1ያም ወንጀለኛ እንደ ሞቱ በአየ ጊዜ ዐመድ እስኪሆን ድረስ ሥጋቸውን በእሳት ያቃጥሉ ዘንድ፥ በነፋስም ይበትኗቸው ዘንድ አዘዘ፤ እሳቱ ግን ከሬሳቸው ወገን የራሳቸውን ጠጕር ያቃጥል ዘንድ አልተቻለውም፤ ከጕድጓዱም አወጧቸው። 2ዳግመኛም ከጧት ጀምረው እስከ ማታ ድረስ በላያቸው እሳትን አነደዱ፤ አልነካቸውምም፤ “አሁንም ኑ፤ ሬሳቸውን ወደ ባሕር እንጣለው” አሉ። 3ንጉሡም እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ወደ ባሕርም ጣሏቸው፤ ምንም ከባድ ከባድ ብረቶችንና ታላላቅ ድንጋዮችን፥ አህያ በመዘውር የሚፈጭበትንም ወፍጮ ጨምረው ወደ ባሕር ቢጥሏቸው ባሕሩ ያሰጠማቸው ማስጠም የለም፤ የእግዚአብሔር መንፈስ አድሮባቸዋልና በባሕሩ ላይ ተንሳፈፉ እንጂ በጥልቁ ባሕር አልሰጠሙም፤ በተተነኰለባቸውም ተንኰል ሁሉ እነርሱን ማጥፋት ተሳነው። 4“ከሕይወታቸውም ይህ ሞታቸው አድክሞኛልና ይበሏቸው ዘንድ ሬሳቸውን ለአውሬዎች ልጣል እንጂ ምን አደርጋለሁ?” አለ። 5እንዲሁም አደረጉ፤ አውሬዎችና አሞሮችም ሬሳቸውን አልነኩትም፤ አሞሮችና ወፎች በፀሐይ ከመቃጠል በክንፋቸው ጋርደዋቸው የአምስቱ ሰማዕታት ሬሳቸው ዐሥራ አራት ቀን ተቀመጠ። 6በአዩአቸውም ጊዜ ሰውነታቸው እንደ ፀሐይ ጨረር አበራ፤ ብርሃንም ድንኳኑን እንዲከብ፥ መላእክት ሬሳቸውን ከበቡት። 7ምክርን መከረ፤ የሚያደርገውንም አጣ፤ ከዚህም በኋላ ምድርን ቈፍሮ የአምስቱን ሰማዕታት ሬሳቸውን ቀበረ። 8ለዚያም ዝንጉ ንጉሥ ሌሊት በአልጋ ተኝቶ ሳለ አምስቱ ሰማዕታት ተቈጥተው ሰይፋቸውን ይዘው ሌሊት በፊቱ ቁመው ታዩት። 9ሌሊት በወንጀል ወደ ቤቱ የገቡ መስሎታልና ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ ፈርቶ ከቤት ማዕዘን ወደ ማዕዘን ይሸሽ ዘንድ ወደደ፤ የወነጀሉትም መሰለው፤ የሚገድሉትም መስሎታልና ፈርቶ ጕልበቱ ተንቀጠቀጠ። 10ስለዚህም “ጌቶች፥ ምን ትፈልጋላችሁ? እኔስ ምን ላድርግላችሁ?” አለ። 11“በእሳት አቃጥለህ የገደልኸንና እኛን በባሕር ላይ ይጥሉን ዘንድ ያዘዝህ አይደለምን፤ ስለአመንበት እግዚአብሔር ሰውነታችንን ጠብቆአልና እኛን ማጥፋት ተሳነህ፤ በእርሱ ያመነ ሰው አይጠፋምና ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው፤ ያመንበት እኛም በመከራው አላፈርንም” ብለው መለሱለት። 12“እንደዚህ ያለ ቅጣት እንዲያገኘኝ አላወቅሁምና ክፉ ነገርን ስላደረግሁባችሁ ፋንታ ምን ዋጋ ልስጣችሁ? 13አሁንም ሰውነቴን በሞት እንዳትወስዱ፥ በሕይወትም ሳለሁ ወደ ሲኦል እንዳታወርዱኝ የምሰጣችሁን ዋጋ ለዩልኝ። 14እኔ በድያችኋለሁና የአባታችሁ የእግዚአብሔር ሕግ ርኅራኄ ስለሆነ ኀጢአቴን ይቅር በሉኝ” አላቸው። 15እነዚያም ቡሩካን ሰማዕታት እንዲህ ብለው መለሱለት፥ “ክፉ ነገርን ስላደረግህብን ፋንታ እኛ ክፉ ነገርን አንከፍልህም፤ ፍዳን የሚከፍል እግዚአብሔር ነውና ፍዳንስ የሚከፍልህ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር አለ። 16ነገር ግን ስለዕውቀትህ ማነስና ስለ ልቡናህ ድንቍርና እኛ ሕያዋን እንደ ሆንን ተገልጠን ታየንህ፤ እኛንስ የገደልኸን መስሎህ ሕይወትን አዘጋጀህልን። 17አንተና የጣዖቶችህ ካህናት ግን ለዘለዓለሙ መውጫ ወደሌለባት ወደ ገሃነም ትወርዳላችሁ። 