገው ለዚያ ለዝርዝሩም ከእግዚአብሔር ፍሬ ይሰጠዋል፤ ፍሬውንም ገለባ ያለብሰዋል። 27የዘራኸው ዘር ቅንጣቱ እንደበዛ መጠን እይ እንጂ ቅጠሉ፥ ብርዑ፥ ገለባውና ምርቁ ግን አይቈጠርልህም። 28“ሰነፍ አትሁን፤ ዘርህንም እንደ በዛ እይ፤ እንደዚሁም ሁሉ የሙታንን ትንሣኤ፥ እንደ ሥራቸውም እንደሚከፈላቸው አስብ። 29ዳግመኛም ዘር ወደ ሌላ ዘር እንደማይለወጥ ስማኝ፤ ልንገርህ፤ ስንዴ ብትዘራ ገብስ ትሰበስባለህን? ከሙን ብትዘራ ተልባ ትሰበስባለህን? 30ከተክልስ ወገን በለስ ብትተክል በውኑ ለውዝ ሆኖ ይበቅልልሃልን? ገውዝስ ብትተክል ወይን ሆኖ ይበቅልልሃልን። 31ጣፋጭ ፍሬ ብትተክል የመረረ ሆኖ ይበቅልልሃልን? የመረረውንስ ፍሬ ብትተክል የጣፈጠ ሆኖ ይበቅልልሃልን። 32እንደዚሁስ ሁሉ ኀጢአተኛ ቢሞት በትንሣኤ ጊዜ ጻድቅ መሆን ይችላልን? ጻድቅስ ቢሞት በትንሣኤ ጊዜ ኃጥእ መሆን ይችላልን? ሁሉም እንደ ሥራው ይከፈለዋል፤ እንደ ሥራው ፍሬ፥ እንደ እጁም ሥራ ይከፈለዋል እንጂ፥ በሌላ ኀጢአት የሚፈረድበት የለም። 33የሊባኖስ ዛፍ ይተከላል፤ ረጃጅምና ታላላቅ ቅርንጫፎችንም ያወጣል፤ ይደርቅና ይረግፋል እንጂ፥ የአርሞንኤም ጠል ካልዘነመበት ቅጠሉ አይለመልምም። 34ዝግባውም የክረምት ዝናም በእርሱ ካልወረደ ከሥሩ ይነቀላል። 35እንደዚሁም ሁሉ ከእግዚአብሔር የሕይወት ጠል ካልወረደላቸው ሙታን አይነሡም።