1“አንተ ንጉሥም ብትሆን፥ ገዥም ብትሆን አንተ ምንድን ነህ? የፈጠረህ እግዚአብሔር አይደለምን 2ፈቃዱን ታደርግ ዘንድ፥ በትእዛዙም ትሔድ ዘንድ፥ ፍርዱንም ትፈራ ዘንድ ካለመኖር ወደ መኖር አመጣህ፤ አንተ ባሮችህን እንደምትቈጣቸው፥ በላያቸውም እንደ ሠለጠንህ እንደዚሁም ሁሉ አንተንም የሚቈጣህ፥ በላይህም የሠለጠነ አለ። 3አንተ ኀጢአት የሠሩ ሰዎችን ያለ ርኅራኄ እንደምትመታ እንደዚሁም ሁሉ አንተንም የሚመታህ፥ እስከ ዘለዓለም ድረስ መውጫ ወደሌለበት ፍርድም የሚጨምርህ እግዚአብሔር አለ። 4ያልተገዛልህን፥ እጅ መንሻም ያላመጣልህን አንተ እንደምትገርፈው አንተ ለእግዚአብሔር ለምን እጅ መንሻ አታገባም? 5አንተን ይፈሩህ ዘንድ እንደምትወድ አምላክህን እግዚአብሔርን ለምን አትፈራውም? ሕዝቡንና መንጋውን በእውነት ትጠብቅ ዘንድ የፈጠረህና በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ያነገሠህ እርሱ ነውና። 6“እግዚአብሔር እንደ ሾመህ በሚገባና በእውነት ፍረድ እንጂ ለታላቅና ለታናሽ ፊት አታድላ፤ ያለ እርሱ ማንን ትፈራለህ? መንገዱንና ትእዛዙን ጠብቅ። 7እሳትንና ውኃን አቀረብኩልህ፤ እጅህን ወደ ወደድኸው ጨምር ብሎ ሙሴ የእስራኤልን ልጆች እንዳዘዛቸው ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አትበል። 8ቃሉን ትሰማ ዘንድ፥ ትእዛዙንም ታደርግ ዘንድ የምነግርህን ቃሉን ስማ፤ በባሕር ማዶ፥ ወይም በጥልቁ ማዶ፥ ወይም በወንዙ ማዶ ቃሉ አለች፤ አያት ዘንድ፥ ቃሉንም እሰማ ዘንድ፥ የእግዚአብሔርንም ትእዛዙን አደርግ ዘንድ ማን ያመጣልኛል? እንዳትል፥ 9ዳግመኛም ሰምቼ አደርጋት ዘንድ ወደ ሰማይ ወጥቶ ያቺን የእግዚአብሔርን ቃል ማን ያወርድልኛል? እንዳትል እነሆ ቃሉ በአፍህ ቅርብ ነው። በእጅህም ውስጥ ነው። 10መጽሐፉንም ካልሰማኸው አምላክህ እግዚአብሔርን አልሰማኸውም፤ ቃሉንም ካልጠበቅህ እርሱን አልወደድኸውም፤ ትእዛዙንም አላደረግህም። 11አንተም ትእዛዙን ካልወደድህ በእውነትም ትጠብቃቸው ዘንድ ከወገኖችህ ሁሉ ለይቶ ያከበረህንና ያገነነህን ፈቃድ ካላደረግህ ለዘለዓለም ወደ ፍርድ ትገባለህ። 12የፈጠረህን የአምላክህን ስም እንድታስብ በሕዝቡ ሁሉ ላይ የበላይና አለቃ አደረገህ። በእውነትና በሚገባም ወገኖቹን ትገዛ ዘንድ ሰጠህ 13አንተን ከበደሉህ ሰዎችም የምትቀጣቸው አሉ፤ የእግዚአብሔርን መንገድ እያሰብህ፥ ልቡናህንም እያቀናህና በሚገባ እየፈረድህ የምትምረውም አለ። 14በፊትህም በተከራከሩ ጊዜ ፊት አይተህ አታድላ፤ ምድር ሁለንተናዋ ያንተ ገንዘብ ናትና ኀጢአተኛውን ሰው ትምረው፥ ንጹሑንም ሰው ትበድለው ዘንድ መማለጃ አትቀበል። 15“ፈቃዱንም ካደረግህ በምድር ላይ ዕድሜህን ያበዛልሃል፤ ብታሳዝነው ግን ዕድሜህን ያሳንሰዋል። 16ከሞት እንደምትነሣ፥ በጎም ቢሆን፥ ክፉም ቢሆን በሠራኸው ሥራ ሁሉ በፊቱ ቁመህ እንደምትመረመር አስብ። 17በጎ ሥራ ብትሠራ በደጋግ ነገሥታት ማደሪያ በብርሃን ቤቶች ትኖራለህ። ክፉ ሥራ ብትሠራ ግን በክፉዎች ነገሥታት ማደሪያ ትኖራለህ። 