18እናንተ ምራቅ ስትሆኑ ለፈጠራችሁ ለእግዚአብሔር መስገድን ትታችሁ ለምታመልኩአቸውና ለምትሰግዱላቸው ጣዖቶችና ለአንተ ወዮላችሁ፤ ከወዴትም እንደ አመጣችሁ አታውቁም፤ ዛሬ ታይታችሁ ነገ የምትጠፉ ጢስ አይደላችሁምን?” 19ንጉሡም፥ “የወደዳችሁትን ሁሉ አደርግላችሁ ዘንድ ምን ታዝዙኛላችሁ?” ብሎ መለሰላቸው። 20“ወደ ገሃነመ እሳት እንዳትገባ ስለ ራስህ ነው እንጂ የምናስተምርህ ስለ ራሳችን አይደለም። 21ጣዖቶቻችሁ ነፍስና ልቡና፥ ዕውቀትም የሌላቸው፥ የሰው እጅ የሠራቸው ወርቅና ብር፥ ድንጋይና እንጨት ናቸውና። 22እነርሱ ግን አይገድሉም፤ አያድኑምም፤ መልካም አያደርጉም፤ ክፉም አያደርጉም፤ አያዋርዱም፤ አያከብሩምም፤ አያደኸዩም፤ ባለጸጋም አያደርጉም፤ አይነቅሉም፤ አይተክሉምም። 23“ነገር ግን ከሰዎች ይልቁንም እንደ እናንተ ዕውራነ ልብ ከሆኑ አንዱስ እንኳ እንዳይድን በሚወድዱ አጋንንት መንፈስ እናንተን ያስታሉ። እናንተ የሠራችኋቸው ስትሆኑ እነርሱ የፈጠሯችሁ ይመስላችኋልና። 24የአጋንንትና የሰይጣናት መናፍስት አድረውባቸዋልና በባሕረ ገሃነም ውስጥ ያሰጥሟችሁ ዘንድ እንደ ወደዳችሁ ይመልሱላችኋል። 25አንተ ግን ይህን ስሕተትህን ትተህ አምላካችን እግዚአብሔርን አምልከው፤ ይህም ነፍሳችንን እንጠቅማት ዘንድ ስለ ሞታችን ፋንታ ዋጋችን ይሁን” አሉት። 26እርሱ ግን ደንግጦ ፈጽሞ ያደንቅ ነበር፤ አምስቱም ሁሉ ሰይፋቸውን መዝዘው ታይተውታልና ፈራ፤ ስለዚህም ሰገደላቸው። 27“እንግዲህስ ትቢያ የሆኑ ሙታን ከሞቱ በኋላ በእውነት እንዲነሡ ዐወቅሁ፤ እኔስ ልሞት ጥቂት ብቻ ቀርቶኝ ነበር” አለ። 28ከዚህ በኋላ ከዚያ ንጉሥ ፊት ተሰወሩ፤ ከዚያችም ቀን ወዲያ ፈጽሞ ትዕቢተኛና ኵራተኛ የሚሆን ያ ጺሩጻይዳን ሬሳቸውን ማቃጠልን ተወ። 29ብዙ ዘመን አስተውታልና በልቡናው ስሕተት በጣዖቶቹ ደስ ይለው ነበር፤ የፈጠራቸውንም መከተል እስኪተዉ ድረስ እንደ እርሱ ያሉ ብዙ ሰዎችን አሳተ እንጂ እርሱ ብቻ የሳተ አይደለም። 30ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውንም ለአጋንንት ይሠዉ ነበር፤ እግዚአብሔር የማይወድደውን ሁከትንና መዳራትን ያደርግ ዘንድ አባታቸው ሰይጣን ያስተማራቸው የልቡናቸውን ፈቃድ ዝሙትንና መዳራትን ይሠሩ ነበር። 31እናታቸውን ያገቡ፥ እኅቶቻቸውንና አክስቶቻቸውንም ያረክሱ ነበር፤ ይህን የረከሰ ሥራና የሚመስለውንም ሁሉ ይሠሩ ነበር፤ ሰውነታቸውንም ያረክሱ ነበር፤ ሰይጣን የእነዚያን ጠማሞች ሰዎች ልቡናቸውን አጥንቶታልና አንመለስም አሉ። 32ፈጣሪውን የማያውቅ ያ ጺሩጻይዳን ግን ኵሩና ትዕቢተኛ ነበር፤ በጣዖቶቹም ይመካ ነበር። 33“እግዚአብሔር ለማያውቁት ሰዎች መንግሥትን እንዴት ይሰጣል? ፈጽመው ወደ እርሱ ይመለሱ እንደ ሆነ ስለሚፈትናቸው ነው” አለ። 34እነርሱ ግን ፈጽመው ቢመለሱ ይወድዳቸው ነበር፤ መንግሥታቸውንም ይጠብቅ ነበር፤ እንቢ ቢሉ ግን ለዘለዓለሙ በገሃነም እንቅጥቅጥ ይቀጣቸዋል። 35ንጉሡ ግን እንደ መንግሥቱ ገናናነት እግዚአብሔር አምላክን ሊፈራው ይገባው ነበር፤ ፈራጅም እንደ ግዛቱ ገናንነት ለፈጣሪው በመልካም ሊገዛ ይገባ ነበር። 36ታላላቆች ሽማግሌዎች፥ አለቆችና ሹሞችም እንደ ክብራቸው ገናንነት ለፈጣሪያቸው ሊታዘዙ ይገባ ነበር። 37ፍጥረቱን ሁሉ የፈጠረ የሰማይና የምድር ጌታ እርሱ ነውና፤ የሚያደኸይ፥ ባለጸጋም የሚያደርግ፥ የሚያዋርድ፥ የሚያከብርም እርሱ ነው፤ በላይ በሰማይ፥ በታችም በምድር ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለምና።