1ከሰማይም እንዲህ የሚል ቃል መጣ፤ “የልዑል እግዚአብሔር ባሮች አብያ፥ ሲላ፥ ፈንቶስ፥ ሞተው የተነሡ እነዚህን በፊታችሁ እንዳያችሁ ከሞታችሁ በኋላ እንደዚሁ ትነሡ ዘንድ አላችሁ፤ ፊታችሁም በመንግሥተ ሰማይ ይበራል። 2ከእነዚያ ሰዎችም ጋራ ሂዱ፤ በዚያም ሰማዕትነትን ተቀበሉ።” 3ያንጊዜም ጸለዩና አመሰገኑ፤ ለእግዚአብሔርም ሰገዱ፤ ሞትና የንጉሡ ቅጣትም አላስፈራቸውም። 4ወደ እነዚያ ብላቴኖችም ሄዱ፤ ክፋት እንደሌለው በግ ሆኑ እንጂ አላስፈሩአቸውም፤ ወደ እነርሱም በደረሱ ጊዜ ይዘው መትዋቸው፤ አስረውም ገረፏቸው፤ ወደ ንጉሡም አድርሰው በፊቱ አቆሟቸው። 5ንጉሡም፥ “እናንተ እንቢተኞች ለአማልክቶች እንዴት አትሠዉም? እንዴትስ አትሰግዱም?” ብሎ መለሰላቸው። 6እነዚያ ቅዱሳንና ቡሩካን፥ የተመረጡና ደስ ያላቸው፥ ዋጋው ድንቅ እንደ ሆነ ዕንቍም የሚያበሩ ወንድማማቾች አብያ፥ ሲላና ፈንቶስም ባንድ ቃል መለሱለት። 7ቸነፈር የሆነ ያን ንጉሥም እንዲህ አሉት፥ “እኛስ ዕውቀትና ልቡና ለሌላቸው ለረከሱ ጣዖቶች አንሠዋም፤ አንሰግድምም። 8ዳግመኛም፦ የሰው እጅ ለሠራቸው ወርቅና ብር፥ ድንጋይና እንጨት ለሆኑ፥ ነፍስና ልቡና፥ ዕውቀትም ለሌላቸው፥ መልካም ለሚያደርግላቸው መልካምን ለማያደርጉ፥ ክፉ ለሚያደርግባቸውም ክፉን ለማያደርጉ ጣዖታት አንሰግድም።” 9ንጉሡም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፥ “ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? እነርሱ የሚሰድባቸውንና የሚበድላቸውን ያውቃሉና የከበሩ አማልክቶችን ለምን ትሰድባላችሁ”። 10“እነርሱም በእኛ ዘንድ እንደ ኢምንት ናቸውና እኛ እንሰድባቸዋለን፤ አናከብራቸውምም” ብለው መለሱለት። 11ንጉሡም፥ “እንደ ሥራችሁ ክፋት መጠን እቀጣችኋለሁ፤ በጽኑ መከራና በግርፋት፥ በእሳትም የመልካችሁን ደም ግባት አጠፋለሁ። 12አሁንም ለአማልክቶች ትሠዉ እንደ ሆነ ወይም አትሠዉ እንደ ሆነ ንገሩኝ፤ ይህ ካልሆነ ግርፋትንና ሰይፍን በእናንተ ላይ አነሣለሁ” ብሎ መለሰላቸው። 13እነርሱም፥ “እኛስ ለረከሱ ጣዖታት አንሠዋም፤ አንሰግድምም” ብለው መለሱለት፤ ንጉሡም በወፍራም በትር ይመትዋቸው ዘንድ፥ ዳግመኛም በጅራፍ ይገርፏቸው ዘንድ፥ ከእዚያም በኋላ የውስጥ አካላቸው እስኪታይ ድረስ ይሰነጥቋቸው ዘንድ አዘዘ። 