1የኢየሩሳሌም ልጅ! በነቢዩ የተጻፈው ውርደትሽ ይህ ነው፤ የኢየሩሳሌም ልጅ! ሥራሽና በደልሽ እንደ ሰዶምና ገሞራ ሰዎች ሥራና በደል ነውና። 2ውርደትሽም እንደ ገሞራና እንደ ሰዶም ነው፤ የወይናቸው ቦታ በዝሙትና በትዕቢት ተተከለ። 3ከዝሙትና ትዕቢት፥ ከዐመፅና በደል፥ ከቅሚያና ደም ከማፍሰስ፥ የፈጣሪያቸው የእግዚአብሔርንም ስም ከመርሳት በቀር የትሕትናና የምሕረት ዝናም አልዘነመላቸውም። 4ከክፉ ሥራቸውና ከጣዖታቸው በቀር ፈጣሪያቸውን እግዚአብሔርንም አላወቁትም፤ በእጃቸውም ሥራ ደስ ይላቸዋል፤ ከከብትና ከወንድ ጋር ይሰስናሉ። 5እንዳያዩ ዐይኖቻቸው ታውረዋልና፥ እንዳይሰሙም የእግዚአብሔርን ፈቃዱንና የሚወደውን እንዳያደርጉ ጆሯቸው ደንቁሯልና፥ በሥራቸው እግዚአብሔርን አያውቁትም፤ እነርሱ የሰዶም የወይን ቦታ ናቸው። ወገናቸው የጣፈጠ ፍሬን የማያፈሩ የገሞራ ወይን ሐረግም ናቸው። 6ከተተከለበት ቀን ጀምሮ በርግማን ተተክሎአልና፥ አበቃቀሉም በጥፋት ዘመን ሆኗልና ወይናቸውን በጨመቁት ጊዜ የሚገድል መርዝ ይሆናል። 7የወይናቸው ተክል የሲዖልን ውኃ ጠጥቶአልና፥ ሐረጋቸውም በሐሩር ነፋስ ጸንቶአልና ሁልጊዜ ለወይናቸው ሐረግ መልካምነት የለውም። 8አፍርቶም በተጨመቀ ጊዜ ለመቅሠፍትና ለጥፋት ሆነ፥ የጠጡትንም ሰዎች ልቡናቸውን ያጸናዋል፤ የሚያጸይፉና ከእግዚአብሔር የሚርቁ ያደርጋቸዋል። 9በክፉ ሥራውም ይኖራሉና የዲያብሎስ ማደሪያ ያደርጋቸዋል፤ የሰዶም ሐረግም መብላት ትጀምራለች፤ ወደ ተራራዎቹም፥ ወደ ዛፎቹም ትወጣለች። 10በዙሪያዋ ያሉ የሚያመልኩትን ጣዖቱንም ትጋርደዋለች፤ ክፉና በጎን ለማያውቁ አጋንንትም ሴቶች ልጆችዋንና ወንዶች ልጆችዋን ትሠዋለች። 11ንጹሕ ደምንም ያፈስሳሉ፤ ከሰዶም ወይን ዘለዓለም ፍልቅ አድርገው ለጣዖቱ ያፈስሳሉ። 12ኢሎፍላውያን የሚያመልኩትን ዳጎንንም አክብራ ታመልካለች። 13ትሠዋላቸው ዘንድ፥ ፈቃዳቸውንም ታደርግ ዘንድ፥ ከሕፃንነቷ ጀምሮ እስከ ወጣትነቷ ድረስ፥ ዳግመኛም እስከ እርጅናዋ ወራትና እስከ ዕለተ ሞቷ ድረስ ሁልጊዜ የሚመግባትና የሚንከባከባት ፈጣሪዋ እግዚአብሔርንም እንዳታውቅ አጋንንት በአስተማሩአት መጠጣቸውና ስንፍናቸው ደስ ይላት ዘንድ ከመንጋዎችዋ የሰቡትን ትሠዋለታለች። 14ዳግመኛም በትንሣኤ ጊዜ እበቀላታለሁ፤ ወደ ሕጌ አልተመለሰችምና፥ በትእዛዜም ጸንታ አልኖረችምና ጊዜዋ እስከ ዘለዓለም ድረስ ይሆናል። 15አምላኮችዋ በእውነት ፈጣሪዎች ከሆኑ በቍጣዬ በተቈጣኋት ጊዜ፥ ከእርስዋም ጋር የሚሰስኑ ወዳጆችዋን በአራቅሁ ጊዜ ተነሥተው ወደ ገሃነም ሮጠው ያድኑአት። 