1“ፈቃዱን የሚያደርጉ ነገሥታቱን በእውነት ያነግሣቸዋልና ነገሥታቱ ስለ እርሱ የቀና ነገርን ጻፉ። 2አብርሃምና ይስሐቅ፥ ያዕቆብም፥ ዳዊትና ሰሎሞን፥ ሕዝቅያስም፥ ማደሪያቸው ብርሃን የሆነች ደጋጉ ነገሥታትም ሁሉ ባሉበት ማደሪያቸውን በማይመረመር ብርሃን ያበራል፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርገዋልና። 3በምድር እንደ አለ አዳራሽም አይደለም፤ ነገር ግን ፈጽሞ ብሩህ የሆነ በሰማይ ያለ አዳራሽ ነው፤ የወርቅ፥ የብርና የዕንቍ የሆነ ወለሉም ንጹሕ ነው። 4ፈጽሞ የሚያበራ መልኩም ከሰው ልቡና የራቀ ነው፤ የመንግሥተ ሰማያት አዳራሽ በጳዝዮንና በመረግድ፥ በጠልማና በወራውሬ የሚያበራ ነው። 5ከሰው ሕሊና ባለፈ በከበረ ዕንቍ እጅግ የሚያበራ የመንግሥት አዳራሽ ነው። እርሱ ራሱ እግዚአብሔር እንደሚያውቅ የሠራው የመንግሥተ ሰማያት አዳራሽ ነው። የወርቅና የብር፥ የሰማያዊ ዕንቍና የአረንጓዴ ዕንቍ፥ የብጫ ዕንቍና የነጭ ሐር መልክ ያለው ወለሉም ንጹሕ ነው። 6እንደዚህ እጅግ ፈጽሞ ያማረ ነው፤ ንጹሕና ብሩህ ነው። 7በጽድቅና በእውነት የተታታ ነው፤ በይቅርታና በምሕረትም የተሠራ ነው። 8ከእርሱም የሚፈስስ የሕይወት ውኃ አለ፤ እንደ ፀሐይም እጅግ የነጻ ነው፤ የብርሃን ድንኳንም አለ፤ በኤርሞን ሽቱም የተከበበ ነው። 9በቤቱም ዙሪያ መልኩና መዓዛው ልዩ የሆነ ጣፋጭ የገነት ፍሬ ተተክሏል። በዚያም የወይንና የዘይት ቦታ አለ፤ ፈጽሞም ያማረ ነው፤ የፍሬውም መዓዛ የጣፈጠ ነው። 10ሥጋዊ ሰው ወደ እርሱ ቢገባ፥ ከመዓዛውም ጣዕም የተነሣ ከደስታው ብዛት ነፍሱ ከሥጋው በተለየች ነበር። 11“በዚያም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያደረጉ ደጋግ ነገሥታት ደስ ይላቸዋል፤ ሥራቸውም ቦታቸውም በመንግሥተ ሰማያት በዘለዓለም ሕይወት ቦታ የታወቀ ነው። 12በምድር እንደ አለ የመንግሥታቸው ክብር በሰማይ እንደ አለ እንዲሁ በምድር አሳየ፤ በምድርም እንደሚያከብሯቸውና እንደሚሰግዱላቸው በሰማይ ይከብራሉ፤ ከፍ ከፍም ይላሉ፤ በዚህ ዓለምም በጎ ሥራ ቢሠሩ ደስ ይላቸዋል። 13እግዚአብሔር በሰጣቸው መንግሥታቸውና ግዛታቸው ክፉ የሆኑ ነገሥታት ግን በእውነትና በሚገባ አይፈርዱም፤ የድሆችንና የጦም አዳሪዎችን ጩኸት ቸል ብለዋልና፥ የተገፋውንና መጻተኛውን፥ አባትና እናት የሞቱበትንም አያድኑም። 14ድሆችንና ጦም አዳሪዎችን ከሚቀማቸው እጅ አያድኑአቸውም፤ ከምግባቸው የተራቡትን አያጠግቡም፤ ከመጠጣቸውም የተጠሙትን አያጠጡም፤ ጆሯቸውንም ወደ ድሃው ጩኸት አልመለሱም። 15እነርሱንም የጨለማ መጨረሻ ወደ ሆነ ወደ ሲኦል ማደሪያ ይወስዷቸዋል፤ እግዚአብሔር የፈጠራት ታላቋ ዕለት፥ ቍጣውም በደረሰችባቸው ጊዜ ዳዊት በመዝሙሩ “አቤቱ በቍጣህ አትቅሠፈኝ፤ በመቅሠፍትህም አትገሥጸኝ” ብሎ እንደ ተናገረው እንደ ገናንነታቸው ብዛት መጠን ችግራቸውና ውርደታቸው ይበዛል። 16“ነገሥታትና መኳንንት በምድር ይህን ዓለም የሚገዙ ሲሆኑ ሕግህን ያልጠበቁ ሰዎችን ይወስዱአቸዋል። 17በሰማይ ግን ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር አለ፤ የሁሉ ነፍስ በእጁ ነው፤ የሁሉም ሕይወት በአፉ ነው፤ ለሚያከብሩት ሰዎችም ክብርን የሚሰጣቸው እርሱ ነው፤ ሁሉን የሚችል ነውና፥ ሁሉንም ይገዛልና የሚወዱትንም ይወድዳቸዋል። 18እርሱ የሰማይና የምድር ንጉሥ ልብንና ኵላሊትን ይመረምራል፤ ወደ እርሱም በንጹሕ ልቡ የጸለየውን የጸሎቱን ዋጋ ይሰጠዋል። 19በባልቴቶችና በሙት ልጅ ክፉ የሚሠሩ የኀይለኞች ትዕቢትን ያጠፋል። 