1ከነገደ ብንያም ስሙ መቃቢስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ። 2መልከ መልካሞችና እጅግ ብርቱዎች የሆኑ ሦስት ልጆች ነበሩት፥ በሰው ሁሉ ዘንድ በዚያች የጺሩጻይዳን ግዛት በምትሆን በከለዳውያን ምድር በምድያምና በሜዶን ሀገር መወደድ ነበራቸው። 3በአገኙአቸውም ጊዜ እንዲህ አሏቸው፥ “ንጉሡ እንዳዘዘ ለጺሩጻይዳን አማልክት አትሰግዱምን? መሥዋዕትስ አትሠዉምን? 4እንቢ ብትሉ ግን ይዘን ወደ ንጉሡ እንወስዳችኋለን፤ ንጉሡም እንዳዘዘ ገንዘባችሁን ሁሉ እናጠፋለን።” 5እነዚያ መልከ መልካሞች ጐልማሶችም፥ “እኛስ የምንሰግድለት ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርን፥ በውስጧም ያለውን፥ ፀሐይንና ጨረቃን፥ ከዋክብትንና ደመናትን የፈጠረ የአባቶቻችን አምላክ አለ፤ እኛ የምናመልከው፥ የምናምንበትም እውነተኛ አምላክ እርሱ ነው” ብለው መለሱላቸው። 6እነዚያም የንጉሡ ብላቴኖች አራት መሳፍንት ነበሩ፤ የጦር መሣሪያቸውን የሚሸከሙ አሽከሮቻቸውም ሃምሳ፥ ሃምሳ ነበሩ። 7እነዚህንም ቅዱሳን ይይዟቸው ዘንድ በወደዱ ጊዜ ከእጃቸው አመለጡ፤ የነካቸውም የለም፤ እነዚያ ጐልማሶች በኀይል ፈጽሞ አርበኞች ናቸውና ጋሻ ጦራቸውን ይዘው ሄዱ። 8ከእነርሱም ድብን አንቆ የሚገድል ነበር፤ ወዲያውኑም እንደ ዶሮ ያንቀው ነበር። 9ከእነርሱም በአንዲት ድንጋይ ወይም በአንድ ጊዜ በበትር መትቶ አንበሳ የሚገድል ነበር። 10ከእነርሱም በሰልፍ ጊዜ በአንድ ሰይፍ በአንድ ጊዜ መትቶ ሰው የሚገድል ነበር፤ እንዲሁም ስማቸውና አደናቸው በሞዓብና በከለዳውያን ምድር ሁሉ የተጠራ ነበር። 11በኀይልም አርበኞች ነበሩ፤ ደም ግባትም፥ የነገርም መወደድ ነበራቸው። 12ዳግመኛም የመልካቸው ደም ግባት ድንቅ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን ስላመለኩት፥ ሞትንም ስላልፈሩት ከሁሉ የምትበልጥ የልቡናቸው ደም ግባት ናት። 13ጭፍራዎችንም ባስፈሩአቸው ጊዜ ይይዛቸው ዘንድ የቻለ የለም፤ ብርቱዎች የሆኑ እነርሱ ግን ከፍ ወደ አለ ተራራ ወጥተው አመለጡ። 14እነዚያ ጭፍሮችም ወደ ከተማ ተመልሰው ያንባውን በር ዘጉ፤ እነዚያን አርበኞች መቃብያንን ካላመጣችኋቸው ከተማችሁን በእሳት እናቃጥላታለን፤ ወደ ንጉሡም ልከን ሀገራችሁን እናጠፋለን ብለው ሕዝቡን አስፈራሯቸው። 15የዚያን ጊዜም የሀገሩ ሰዎች ድሆችና ባለጸጎች፥ ወንዶችና ሴቶች፥ አባቱና እናቱ የሞቱበት ልጅና ባልቴቶችም፥ ሁሉም ወጥተው በአንድነት ጮሁ፤ ዐይኖቻቸውንም ወደ ተራራ አቀኑ፤ “እኛንና ሀገራችንን አታጥፉ” ብለው ወደ እነርሱ ጮሁ። 16የዚያን ጊዜም በአንድነት አለቀሱ፤ ከእግዚአብሔርም የተነሣ ፈሩ። 17ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ መልሰው፥ እጃቸውንም ዘርግተው በአንድነት ወደ እግዚአብሔር ለመኑ፤ እንዲህም አሉ፥ “አቤቱ ትእዛዝህንና ሕግህን ያፈረሱ እነዚህን ሰዎች እንቢ እንበላቸውን? 18እኛ ግን በወርቅና በብር፥ የሰው እጅም በሠራው በደንጊያና በእንጨት ይታመናል እንጂ ሕግህን የማያምን የዚያን ወንጀለኛ ቃል እንሰማ ዘንድ አንወድም። 19የምታድንና የምትገድል አንተ ፈጣሪው ሳለህም ራሱን እነርሱ እንደ ፈጠሩት ያደርጋል፤ እርሱስ የሰውን ደም የሚያፈስ፥ የሰውንም ሥጋ የሚበላ ነው። 20እኛ ግን የዚያን የወንጀለኛ ፊት እናይ ዘንድ፥ ቃሉንም እንሰማ ዘንድ አንወድም። 21ነገር ግን አንተ ካዘዝኸን ወደ እርሱ እንሄዳለን፤ በአንተ ስላመንን ሰውነታችንን ለሞት አሳልፈን እንሰጣለን፤ ለአማልክቶች መሥዋዕት ሠዉ ባለ ጊዜም የዚያን የወንጀለኛ ቃል አንሰማም። 22ፈቃድህን ያደረጉ፥ በሕግህም ጸንተው የኖሩ የአባቶቻችን አምላክ አቤቱ፥ ኵላሊትንና ልቡናን የምትመረምር የአብርሃም፥ የይስሐቅ፥ የያዕቆብም አምላክ ሆይ! እኛ ግን በፍጹም ልባችን አንተን አመንን። 23የሰውን ልቡና መርምረህ ኃጥኡንና ጻድቁን ትረዳዋለህ፤ የሚሰወርህም የለም፤ የተሸሸገውም ባንተ ዘንድ የተገለጠ ነው። 24እኛ ግን ከአንተ በቀር ሌላ አምላክ የለንም። 25ነገር ግን ስለ ቅዱስ ስምህ ሰውነታችንን ለሞት እንሰጥ ዘንድ በዚህ በምንገዛልህ ሥራ ኀይል፥ ብርታትና መጠጊያም ሁነን። 26እስራኤልም ወደ ግብፅ ሀገር በገቡ ጊዜ የያዕቆብን ጸሎት ሰማህ፤ አሁንም ቅዱስ አምላክ ሆይ እንለምንሃለን።” 27መልካቸው ፈጽሞ ያማረ፥ ሁለቱም ሰዎች በፊታቸው ቆመው በታዩአቸው ጊዜ እንደ መብረቅ የሚያስፈሩ የእሳት ሰይፎች ወርደው ያንጊዜ አንገታቸውን ቈርጠው ገደሏቸው፤ ያንጊዜም እንደ ቀደመው ሕያዋን ሁነው ተነሡ። 28የመልካቸው ደም ግባት ፈጽሞ ያማረ ሆነ፤ ከፀሐይም ይልቅ አበሩ፤ ከቀደመውም ይልቅ ያማሩ ሆኑ።