18እግዚአብሔር የጌትነትህን ሥልጣን አያፍርም፤ አንተ ግን የመፈራትህን ገናንነት፥ የአርበኞችህንም ሽልማት፥ የተሰቀለ የጦር መሣሪያህንም ባየህ ጊዜ፥ ፈረሶችህንም፥ ከሥልጣንህ በታች ያሉ ጭፍሮችህንም፥ መለከት የሚነፉትንና በፊትህም በበገና የሚጫወቱትን ሰዎች በአየህ ጊዜ፥ 19አንተ ይኽንን ሁሉ በአየህ ጊዜ ሕሊናህን ከፍ ከፍ ታደርጋለህ፤ አንገትህንም ታደነድናለህ፤ ይኽን ሁሉ ክብር የሰጠህንም አታስበውም፤ ተው ባለህ ጊዜ አንተ የምትተወው አይደለህምን? 20የሾመህን ሹመትም ፈጽመህ ቸል ብለሃልና ክብርህን ለሌላ ይሰጠዋል። 21ድንገት ሞት ይመጣብሃልና፥ በትንሣኤም ጊዜ ፍርድ ይደረጋልና፥ የሰውም ሥራ ሁሉ ይመረመራልና በዚያ ይመራመርሃል፤ ይቈጣጠርሃልም፤ ይፈርድብሃልም። 22የምድርን ነገሥታትም የሚያከብራቸው የለም፤ እርሱ የእውነት ዳኛ ስለሆነ በፍርድ ጊዜ ድሃና ባለጸጋ በአንድነት ይቆማሉና። የምድር መኳንንት የሚመኩበት ዘውዳቸው ይወድቃል። 23“ፍርድ የተዘጋጀ ነው፤ ነፍስም ትንቀጠቀጣለች፤ መጻሕፍትም ይገለጣሉ፤ የሰዎችም ሥራ ይገለጣል፤ የሚሰወርም የለም። 24ሴት ለመውለድ በደረሰች ጊዜ፥ በሆዷም ያለ ፅንስ ለመወለድ በደረሰ ጊዜ ማኅፀኗን ለመከልከል እንደማትችል ምድር በሙታን ትንሣኤ ጊዜ በርሷ ላይ ያለ አደራዋን ትመልሳለች። 25ወይስ ደመናዎች እግዚአብሔር ወዳዘዛቸው ቦታ ወስደው እንዳያዘንሙ ዝናምን መቋጠር ይችላሉን? እንደዚሁም የእግዚአብሔር ቃል ሁሉን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ፈጥሮታልና፥ ዳግመኛም የእግዚአብሔር ቃል ሁሉን ወደ መቃብር አግብቶታልና የትንሣኤ ጊዜ ከደረሰ በኋላ የሞቱ ሰዎች እንዳይነሡ ማድረግ አይቻልም። 26ዳግመኛም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ነው እንጂ ሰው የሚድን በእህል ብቻ አይደለም ብሎ ሙሴን እንደ ተናገረ የእግዚአብሔር ቃል ሰውን ሁሉ ከመቃብር ያስነሣዋል። 27እነሆ የሞቱ ሰዎች በእግዚአብሔር ቃል ሕያዋን እንደሚሆኑ ታወቀ። 28ዳግመኛም ስለ ነገሥታትና መኳንንት፥ ፈቃዱንም ስለሚያደርጉ ሰዎች እግዚአብሔር በዳግም ሕግ እንዲህ አለ፦ የሚቈጠሩበት ቀን ደርሷልና በፍርድ ቀን እግራቸው በሚሰናከልበት ጊዜ እበቀላቸዋለሁ። 29“ዳግመኛም የእግዚአብሔርን ፍርድ የማያውቁ ሰዎችን እግዚአብሔር እንዲህ አላቸው፦ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ዕወቁ፤ እኔ እገድላለሁ፥ አድናለሁም። 30እቀሥፋለሁ፤ ይቅርም እላለሁ፤ ወደ ሲኦል አወርዳለሁ፤ ዳግመኛም ወደ ሰማይ አወጣለሁ፤ ከእጄም የሚያመልጥ የለም። 31ሕጉን ስላልጠበቁ ነገሥታትና መኳንንት እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ ምድራዊ መንግሥት ኀላፊ ነውና፥ ከጧት እስከ ማታም ድረስ ያልፋልና ወደ ዘለዓለማዊው መንግሥቴ ትገቡ ዘንድ ሕጌንና ሥርዐቴን ጠብቁ። 32የእግዚአብሔር ጥሪው ለክብርም፥ ለአሣርም ነውና ይህን ያዋርዳል፤ ያንም ያከብራል። 33ፈቃዱን ያላደረገውን ይሽረዋል፤ ፈቃዱን ያደረገውንም ይሾመዋል።