1ስሙ ጺሩጻይዳን የሚባል፥ ክፋትንም የሚወዳት አንድ ሰው ነበር፤ በፈረሶቹ ብዛትና ከሥልጣኑ በታች ባሉ በጭፍራዎቹ ጽናት ይመካ ነበር። 2የሚያመልካቸውና የሚሰግድላቸው፥ በመዓልትና በሌሊት መሥዋዕት የሚሠዋላቸው ብዙ ጣዖታት ነበሩት። 3እርሱ ግን በልቡናው ድንቍርና እነርሱ ኀይልንና ብርታትን የሚሰጡት ይመስለው ነበር። 4በልቡም በግዛቱ ሁሉ እነርሱ ሥልጣንን የሚሰጡት ይመስለው ነበር። 5ዳግመኛም በሰልፍ ጊዜ እነርሱ ሥልጣንንና የተመኘውንም ሁሉ የሚሰጡት ይመስለው ነበር። 6እርሱም ቀንና ሌሊት ይሠዋላቸው ነበር። 7ጣዖታቱን የሚያገለግሉ ካህናትን ሾመ። 8ከዚያች ከረከሰች መሥዋዕት እነርሱ እየበሉ ቀንና ሌሊት ጣዖቶቹ የሚበሉ አስመስለው ይነግሩት ነበር። 9ዳግመኛ መሥዋዕት ሠውተው ይበሉ ዘንድ ሌሎች ሰዎችን እንደ እነርሱ ያተጉ ነበረ። ዳግመኛም እነርሱ መሥዋዕት ሠውተው እንደ እነርሱ መሥዋዕት ይሠዉ ዘንድ ሌሎች ሰዎችን ያተጉ ነበር። 10እርሱ ግን ጥቅም በሌለው ጣዖቱ ይታመን ነበር። 11በልቡ ድንቍርናና በዕውቀቱ ማነስ እነርሱ የፈጠሩት፥ እነርሱም የሚመግቡትና የሚያነግሡት ይመስለው ነበር፤ አማልክት ሳይሆኑ አማልክት ካላቸው ከእርሱ ጋራ ተፈርዶባቸው ለዘለዓለም ወደ ገሃነመ እሳት ይሄዱ ዘንድ ካለ መኖር ወደ መኖር አምጥቶ የፈጠረውን ፈጣሪውን እርሱ ከወገኖቹ ጋር እንዳያውቅ ሰይጣን ልቡናውን አደንቁሮታልና የፈጠሩት ይመስለው ነበር። 12መቼም መች ሕያዋን አይደሉምና ሙታን ይሏቸው ዘንድ ይገባል። 13የሚያስታቸው የሰይጣን መንፈስ በዚያ በጣዖቱ ምስል ያድራልና፥ የልቡናቸውንም ፈቃድ ይነግራቸዋልና፥ እንደ ወደዱም ይገለጥላቸዋልና ባመኑባቸው፥ ልቡናቸውም እንደ ዐመድ የሆነ የአዳም ልጆች በሚታመኑባቸው በጣዖቶቹ ይፈረድባቸዋል። 14ያሰቡትንም እንደ ፈጸመላቸው በአዩ ጊዜ ያደንቃሉ፤ እነርሱም ከባሕርያቸው የተወለዱ ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን እስኪሠዉ፥ የወንዶች ልጆቻቸውንና የሴቶች ልጆቻቸውን ንጹሕ ደም እስኪያፈስሱ ድረስ ፈቃዱን ያደርጋሉ። 15እስከ ዘለዓለም ድረስ መውጫ ወደሌለባት፥ እርሱ መከራ ወደሚቀበልባት እንደ እርሱ ወደ ገሃነም ያወርዳቸው ዘንድ ሰይጣን ክፉ ፈቃዳቸውን ለመፈጸም መሥዋዕቱን አጣጥሞላቸዋልና አላሳዘኗቸውም። 16ያ ጺሩጻይዳን ግን ትዕቢተኛ ነበር፤ በወንዶች አምሳል የተሠሩ ሃምሳ፥ በሴቶች አምሳል የተሠሩም ሃያ ጣዖቶች ነበሩት። 17ጥቅም በሌላቸው በእነዚያ በጣዖታቱም ይመካ ነበር፤ እጅግም ያከብራቸው ነበር፤ ጧትና ማታም ይሠዋላቸው ነበር። 18ሰዎችንም ለጣዖቱ መሥዋዕት ይሠዉ ዘንድ ያዛቸው ነበር፤ እርሱም ከዚያች የረከሰች መሥዋዕት ይበላ ነበር፤ ሌሎችንም ከመሥዋዕቱ ይበሉ ዘንድ ያዝዛቸው ነበር፤ ይልቁንም ለክፋት ይተናኰል ነበር። 19የብረትና የናስ፥ የእርሳስም ለሆኑ፥ ተመትተውም ለተሠሩ ጣዖታቱ አምስት ቤት ሠራላቸው። 20በወርቅና በብርም አስጌጣቸው፤ በቤቱም ዙሪያ መጋረጃ አስጋረደላቸው፤ ድንኳንም አስተከለላቸው። 21በዚያም ጠባቂዎችን ሾመላቸው፤ የሰቡ ዐሥር በሬዎችን፥ ዐሥር መሲናዎች ላሞችን፥ የሰቡ ዐሥር የበግ ሙክቶችን፥ የመሰኑ ዐሥር ፍየሎችንም ክንፍ ከአላቸው ከወፎች ጋራ ለጣዖታቱ ዘወትር አርባ ይሠዋላቸው ነበር። 22ለእርሱ ግን ጣዖታቱ የሚበሉ ይመስለው ነበር፤ ሃምሳ ፊቀን ወይን፥ በዘይት የታሸ ሃምሳ ወጪት ስንዴንም ያቀርብላቸው ነበር። 23ካህናቱንም “ወስዳችሁ ስጧቸው፤ ፈጣሪዎች ያረድሁላቸውን ሥጋ ይብሉ፤ ያቀረብሁላቸውንም ወይን ይጠጡ፤ ባይበቃቸውም እኔ እጨምርላቸዋለሁ” አላቸው። 24ከዚያች ከረከሰች መሥዋዕትም ይበሉና ይጠጡ ዘንድ ሁሉን ያስገድድ ነበር። 25እርሱ ግን በክፉ ተንኰሉ የማይሠዋም፥ የማይሰግድም እንዳለ ለይተው ዐውቀው ያመጡት ዘንድ፥ በፊቱም በእሳትና በሰይፍ ይቀጡት ዘንድ ገንዘቡንም ይበረብሩት ዘንድ፥ ቤቱንም በእሳት ያቃጥሉት ዘንድ፥ ያለውንም ገንዘቡን ሁሉ ይወስዱበት ዘንድ በግዛቱ ሁሉ የሚሰልሉ ጭፍራዎቹን ላከ። 26ለአማልክቶችም መሠዋትንና ማምለክን እንቢ ካለ ለእርሱ እኔ መከራንና ቅጣትን አሳየዋለሁ። እነርሱ ደጋጎችና ታላላቆች ናቸውና፥ በቸርነታቸውም እኛን ፈጥረዋልና፤ 27ሰማይንና ምድርን፥ ታላቅ ባሕርንም፥ ፀሐይንና ጨረቃን፥ ከዋክብትንም፥ ነፋሳትንና ዝናማትንም፥ ለእኛም ምግብና ጥጋብ ሊሆነን የሚንቀሳቀሰውን ሁሉ ፈጥረዋልና። 28የማያመልኳቸው ግን በፍጹም መከራ ይቀጣሉ፤ አይራሩላቸውምም።