16በቤቴና በንዋየ ቅድሳቴ ላይ ስድብንና ውርደትን እንደ አደረገች ሁሉ በሁሉ ዘንድ ጐስቋላ አደረግኋት። 17እነሆ ይህች የእግዚአብሔር ወገን ናት፤ የእስራኤል ፈጣሪ የእግዚአብሔር ቤት ናት፤ የልዑልም የስሙ ማደሪያ ናት፤ ከተለዩ የተለየች የገናናው ንጉሥም ከተማ ኢየሩሳሌም ሲሏት በእርሷ የተጠራ ስሜን አሳዘነች። 18እርሷ ባርያዬ እንደ ሆነች፥ እኔም ጌታዋ እንደ ሆንሁ በእኔ ትመካለች፤ እንደ ወንጀለኛ ትጠቃቀስብኛለች እንጂ ጌታዋ እንደ መሆኔ የምትፈራኝ፥ ፈቃዴንም የምታደርግ አይደለችም። 19ከእኔ ያርቋት ዘንድ ለማሳት መሰናክል ሆኑባት እንጂ ለማይመግቧትና ለማያሳድጓት፥ ለማያለብሷትም ለሌሎች አማልክት ትገዛለች። 20መሥዋዕት ትሠዋላቸዋለች፤ መሥዋዕታቸውንም ትበላለች፤ የመጠጡንም ቍርባን ታፈስላቸዋለች፤ የመጠጡንም ቍርባን ትጠጣለች፤ ዕጣን ታጥንላቸዋለች፤ የዕጣኑንም መዓዛ ታሸትላቸዋለች፤ ያዝዟታል፤ እርሷም ትታዘዝላቸዋለች። 21ዳግመኛም ወንዶች ልጆችዋንና ሴቶች ልጆችዋን ትሠዋላቸዋለች፤ ስለ ፍቅራቸውም ዕልል ትላለችና በእጅዋ ሥራና በከንፈርዋ ንግግር ደስ ይላታል። 22በፍርድ ቀን ለእርሷ ወዮላት፤ ለምትወዳቸውና ለምታቅፋቸው አማልክቶችዋ ወዮላቸው፤ ከእነርሱ ጋር ትሉ ወዳማያንቀላፋበት፥ እሳቱም ወደማይጠፋበት የታች ታች ወደ ሆነው ሲዖል ትወርዳለች። 23የፈጠርሁሽን እኔን ትተሽ ሌሎች አማልክትን አምልከሻልና ጐስቋላ የኢየሩሳሌም ልጅ ወዮልሽ። 24እኔም እንደ ሥራሽ ፍዳውን አመጣብሻለሁ፤ አሳዝነሽኛልና፥ ቃሌንም ቸል ብለሽዋልና፥ ሥራሽንም አላሣመርሽምና እንደ ተግዳሮትሽ እበቀልሻለሁ። 25አንቺ ቃሌን አሳዝነሽዋልና ትእዛዜን ትጠብቂ ዘንድ፥ እኔም ከአንቺ ጋራ እኖር ዘንድ፥ ከሚጣሉሽም ሁሉ አድንሽ ዘንድ፥ አንቺም ያዘዝሁሽን ትእዛዜንና ሥርዐቴን ትጠብቂ ዘንድ፥ ከኔ ጋራ በተማማልሽበት ቃል ኪዳኔ አልጸናሽምና እኔ ቸል እልሻለሁ፤ ፈጥኜም አላድንሽም። 26ይህንም ሁሉ አልጠበቅሽም፤ እኔም ቸል አልሁሽ፤ በፍርድ ጊዜም እበቀልሻለሁ፤ እኔ የፈጠርሁሽ አይደለምን? ቃሌንና ትእዛዜንም አልጠበቅሽም፤ የእኔም ወገን ትሆኚ ዘንድ አከበርሁሽ። 27ሰዶምና ገሞራ እንደ ተለዩ አንቺም ከእኔ ተለየሽ። 28እኔ በቍጣዬ አጠፋኋቸው፤ እኔ ካጠፋኋቸው ከሰዶምና ከገሞራ ወገን ነሽና፥ ወደ ጐልማሳ ሚስት በመሔድ፥ ከሴቶች ጋር እንደ መድረስ ከእንስሳና ከወንድ ጋራ ያለ ሕግ በመሰሰን፥ የፈጠርኋቸው እኔን አሳዝነውኛልና፥ በደስታቸው እንዳይኖሩ ስም አጠራራቸውን ከምድር አጠፋሁ። 29ከታናናሾቻቸው ጀምሮ እስከ ታላላቆቻቸው ድረስ በፊታቸው እግዚአብሔርን መፍራት የለም፤ በክፉ ሥራ ሁሉ ይረዱታል እንጂ እርሷን መሥራት ይተዉ ዘንድ አንዱ ሌላውን አይቈጣውም፤ ሥራቸው ክፉ ነውና ዐመፅንና በደልን የጠገቡ ናቸው። 30ክፉ ሥራ ሁሉ ቅሚያና ትዕቢት፥ ስስትም በአሳባቸው የተዘጋጀ ነው። 31ስለዚህም እግዚአብሔር ቸል አላቸው፤ ከተሞቻቸውንም ገለበጣቸው፤ እስከ መሠረታቸው ድረስ በእሳት ያቃጠላቸውም አሉ፤ እስከ ዘለዓለም ድረስ ፈጽመው ጠፉ እንጂ ከእነርሱ አንድ ስንኳ አልቀረም። 32በኀጢአት ታስረዋልና የዘለዓለም ፍርድ እስከሚሰጥባት እስከ ታላቋ የፍርድ ቀን ድረስ ይቈያሉ፤ በክፉ ሥራቸውም አሳዝነውኛልና አልምራቸውም፤ ይቅርም አልላቸውም። 33እኔም ቸል አልኋቸው፤ እንደዚሁም አንቺ ጐስቋላ የኢየሩሳሌም ልጅ፥ በፍርድ ቀን እንደ እነርሱ ትታሰሪያለሽ፤ ሥራሽ ሁሉ ቅሚያና ኀጢአት፥ ዝሙትና ስስት፥ ሐሰት መናገርም፥ እኔም የማልወደው የስሕተትና የድጥ መንገድ ስለ ሆነ ተቈጥቼ በያዝሁሽ ጊዜ ምክንያት አታገኝምና። 34እኔ ለክብር አድርጌሽ ነበር፤ አንቺ ግን ራስሽን ለውርደት አደረግሽ፤ እኔ ለእኔ ብዬሽ ነበር፤ አንቺ ግን ለሌላ ሆንሽ። 35እኔ ለቅድስና አጭችሽ ነበር፤ አንቺ ግን ለዲያብሎስ ሆንሽ፤ እኔም እንደ ሥራሽ ክፋት እበቀልሻለሁ። 36ቃሌን ሁሉ ስላልሰማሽ፥ በወደድሁሽም ጊዜ ያዘዝሁሽን ትእዛዝ ስላልጠበቅሽ የፈጠርሁሽ እግዚአብሔር እኔ ነኝና ክፉ በቀልን አበዛብሻለሁ፤ እንደ አንቺ ባሉ በኃጥኣንም ሁሉ ላይ እቈጣለሁ፤ እንደ ክፋታቸውም በፍርድ ቀን እከፍላቸዋለሁ። 37ቃሌንም አልጠበቅሽምና፥ ፍርዴንም ቸል ብለሻልና አንቺንም ከእነርሱ ጋር እቀጣሻለሁ። 38በልቡናችሁ እግዚአብሔርን መፍራት የሌላችሁ፥ ሰዶምና ገሞራ፥ ወዮላችሁ። 39በእሳተ ገሃነም ካንቺ ጋራ በአንድነት የሚፈረድባት እኅትሽ የኢየሩሳሌም ልጅ እንደዚሁ ወዮላት! ለዘለዓለሙ መውጫ ወደሌለበት ወደ ተዘጋጀው ወደ ገሃነም በአንድነት ትወርዳላችሁና ያንቺን ሥራ የሠሩ ሁሉ ወዮላቸው። 40ቃሌንና ትእዛዜን አልጠበቃችሁምና ቃሌንና ትእዛዜን ያልጠበቃችሁ አንቺና እርሷ በፍርድ ቀን በአንድነት ወደ ሲዖል ትወርዳላችሁ። 41ቃሌንና ትእዛዜን የጠበቁ ጻድቃን ግን ኃጥኣን ያደለቡትን ይበላሉ፤ ክፉዎች ሰዎች የማረኩትንም ምርኮ እግዚአብሔር እንደ አዘዘ ደጋጎች ይካፈላሉ፤ ጻድቃንና ደጋጎችም ደስ ይላቸዋል። ሐሤትንም ያደርጋሉ። 42በደለኞችና ኃጥኣን ግን ያለቅሳሉ፤ ከትእዛዜ ወጥተው ስለ በደሉት በደላቸው ሁሉ ያዝናሉ። 43ቃሌን የሚጠብቅ፥ በትእዛዜም የሚሔድ በረከቴን የሚያገኝ፥ በእኔ ዘንድም የሚከብር እርሱ ነው። 44ቃሌን የሚጠብቅ፥ ትእዛዜንም የሚያደርግ የምድርን በረከት ይበላል፤ ደጋጎችና ቅኖች ነገሥታት ወደሚገቡበትም ገብቶ ይኖራል።