1“እንዲህ ካልሆነ ግን የቀደሙ አባቶች ከአዳም ጀምሮ ከአቤልና ከሴት፥ ከኖኅና ከሴም፥ ከአብርሃምና ከይስሐቅ፥ ከያዕቆብና ከዮሴፍ፥ ከሙሴና ከአሮን ጀምሮ ከአባቶቻቸው መቃብር ውጭ ይቀበሩ ዘንድ ያልወደዱ ለምንድን ነው? 2በትንሣኤ ጊዜ ከዘመዶቻቸው ጋር በአንድነት እንዲነሡ አይደለምን? አጥንታቸውስ ጣዖት ከሚያመልኩ ከክፉዎች፥ ከጣዖት አምላኪዎችና ከአረማውያንም አጥንቶች ጋራ እንዳይቈጠሩ አይደለምን? 3አንተ ግን እልፍ እልፍ ሆነው በአንድ መቃብር የሚቀበሩ፥ አጥንታቸው የሚበሰብስ ሙታን ከሞቱ በኋላ እንዴት ይነሣሉ? እያልህ ልቡናህን አታስት። 4“ወደ መቃብርም በምታይ ጊዜ እፍኝ ሙሉ መሬት አይገኝም፤ የሞቱ ሰዎች እንዴት ይነሣሉ? እያልህ በልቡናህ ስንፍና ይህን ትናገራለህ። 5አንተ የዘራኸው ዘር አይበቅልም ትላለህን? አንተ የዘራኸው ዘር ስንኳ ይበቅላል። 6እንደዚሁም ሁሉ እግዚአብሔር የዘራቸው ነፍሳት ፈጥነው ይነሣሉ፤ እርሱ ሰውን በእውነቱ ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶታልና በሕይወት ሰጪ ቃሉ እነርሱን ማስነሣቱን አያዘገይም። 7ዳግመኛም ከመኖር ወደ ሞት ይመልሰዋል፤ ዳግመኛም ከሞት ወደ መኖር ይመልሰዋል። 8እግዚአብሔር ሕይወት መስጠትና ማስነሣት ይችላል።”