14ከዚህም በኋላ ይቀጣቸውና ይገድላቸው ዘንድ እስኪመክር ድረስ አስረው በግዞት ቤት አዋሏቸው። 15ወስደውም ያለ ርኅራኄ በእስር ቤት ጽኑዕ እስራት አሰሩአቸው፤ እነርሱም በእስር ቤት ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ተቀመጡ። 16ከሦስት ቀንም በኋላ ንጉሡ፥ መኳንንቱና አማካሪዎቹ፥ ሹሞቹና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሰበሰቡ ዐዋጅ ነጋሪ ይዞር ዘንድ አዘዘ፤ 17ንጉሡ ጺሩጻይዳንም በአደባባይ በተቀመጠ ጊዜ እነዚያን የከበሩ አብያን፥ ሲላንና ፈንቶስን ያመጧቸው ዘንድ አዘዘ፤ የታሰሩና የቈሰሉ ሆነውም በፊቱ ቆሙ። 18ንጉሡም፥ “ይህን ሦስቱን ቀን ስትቀመጡ በውኑ የተመለሳችሁት መመለስ አለን? ወይስ እናንተ በቀደመው ክፋታችሁ አላችሁ?” አላቸው። 19የከበሩ የእግዚአብሔር ጭፍራዎችም፥ “እኛስ የጨከን ነን፤ ኀጢአትና ክፋትን የተመላ፥ አንተ የምታመልከውን ጣዖትን እናመልክ ዘንድ እሺ አንልም” ብለው መለሱለት። 20ያም ወንጀለኛ ተቈጥቶ ይሰቅሉአቸውና ቍስላቸውንም ያድሱት ዘንድ አዘዘ፤ ደማቸውም በምድር ላይ ፈሰሰ። 21ዳግመኛም በጭራሮ መብራት ያቃጥሏቸው ዘንድ፥ ሥጋቸውም ያር ዘንድ አዘዘ፤ እንዲሁም አደረጉ፤ እነዚያም የከበሩ ሰዎች “አንተ ዝንጉዕ፥ ተናገር፤ ቅጣታችንን በምታበዛብን መጠን ዋጋችን ይበዛል” አሉት። 22ዳግመኛም ሥጋቸውን ከአጥንታቸው ጋራ ፈጽመው ይበሏቸው ዘንድ ምግባቸውን ሳይበሉ ክፉ አውሬዎችን ነብርንና ድብን፥ አንበሳንም አምጥተው ይሰዱባቸው ዘንድ አዘዘ። 23አውሬዎችን የሚጠብቁ ሰዎችንም አውሬዎቹን ይሰዱባቸው ዘንድ አዘዘ፤ እነርሱም እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ የከበሩ እነዚያን ቅዱሳን ሰማዕታትንም የፊጥኝ አሰሩአቸው፤ ዳግመኛም ተተንኵለው፥ ካስማ መትተው አሰሩዋቸው። 24እነዚያም አውሬዎች እያገሡ በላያቸው ተወረወሩ፤ ወደ ሰማዕታቱም በደረሱ ጊዜ ሰገዱላቸው፤ እጅም ነሡአቸው። 25እያገሡም ወደ ጠባቂዎቻቸው ተመለሱ፤ ጠባቂዎቻቸውንም አስፈሯቸው፤ ወደ ንጉሡም ፊት እስኪያደርሷቸው ድረስ አባረሯቸው። 26በዚያም ከወንጀለኞች ሠራዊት ሰባ አምስት ሰዎችን ገደሉ። 27ንጉሡ ዙፋኑን ትቶ እስኪሸሽ ድረስ በፍርሀት አንዱ ባንዱ ላይ ተጨናንቀው ብዙ ሰዎች ተሰበሩ፤ አውሬዎቹንም በጭንቅ ይዘው ወደ ማደሪያቸው ወሰዱዋቸው። 