20ይህን መንግሥት የያዝኸው በኀይልህ አይደለም፤ በዚህም ዙፋን ላይ የተቀመጥህ በችሎታህ አይደለም፤ ነገር ግን ሕዝቡን መግዛት ትችል እንደ ሆነ፥ በዚያ ወራት ወገኖቹን ሲገዛ የእግዚአብሔርን ቃልና የሳሙኤልን ቃል ቸል እንደ አለና የአማሌቅን ንጉሥና ሠራዊቱን እንደ አልገደለ እንደ ሳኦል ይፈትንህ ዘንድ ፈቅዶ በመንግሥት ዙፋን ላይ አስቀመጠህ። 21እግዚአብሔርም ነቢዩ ሳሙኤልን ሔደህ ሕግ በማፍረስና ጣዖቶቹን በማምለክ፥ ለጣዖቱም በመስገጃዎቹ ውስጥ በመስገድ፥ ጥቅም በሌለው በረከሰ ሥራቸውም ሁሉ አሳዝነውኛልና ሳኦልን ወደ አማሌቅ ሀገር ሔደህ ከሰው ጀምሮ እስከ ከብት ድረስ ነገሥታቱንና ሠራዊቶቻቸውን ሁሉ አጥፋ በለው ብሎት ነበርና። 22ስለዚህም እግዚአብሔርን ባሳዘኑት ጊዜ ያጠፋቸው ዘንድ ላከው። 23እርሱ ግን ንጉሣቸውን አዳነው፤ ብዙ ከብትንም፥ ሴቶችንና ደናግልን፥ ከጐልማሳዎችም መልካማዎችን አዳነ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ነቢዩ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ ቃሌን አቃሎአልና፥ ትእዛዜንም አልሰማምና ሔደህ መንግሥቱን ክፈላት። 24በእርሱ ፋንታ በእስራኤል ላይ ይነግሥ ዘንድ የዕሤይን ልጅ ዳዊትን ቅባው። 25በእርሱ ግን አንቆ የሚጥለው ጋኔንን አሠልጥንበት። 26ፈቃዴን ያደርግ ዘንድ መንግሥትን ብሰጠው እንቢ ብሏልና ፈቃዴን ማድረግ እንቢ ባለም ጊዜ ከክብሩ ሻርሁት፤ አንተ ግን ሄደህ ንገረው፤ እንዲህም በለው፦ በወገኖቹ በእስራኤል ላይ ያነገሠህን፥ በመንግሥት ዙፋን ላይም ያስቀመጠህን እግዚአብሔርን እንዲህ ቸል ትለዋለህን? 27አንተ ግን ይህን ያህል ታላቅ ክብርንና ገናንነትን የሰጠህን እግዚአብሔርን አላወቅህም። 28“ነቢዩ ሳሙኤልም ወደ ንጉሡ ወደ ሳኦል ሄደ። በማዕድ ተቀምጦ፥ የአማሌቅ ንጉሥ አጋግም በግራው ተቀምጦ ሳለ ወደ እርሱ ገባ። 29ሰውንና እንስሳን ታጠፋ ዘንድ ያዘዘህን እግዚአብሔርን ፈጽመህ ለምን ቸል አልኸው? አለው። 30የዚያን ጊዜም ንጉሡ ፈርቶ ከዙፋኑ ተነሣ፤ የሳሙኤልንም ልብስ ያዘው፤ ሳሙኤልም መመለስን እንቢ አለ፤ የሳሙኤልም ልብስ ተቀደደ። 31ሳሙኤልም ሳኦልን፦ እግዚአብሔር መንግሥትህን ከፈላት አለው። 32ዳግመኛም ሳኦል ሳሙኤልን፦ በሕዝቡ ፊት አክብረኝ፤ ይቅር ይለኝም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአቴን አስተስርይልኝ አለው፤ ሳሙኤልም ቃሉን ለመለወጥ እንቢ አለ። የፈጣሪውን እግዚአብሔርን ቃል ፈርትዋልና፥ የሚሞት ንጉሥን ግን አልፈራውምና። 33ስለዚህም ነገር ያላመጠውን ሳይውጠው የአማሌቅ ንጉሥ አጋግን ወጋው። 34የእግዚአብሔርን ቃል ያፈረሰ ያንም ዝንጉ ርኩስ መንፈስ ያዘው፤ ራሱንም መታው፤ እርሱ ሁሉን የሚያዝዝ ንጉሠ ነገሥት ስለሆነ እግዚአብሔር ዐመፅን ያደረገ ንጉሥን አያፍረውምና። 35የማይፈሩት የነገሥታቱንና የመኳንንቱን ሥልጣን ሁሉ የሚሽር እርሱ የፍጥረቱ ሁሉ ጌታ ነውና እርሱን የሚያዝዘው የለም። 36የዳዊት ወገን እየገነነ ይሄዳል፤ የሳኦል ወገን ግን እየተዋረደ ይሄዳል ብሎ እንደ ተናገረ ከሳኦልና ከልጁ መንግሥትን አጠፋ። 37ስላሳዘነውና በክፉ ሥራቸው ያሳዘኑትን ወንጀለኞችን ስለ አላጠፋ እግዚአብሔር ተበቅሎ የሳኦልን ወገን አጠፋ። የእግዚአብሔርን ጠላት የማይበቀል ሰው እርሱ የእግዚአብሔር ጠላት ነውና። 38መበቀል ሲቻለው፥ ሥልጣንም ሳለው ኀጢአተኛውን የማይበቀል፥ የእግዚአብሔር ሕግ የሌለውንም የማይበቀል ሰው እርሱ በእውነት የእግዚአብሔር ጠላት ነው።