1አርሞንና ቅጥሮችዋ ወደቁ፤ እግዚአብሔርም እንደ ክፋታቸውና በእጃቸው እንደ ሠሩት ሥራ ከፍሎአቸዋልና በዛብሎንና በኤዶምያስ ጣዖቶችን የሚያመልኩ ያንጊዜ ይዋረዳሉ፤ በሕፃንነታቸው በሠሩት እስከ እርጅናም ድረስ ባልተዉት ስለ ጣዖታቸውና ስለ ክፋታቸው የሚፈርድባቸው ቀርቧልና ጢሮስና ሲዶና ያለቅሳሉ። 2ስለዚህም መዳራትንና ርኩሰትን፥ ዝሙትንም ስለ ሠሩ፥ ጣዖትንም ስለ አመለኩ እግዚአብሔር ይበቀላቸዋል። የይሁዳም ሴቶች ልጆች በፈጣሪያቸው በእግዚአብሔር ትእዛዝ አልጸኑምና ይዋረዳሉ። 3እንደ እርሷም በትንሣኤ ጊዜ የኢየሩሳሌም ውርደቷ ይገለጣል፤ በእግዚአብሔር ሕግና ፍርድ አልሔደችምና፤ ነገር ግን በደስታና ጻድቃንን በመግደል ኖረች። 4ያንጊዜ እግዚአብሔር በጥበቡ ብርሃን ይመራመራታል፥ በሕፃንነትዋ ወራት በሠራችው ሁሉ፥ በወጣትነቷም ወራት እስከ እርጅናዋ በአልተወችው ክፋቷ ሁሉ ይበቀላታል። 5በልማዳቸው እንደ ኖሩና የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንቢ እንደ አሉ፥ በትንሣኤም ጊዜ እንደሚበቀላቸው፥ እንደ ቀደሙት አባቶችዋ ወደ መቃብር ትገባለች፤ ዐመድም ትሆናለች። 6ሙሴ ስለ እነርሱ እንዲህ ብሎአልና፥ “የወይናቸው ቦታ እንደ ሰዶም የወይን ቦታ ሆነ። 7ሐረጋቸውም ከገሞራ ነው፤ ዘለላቸውም የሐሞት ዘለላ ነው፤ ፍሬያቸውም መራራ ነው። 8ወይናቸውም የዕባብ መርዝ ነው፥ ያውም የሚገድል የእፉኝት መርዝ ነው።”