1ረዓይታዊው ኮራ፤ እግዚአብሔርም፦ በአንዲት የወባ ትንኝ ከእግሩ ጀምሮ እስከ ራሱ ድረስ ሰውነቱ እንዲያብጥ አደረገው፤ በዚያችም ትንሽ የወባ ትንኝ ሞተ። 2ዳግመኛም ከኀይለኝነቱ ብዛት የተነሣ የብረት አልጋ ያሠራው ናምሩድ ኰራ፤ እርሱንም እግዚአብሔር አጠፋው። 3ዳግመኛም ናቡከደነጾር ኰራ፤ “ያለ እኔም ሌላ ንጉሥ የለም፤ በምድርም ላይ ፀሐይን የማወጣ እኔ ነኝ” አለ፤ ከትዕቢቱም ብዛት የተነሣ እንዲህ አለ። 4እግዚአብሔር ከሰው ለይቶ ሰባት ዓመት ወደ ምድረ በዳ ሰደደው፤ የፈጠረውም እግዚአብሔር እንደ ሆነ እስኪያውቅ ድረስ ዕድሉን ከምድረ በዳ አራዊትና ከሰማይ ወፎች ጋር አደረገ። 5ባወቀውም ጊዜ ዳግመኛ ወደ መንግሥቱ መለሰው፤ በፈጠረው በእግዚአብሔር ላይ ተደፋፍሮ የኰራ፥ መሬትም ያልሆነ ማን ነው? 6ሕጉንና ሥርዐቱንስ አፍርሶ መሬት ያልዋጠችው ማን ነው? 7“ጺሩጻይዳን አንተም በፈጣሪህ ላይ ትኰራ ዘንድ ትወድዳለህ፤ አንተንም ዳግመኛ ከትዕቢትህ የተነሣ እንደ እነርሱ ያጠፋህ ዘንድ፥ ወደ መቃብርም ያወርድህ ዘንድ አለህ። 8ዳግመኛም ጥርስ ማፋጨትና ልቅሶ ወዳለበት የጨለማ ፍጻሜ ወደ ሆነው ወደ ሲኦል፥ ከገቡም በኋላ ለዘለዓለም መውጫ ወደሌለበት ወደ ትልቁና ጥልቁ ጕድጓድ ያወርድህ ዘንድ አለህ። 9አንተስ እንደ አንተ እንደ ነበሩና የዚህን ዓለም ኑሮ እንደ ተዉ እንደ ትዕቢተኞች ነገሥታት ነገ የምትሞትና የምትፈርስ ነህ።” 10እኛስ እንዲህ እንላለን፥ “አንተ ሰው ነህ፤ እግዚአብሔርም አይደለህም፤ እግዚአብሔር ምድርንና ሰማይን የፈጠረ፥ አንተንም የፈጠረ ነውና፤ 11እርሱም ትዕቢተኞችን ያወርዳቸዋል፤ የተዋረዱትንም ያከብራቸዋል፤ እርሱም ለደከሙት ብርታትን ይሰጣቸዋል፤ ለኀያላኑም ድካምን ይሰጣል። 12እርሱ ሕያዋንን ይገድላል፤ እርሱም በመቃብር ተቀብረው መሬት የሆኑትን ሙታን ያስነሣቸዋል። 13ባሮችንም ከኀጢአት ባርነት ወደ ሕይወት ነጻ ያወጣቸዋል። 14“ንጉሥ ጺሩጻይዳን ሆይ! ጥቅም በሌላቸው በረከሱ ጣዖቶችህ ለምን ትመካለህ? 15እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ፈጠረ፤ ምድርንም መሠረተ፤ ታላቁንም ባሕር ፈጠረ፤ ፀሐይንና ጨረቃን ፈጠረ፤ ዘመኖችንና ዓመታትን አዘጋጀ። 16ሰውም ወደ እርሻው ይሰማራል፤ እስኪመሽም ድረስ ሲያርስ ይውላል፤ የሰማይ ከዋክብትም በቃሉ ጸንተው ይኖራሉ። 17ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ እግዚአብሔርም ሳያውቀው የሚደረግ ነገር የለም። 18እርሱም ያገለግሉት ዘንድ፥ የከበረ ስሙንም ያመሰግኑ ዘንድ የሰማይ መላእክትን አዘዘ፤ መላእክትም ሕይወትን ወደሚወርሱ ሰዎች ሁሉ ይላካሉ። 19መልአኩ ሩፋኤል ወደ ጦቢት ተላከ፤ ጦብያንም በራጉኤል ሀገር አዳነው። 20ኤሎፍላውያንንም እንዲያጠፋቸው ያሳውቀው ዘንድ መልአክ ወደ ጌዴዎን ተላከ፤ እስራኤልንም የኤርትራን ባሕር ባሻገራቸው ጊዜ መልአክ ወደ ነቢዩ ሙሴ ተላከ። 21እንዲህ ብሏልና፦ እግዚአብሔር ብቻውን መራቸው፥ ከእነርሱም ጋር ሌላ አምላክ አልነበረም። 22በምድር ላይ ወደአለ አዝመራም አወጣቸው። 23የሁዳዱንም እህል መገባቸው፤ ፈጽሞ ወዷቸዋልና፥ ከዐለት ማርን መገባቸው። 24“አንተንም በሕዝቡ ላይ አነገሠህ፤ ወገኖቹንም በሚገባ ፈጽመህ ትጠብቅ ዘንድ፥ የፈጠረህ የእግዚአብሔርንም ፈቃዱን ታደርግ ዘንድ በአራቱ መንግሥታት ላይ ሥልጣንን ሰጠህ። 25ከሁሉም ከፍ ከፍ አድርጎ አንግሦሃልና ፈጣሪህ እግዚአብሔርን ትወደው ዘንድ ፈጽሞ አነገሠህ። 26አንተም እንደ ወደደህ፥ በሕዝቡም ሁሉ ላይ እንዳመነህ ፈጣሪህ እግዚአብሔርን ፈጽመህ ትወድደው ዘንድ ይገባሃል፤ አንተም የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርግ፥ በምድር ሁሉ ዘመንህ ይበዛ ዘንድ፥ ከአንተም ጋር ይኖር ዘንድ፥ 27በጠላቶችህም ላይ ይቆምልህ ዘንድ፥ በዙፋንህም ሁሉ ያስቀምጥህ ዘንድ፥ ክንፉንም በራስህ ላይ ይጋርድ ዘንድ። 28ብታውቅስ እግዚአብሔር ሳኦልን የአባቱን አህዮች ሲጠብቅ ከእስራኤል ልጆች መርጦ በወገኖቹ በእስራኤል ላይ እንደ አነገሠው፥ ከነቢዩም ከሳሙኤል ጋር በዙፋን እንደ ተቀመጠ አንተን መረጠህ። 29ከወንድሞቹም ለይቶ ከፍ ያለ ዕድልን ሰጠው፤ እንዲህም አለው፦ ከዛሬ ጀምሮ ወገኖቹን ትጠብቅ ዘንድ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ አነገሠህ፤ 30ትገድልና ታድን ዘንድም እግዚአብሔር በላያቸው ሾሞሃልና በጎ የሚሠሩትን በበጎ፥ ክፉ የሚሠሩትንም በክፉ ጠብቃቸው። 31እየገረፍህና እያዳንህም ቢሆን ፈቃዱን ታደርግ ዘንድ እግዚአብሔር አንተን በሁሉ ላይ ሾሞሃልና በጎ የሚሠሩትን በጎ ክፈላቸው፤ ክፉ የሚሠሩትንም ክፉ ክፈላቸው። 32አንተ በሰማይ ያለ ሁሉን የሚገዛ የእግዚአብሔር ባሪያ ነህና፥ ባሰብኸው ሁሉ በፊቱ እየተገዛህ፥ በለመንኸውም ሁሉ ፈቃድህን ያደርግልህ ዘንድ አንተም በየጊዜውና በየሰዓቱ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርግ። 33“እርሱን የሚገዛው የለም፤ እርሱ ግን ሁሉን ይገዛል። 34እርሱን የሚሾመው የለም፤ እርሱ ግን ሁሉን ይሾማል። 35እርሱን የሚሽረው የለም፥ እርሱ ግን ሁሉን ይሽራል። 36እርሱን የሚነቅፈው የለም፤ እርሱ ግን ሁሉን ይነቅፋል። 37እርሱን የሚያተጋው የለም፤ እርሱ ግን ሁሉን ያተጋል፤ የሰማይና የምድር ሥልጣን የእርሱ ነውና ከእጁ የሚያመልጥ የለም፤ በእርሱ ዘንድ ሁሉ የተገለጠ ነው እንጂ ከዐይኑ የተሰወረ የለም። 38ሁሉንም ያያል፤ እርሱን ግን የሚያየው የለም፤ ወደ እርሱ የሚጸልየውን ጸሎቱን ይሰማዋል፤ ጸሎቱንም ይቀበለዋል፤ ሰውን በአምሳሉና በአርኣያው ፈጥሮታልና። 39ከማይጐድል መዝገቡም ሁሉን ይመግባል። ለዘለዓለም የሚኖር ንጉሥ ነውና።