28የአብያና የሲላ የፈንቶስም ሁለቱ ወንድሞቻቸው መጥተው፥ ካሰሩአቸው እስራት ፈትተው “እነዚህ ወንጀለኞችና ተጠራጣሪዎች እንዳያገኙን ኑ እንሽሽ” አሏቸው። 29እነዚያም ሰማዕታት ወንድሞቻቸውን፥ “ለሰማዕትነት ከቆምን በኋላ እንሸሽ ዘንድ አግባብ አይደለም፤ እናንተ ፈርታችሁ እንደ ሆነ ሸሽታችሁ ሂዱ” ብለው መለሱላቸው። 30እነዚያም ታናናሽ ወንድሞቻቸው፥ “እኛም በንጉሡ ፊት ከእናንተ ጋር እንቆማለን፤ ብትሞቱም እኛ አብረን እንሞታለን” አሉ። 31ከዚህም በኋላ ንጉሡ በመንግሥቱ አዳራሽ ሰገነት ላይ ሆኖ እነዚህ የተባረኩ ሰዎች እንደ ተፈቱና አምስቱ ወንድማማቾች ሁሉ በአንድነት እንደ ቆሙ አየ፤ ጭፍራዎችን የሚሠራሩና፥ የሚቀጡ እነዚያ አለቆችም ወንድሞቻቸው እንደ ሆኑ ጠይቀው ለንጉሡ ነገሩት፤ ንጉሡም ተቈጥቶ እንደ ምድረ በዳ እሪያ ጮኸ። 32ንጉሡም አምስቱን ወንድማማቾች ሁሉ ይቀጣቸው ዘንድ እስኪመክር ድረስ ይዘው በእስር ቤት እንዲጨምሩአቸው አዘዘ፤ በተፈለፈለም ግንድ ያለ ርኅራኄ ጽኑ እስራትን አስረው በእስር ቤት አኖሯቸው። 33ንጉሡ ጺሩጻይዳንም፥ “እነዚህ የሳቱ ጐልማሶች አደከሙኝ፤ የእነዚህ ሰዎች ልቡናቸው ምን ይጸና! የሥራቸውም ክፋት እንደ ኀይላቸው ጽናት ነው፤ ይመለሳሉ ብል ልቡናቸውን ያከፋሉ። 34እኔም እንደ ሥራቸው ክፋት መጠን እከፍላቸዋለሁ፤ አርሮም አመድ ይሆን ዘንድ ሥጋቸውን በእሳት አቃጥላለሁ፤ ነፋስም ይወስዳቸው ዘንድ በዚያ የሥጋቸውን ዐመድ እንደ ትቢያ በተራራ ላይ እበትናለሁ” አለ። 35ይኽንም ከተናገረ በኋላ ሦስት ቀን ቈይቶ እነዚያን ቅዱሳን ያመጧቸው ዘንድ አዘዘ፤ እነዚያም ቅዱሳን በቀረቡ ጊዜ በታላቁ ጕድጓድ ምድጃ ውስጥ እሳት ያነዱ ዘንድ እሳቱን የሚያናድድና ድስት የሚያፈሉበት የተንኰል ሥራን ስብንና እንዶድን፥ የባሕር አረፋና ሙጫን፥ ድኝንም በውስጡ ይጨምሩ ዘንድ አዘዘ። 36በጕድጓዱም ያለው እሳት በነደደ ጊዜ መልእክተኞቹ “ያዘዝኸንን አደረግን፤ የሚጨመረውን ሰው ስደድ” ሲሉ ወደ ንጉሡ ሄዱ። 37ተቀብለውም በእሳቱ ጕድጓድ ይጥሏቸው ዘንድ አዘዘ፤ ብላቴኖቹም ንጉሡ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ እነዚያም ቅዱሳን ወደ እሳቱ በገቡ ጊዜ፥ ነፍሳቸውን ለእግዚአብሔር ሰጡ። 38መላእክትም የጣሉአቸው ሰዎች እያዩ ተቀበሉአቸው፤ ነፍሳቸውንም አብርሃምና ይስሐቅ ያዕቆብም ወደ አሉበት፥ ደስታ ወደሚገኝበት ወደ ገነት ወሰዷቸው።